Central Statistics Agency, Ethiopia

የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ

የሰኔ ወር የዋጋ ግሽበት መጠን እስከ ዛሬ ያልተመዘገበ ነው
የምግብ ነክ ምርቶች የዋጋ ግሽበት ከ28 በመቶ በላይ ወጥቷል

ኢዛ (ሐሙስ ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 8, 2021)፦ በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሠረት የሰኔ ወር የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ24.5 (ሃያ አራት ነጥብ አምስት) በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንና የምግብ ዋጋ ግሽበት ደግሞ በ28.7 (ሃያ ስምንት ነጥብ ሰባት) በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጿል።

ይህ የግሽበት መጠን በጥቂት ወራት ውስጥ ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ የመጣ መኾኑንና ከጥቂት ወራት በፊት 20 በመቶ አካባቢ የነበረውን ጭማሪ አሁን ላይ ወደ 24.5 (ሃያ አራት ነጥብ አምስት) በመቶ አድርሶታል።

እንደ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ትንተና፤ እስከዛሬ ድረስ በየዓመቱ በሰኔ ወር ከተመዘገቡ የዋጋ ግሽበቶች ውስጥ የዘንድሮው የዋጋ ግሽበት እጅግ ከፍተኛና በዚህን ያህል ደረጃ ተመዝግቦ የሚያውቅ መኾኑን ለመረዳት ተችሏል።

አሁንም የዋጋ ግሽበቱ እየቀጠለ መኾኑ አሳሳቢ ስለመኾኑና ይህንን ያለማቋረጥ እየቀጠለ ያለው የዋጋ ግሽበት ከዚህም በላይ እንዳይሔድ ካልተደረገ ቀላል የማይባል ቀውስ ያስከትላልም የሚልም ሥጋት እነዚህ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አላቸው።

በተለይ በምግብ ነክ ምርቶች ላይ የታየው የዋጋ ግሽበት አስፈሪ የሚባል በመኾኑ፤ መንግሥት የዋጋ ግሽበቱን ለመቀነስ የሚያስችሉ እርምጃዎች መውሰድ አለበትም ይላሉ።

አሁን ካለው ችግር አንጻር ጊዜያዊ መፍትሔ የሚኾኑ አሠራሮችን መዘርጋት ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የታየባቸውን ምርቶች በራሱ መንገድ በማሠራጨት ገበያውን ማረጋጋት የሚገባ ሲሆን፤ ከረዥም ጊዜ አኳያ ግን በፖሊሲ ደረጃ ሊታዩ የሚገባቸውን ውሳኔን በማሳለፍ ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም ባለሙያዎች እየገለጹ ነው።

በማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሠረት በአንድ ዓመት ልዩነት ምግብ ነክ ምርቶች ከ28 በመቶ በላይ እንዲያሻቅብ ካደረገባቸው ምክንያቶች መካከል በዳቦና በእህሎች ላይ የታየው ጭማሪ አንዱ ሲሆን፣ በተለይ በቆሎና ገብስ በእጥፍ መጨመራቸው የሰኔ ወርን የዋጋ ግሽበት በእጅጉ ከፍ እንዲል አድርጐታል።

በምግብ ዘይት፣ ቅቤ፣ በርበሬ፣ ቡና ሥጋ ቅመማቅመም ምርቶች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪም ግሽበቱ በተለየ ከፍ ማድረጉን ይጠቁማል።

ከምግብ ውጭ ያሉ ምርቶች ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የታየው የዋጋ ግሽበት 19 በመቶ መኾኑም ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ላይ እንደ መንግሥት የዋጋ ግሽበት ፈተና እንደኾነ ማመላከታቸው ይታወሳል። የዋጋ ግሽበቱ በኢኮኖሚ ረገድ የሚጠበቀውን ውጤት እንዲያመጣ ጭምር ማድረጉንም አመልክተው ነበር። ይህም ቢኾን መንግሥት ግሽበቱ ካለበት ከፍ እንዳይል መንግሥት በርካታ ሥራዎችን ቢሠራም፤ የተፈለገውን ያህል ውጤት ያለማምጣቱንም መጠቆማቸው ይታወሳል። በመኾኑም በ2014 በጀት ዓመት የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ወሳኝ ወሳኝ እርምጃዎች እንደሚወሰድ መጥቀሳቸው ይታወሳል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ