PM Abiy Ahmed (L) and President Cyril Ramaphosa (R)

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ እና ፕ/ት ሲሪል ራማፎሳ

በድርድሩ ላይ የአፍሪካ ሕብረት ከሦስቱ አገራት መሪዎች ጋር መክሯል

ኢዛ (ማክሰኞ ጥቅምት ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 27, 2020)፦ በታላቁ ህዳሴ ግድብና በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ በሦስቱ ተደራዳሪ አገራት ተቋርጦ የነበረው ድርድር ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ይካሔዳል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።

በኢትዮጵያውያን ዘንድ ቁጣን የቀሰቀሰው የፕሬዝዳንት ትራምፕ ንግግር በተሰማ በቀናት ልዩነት የተቋረጠው የሦስቱ አገራት የሦስትዮሽ ውይይት፤ ዛሬ እንደሚቀጥል ይፋ ያደረጉት የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ናቸው።

“ግብጽ ግድቡን ልታፈነዳ ትችላለች” በሚል አነጋጋሪው የፕሬዝዳንት ትራምፕ ንግግር ላይ ምንም ዐይነት አስተያየት ያልሰጡት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት፤ ጉዳዩን ሦስቱ አገራት በጀመሩት መንገድ እንዲቀጥሉ ለማድረግ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፣ ከሱዳኑ ጠ/ሚ አብደላ ሐምዱክ እና ከግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታ አልሲሲ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ፤ ድርድሩን ለመቀጠል የዛሬው ፕሮግራም መያዙ ታውቋል።

ዛሬ በሚጠበቀው ድርድር ላይ የሚነሱ አጀንዳዎች ባይታወቁም፤ ከኢትዮጵያ ወገን በቅርቡ የፕሬዝዳንት ትራምፕን ንግግር ተከትሎ እየተሰማ ያለው ተቃውሞ በአገር ውስጥም ኾነ በውጭ አገሮች ቀጥሏል።

የተለያዩ ተቋማትም ይህንን የትራምፕን ንግግር በማውገዝ መግለጫዎችን ማውጣታቸውን ቀጥለዋል። የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና ሌሎች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት በንግግሩ ማዘናቸውንና ይህ ግን ኢትዮጵያ ከምታደርገው ግንባታ የማያስተጓጉላት መኾኑን የሚያመለክት መግለጫዎችን አውጥተዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ