Prosperity Party

ብልጽግና ፓርቲ

ምርጫ በተካሔደባቸው በሁሉም ክልሎች ብልጽግና አሸናፊ ኾኗል

ኢዛ (እሁድ ሐምሌ ፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 11, 2021)፦ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ 2013 ተከትሎ ይፋ ባደረገው ውጤት መሠረት ለክልል ምክር ቤት በተደረገው ምርጫ አኛናፊ ፓርቲዎችን አሳውቋል። ለክልል ምክር ቤቶች በተደረገው ምርጫም ብልጽግና ፓርቲ አሸናፊ መኾኑን የሚያመለክት ኾኗል።

በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ ምክር ቤት ያሉትን 138 ወንበሮች ሙሉ ለሙሉ ብልጽግና ፓርቲ ማሸነፉን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። የአማራ ክልል ካሉት 294 መቀመጫዎች ምርጫ በተካሔደባቸው 125 ምርጫ ክልሎች ሲሆኑ፣ በምርጫ ቦርድ ውጤት መሠረት 128 የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎችን ብልጽግና ሲወስድ አብን 13 መቀመጫዎችን አግኝቷል። በአማራ ክልል ምርጫ ከተደረገባቸው 125 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በአምስቱ በድጋሚ ምርጫ የሚካሔድባቸው እንደሚኾን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

96 መቀመጫ ያለው ለአፋር ምክር ቤት በተደረገው ምርጫ ብልጽግና 51 ወንበር ሲያገኝ፣ የአርጐባ ሕዝብ ዴሞክራሲ ፓርቲ ደግሞ ሦስት ወንበር ያስገኘለትን ውጤት አግኝቷል። በአፋር ክልል በሰኔ 14ቱ ምርጫ ምርጫ የተደረገባቸው የምርጫ ክልሎች ብዛት 25 ሲሆኑ፤ በአምስቱ ድጋሚ ቆጠራ እንዲካሔድ፣ እንዲሁም በአንዱ የምርጫ ክልል ደግሞ ምርጫ የሚደረግበት እንደኾነ ተገልጿል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ የክልል ምክር ቤት የምርጫ ውጤትን በተመለከተ ቦርዱ እንዳስታወቀው በስድስት የምርጫ ክልሎች ምርጫ መካሔዱንና 22 ወንበሮችን ብልጽግና አሸንፏል። በአንድ ምርጫ ክልል ደግሞ ቆጠራ የሚካሔድበት ሲሆን፤ በአንዱ ደግሞ ድጋሚ ምርጫ ይከናወናል። የቤንሻንጉል ክልል ምክር ቤት 99 ወንበሮች ያሉት ነው።

189 ወንበሮች ባሉት የድሬዳዋ ምክር ቤት ደግሞ በ47 የምርጫ ክልሎች ምርጫ ተደርጐ 189ኙን ወንበር ብልጽግና አሸንፏል። ለጋምቤላ ክልል ምክር ቤት ምርጫ ብልጽግና 149 ወንበር ሲያገኝ፤ ጋህነን ሰባት መቀመጫዎችን አግኝቷል። በጋምቤላ ክልል ምርጫው የተካሔደው በ14 የምርጫ ክልሎች ሲሆን፣ የክልሉ ምክር ቤት ያለው ጠቅላላ ወንበር 156 ነው።

ከሌሎች ክልሎች የበለጠ የክልል ምክር ቤቶች ከፍተኛ የሚባለውንና 537 መቀመጫ ያለው የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት 513ቱን ወንበሮች ያሸነፈው ብልጽግና ነው። በሰኔ 14ቱ ምርጫ በኦሮሚያ ክልል ምርጫ የተካሔደባቸው የምርጫ ክልሎች 171 ናቸው።

10ኛ ክልል በመኾን በቅርቡ ምሥረታውን ባካሔደው የሲዳማ የክልል ምክር ቤት ያለውን 190 ወንበሮች ብልጽግና አሸናፊ እንደኾነ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ምክር ቤት 291 ወንበሮች ያሉት ሲሆን፣ በ89 የምርጫ ክልሎች በተደረገው ምርጫ ብልጽግና 243 ወንበሮችን ሲያገኝ፤ ኢዜማ 10 መቀመጫዎችን፣ የጌዲዮ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ፓርቲ ደግሞ ስድስት መቀመጫዎችን አግኝቷል።

በምርጫ ቦርድ መረጃ መሠረት በደቡብ ክልል ምርጫ ከተደረገባቸው 89 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በሦስቱ ድጋሚ ቆጠራ የሚካሔድባቸው ይኾናል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ