ኢትዮጵያ ደህንነቷን የሚያስጠብቅ ህዝባዊ መንግሥት የላትም

Ethiopia Zare (ሐሙስ ግንቦት 27 ቀን 2001 ዓ.ም. June 4, 2009)፦ ጊዜው ቢረዝም እንጂ የዓባይ ጦርነት “አይቀሬ” መሆኑን የሕግና የታሪክ መምህር የሆኑት ኢትዮጵያዊ አቶ ፋሲል አምደፅዮን አስታወቁ። እኚህ ባለሙያ ከወደ አሜሪካ ሆነው የቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ በሚያሳትመው የሕግ መጽሔት ላይ ዓባይን የተመለከተ ለንባብ ባበቁት ጥናታዊ ጽሑፋቸው፣ “የውሃ ጦርነት የዓባይን አጠቃቀም ተከትሎ በምሥራቅ አፍሪቃ መቀስቀሱ የማይታበል እውነት መሆን ችሏል” ብለዋል።

 

በዓባይ ወንዝ ምክንያት የተፋሰሱ ሀገራት በተለይም ወንዙ የሚነሳባቸው ሀገሮች፤ ከግብፅና ከሱዳን ጋር አጠቃቀሙን በተመለከተ አግባቢ ስምምነት የላቸውም። ከዚህም በመለስ የወንዙ የባላይና የበታች ሀገራት ህዝብ ቁጥር ከዕጥፍ በላይ እየጨመረ በመሆኑ፤ ከወዲሁ መፍትሔ ያልተጣለለት ችግር መጨረሻው “የውሃ ጦርነት መሆኑ የማይቀር ነው” ሲሉ አቶ ፋሲል አምደፅዮን በጥናታዊ ጽሑፋቸው አመልክተዋል።

 

”... እ.ኤ.አ. በ1959 ዓ.ም. ካይሮ እና ካርቱም በፈጸሙት የተናጠል ስምምነት የአብዛኛው የዓባይ ውሃ ተጠቃሚ ራሳቸውን አድርገዋል። እነዚሁ “የዓባይ ውሃ ለእኛ ብቻ ነው የሚገባው…” ባይ ሀገሮች፤ በወንዙ ተጋሪ መንግሥታት የጋራ ጉባዔ ላይ በ1997 ዓ.ም. የተደረሰበትን ዓባይን በወል የመጠቀም የእኩል ተጠቃሚነት የመግባቢያ ነጥብ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ ፍላጎት የሌላቸው መሆኑን በግልጽ አሳይተዋል።

 

አቶ አስፋው ዲንጋሞ የኢትዮጵያ የውሃ ሀብት ሚኒስትር “ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝና በዚሁ ወንዝ ገባሮች ላይ ትኩረት በማድረግ የወጠነችውን የልማት ዕቅድ ገቢራዊ ከማድረግ አትቆጠብም” ቢሉም፤ ግብፅና ሱዳን ግን በቅርቡ በኮንጎ ኪንሻሳ የተደረገውን “የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የመቀራረቢያ አጀንዳ” ይዘት የጎሪጥ ከመመልከትና በአጀንዳው ጥቅል ይዘት ላይ የመረረ ቅሬታ ያላቸው መሆኑን ከማሳወቅ አልቆጠቡም።

 

ግብፅ የዓባይ ውሃ 55 ነጥብ 5 በመቶ ባለድርሻ ነኝ የምትል ስትሆን፤ የፈረጠመ ሆኖ የሚታየውን ወታደራዊ ጡንቻዋን የትምክህት መሣሪያ በማድረግ ተጨማሪ ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንደምትሻም ከማመልከት አልቦዘነችም። ሱዳን በበኩሏ 18 ነጥብ 5 በመቶ የዓባይ ውሃ ድርሻ “የእኔ ነው …” ባይ ስትሆን፤ የዚሁ ውሃ ሀብት ዋንኛ ምንጭና 85 እጅ ከመቶ ተፈጥሯዊ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ግን የበዪ ተመልካች ከመሆንና በራሷ ሀብት የሌሎችን ይሁንታ ጠባቂ ሆና ከመቀመጥ አላመለጠችም።

 

“ኢትዮጵያ በዘረኝነትና በጎሠኝነት ካራ 80 ቦታ ተቀርዳ መልሳ እንድትሰፋና ብሔራዊ ቁስሏም መድኃኒት እንዳያገኝ እንቅልፍ አጥተው በሚሠሩ የራሷ ቅጥረኛ አምባገነኖች እጅ የወደቀች ሀገር በመሆኗ ደህንነቷን የሚያስጠብቅ ህዝባዊ መንግሥት እንደሌላት ሆና ነው የምትቆጠረው። በዚህም የተነሳ የቱንም ያህል የህዝቧ ቁጥርና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሩ እየጨመረና እየተወሳሰበ ቢመጣም፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የካይሮንና የካርቱምን ተጽዕኖ እና የማያቋርጥ ዛቻ መክታ የዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነት ባለድርሻ ልትሆን አትችልም” እንደዘርፍ ባለሙያዎች እና የታሪክ ፓለቲካ አዋቂዎች ሰሞንኛ አስተያየት።

 

በአሁኑ ወቅት ከ245 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ የሚነገረው የዓባይ ተዋሳኝ ሀገራት ህዝብ ቁጥር፣ ከ16 ዓመታት በኋላ 860 ሚሊዮን ሊሆን እንደሚችል የጠቆሙት የሕግና የታሪክ መምህሩ አቶ ፋሲል አምደፅዮን፤ ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎቹ የዓባይ ባለድርሻ ሀገሮች ከወንዙ በጋራና በዕኩል ድርሻ ተጠቃሚ ለመሆን፤ በቀጣዮቹ ጊዜያት ጦርነትን ሊያስቀር ከሚችለው የስምምነት ነጥብ ላይ ከወዲሁ መድረስ የሚገባቸው መሆኑን አስምረውበታል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ