አዲሱ የዓባይ ድልድይ ለተሽከርካሪዎች ክፍት ሆነ
Ethiopia Zare (ዓርብ ታህሳስ 24 ቀን 2001 ዓ.ም. January 02, 2009)፦ አዲሱ የዓባይ ድልድይ በተመረቀ በአራት ወሩ በዚህ በያዝነው ሣምንት ለትራፊክ (ለተሽከርካሪዎች) አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ ክፍት መሆኑን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ ጠቆመ።
ባለፈው ዓመት ጳጉሜን 5 ቀን 2000 ዓ.ም. በጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ የተመረቀውና “ኅዳሴ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይኸው የዓባይ ዘመናዊ ድልድይ የተሠራው ከጃፓን ሀገር በተገኘ ለመንገድ ሥራ በተለገሰ የገንዘብ ዕርዳታ ሲሆን፣ ድልድዩ ብቻ ወደ 128 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ መፍጀቱ ታውቋል።
የጃፓን መንግሥት ከመዲናዋ አዲስ አበባ እስከ ደጀን ከተማ ድረስ ለሚወስደውና ይኸው የዓባይ ድልድይ ለሚገኝበት የ41 ኪሎ ሜትር ርቀት ለሚፈጀው የመንገድ ሥራ ወደ 320 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የገንዘብ ዕርዳታ ለኢትዮጵያ መለገሱ ታውቋል።
ድልድዩ 303 ሜትር ርዝመት፣ ዘጠኝ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ የመሸከም አቅሙ 300 ሜትሪክ ቶን እንደሆነ መዘገባችን አይዘነጋም። ድልድዩ በየጊዜው ተገቢው ጥገና ከተደረገለት ለአንድ መቶ ዓመታት ያገለግላል ተብሎ ይገመታል።
ይኸው አዲሱ ድልድይ ሁለት በተቃራኒ አቅጣጫ የሚተላለፉ መኪኖችን እንዲያሳልፍ ተደርጎ የተሠራ ሲሆን፣ ዘጠኝ ሜትር ስፋት እንዳለው ታውቋል። አሮጌው የአባይ ድልድይ አንድ መኪና ብቻ የሚያሳልፍ እንደነበር አይዘነጋም። ከዚህም ሌላ ለእግረኞች መሄጃ የሚሆኑ ግራና ቀኝ እያንዳንዳቸው አንድ ነጥብ አምስት ሜትር ስፋት ያላቸው ቦታዎች እንዳሉት ታውቋል።
ከዚህ ቀደም ከአዲስ አበባ ደጀን ድረስ በመኪና ለመጓዝ 10 ሰዓታት ይፈጅ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን 4 ሰዓታትን ይቀንሳል። በአዲሱ የዓባይ ድልድይና ከጎሃ ጽዮን ደጀን ድረስ በሚገኘው የ41 ኪሎ ሜትር መንገድ ከአዲስ አበባ ደጀን ለመጓዝ 6 ሰዓታት ብቻ እንደሚፈጅ ታውቋል።
አሮጌው የዓባይ ድልድይ ላለፉት 50 ዓመታት ያገለገለ ሲያገለግል እንደነበር ይታወቃል።



