አዲሱ የዓባይ ድልድይ ተመረቀ
ስያሜው ”ኅዳሴ” ተብሏል
Ethiopia Zare (ኀሙስ መስከረም ፩ (1) ቀን ፳፻፩ (2001) ዓ.ም. September 11, 2008)፦ የዓባይ ድልድይ ያለበት እና ከጎሃ ጽዮን (ኦሮሚያ) እስከ ደጀን (ጎጃም) ድረስ ያለውን 40 ኪሎ ሜትር ርቀት የአስፋልት ሥራ 320 ሚሊዮን ብር ፈጅቶ እየተጠናቀቀ ሲሆን፣ የአባይ አዲሱ ድልድይ ረቡዕ ጳጉሜን 5 ቀን 2000 ዓ.ም. ተመረቀ። ስያሜው ”ኅዳሴ” ተብሏል።
አዲሱ የዓባይ ድልድይ ጥቃቅን ሥራዎች የሚቀሩት ሲሆን፣ የአስፋልት ሥራውም መቶ በመቶ ባለመጠናቀቁ ለትራፊክ አገልግሎት ክፍት አልሆነም። ድልድዩ ብቻውን 128 ሚሊዮን ብር (የጠቅላላ ፕሮጀክቱን 40 ከመቶ) የፈጀ ሲሆን፣ ሙሉ ወጪውን የሸፈነው የጃፓን መንግሥት መሆኑ ታውቋል። መሐንዲሶቹና ድልድዩን የሠራውም ጃፓናውያን እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል።
ድልድዩ 300 ሜትር ርዝመት፣ ዘጠኝ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ የመሸከም አቅሙ 300 ሜትሪክ ቶን እንደሆነ ታውቋል።
የላይኛው የድልድዩ ክፍል በጠንካራ ኬብል ተወጥሮ የተሠራ ሲሆን፣ በየጊዜው ተገቢው ጥገና ከተደረገለት ለአንድ መቶ ዓመታት ያገለግላል ተብሎ ይገመታል። ይኸው አዲሱ ድልድይ ሁለት መኪኖችን ጎን ለጎን ያሳልፋል። አሮጌው የአባይ ድልድይ አንድ መኪና ብቻ የሚያሳልፍ መሆኑ ይታወቃል።
ከዚህ ቀደም ከአዲስ አበባ ደጀን ድረስ በመኪና ለመጓዝ 10 ሰዓታት ይፈጅ የነበረ ሲሆን፣ የድልድዩና የመንገዱ ሥራው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ 4 ሰዓታትን ይቀንሳል። በአዲሱ የዓባይ ድልድይና ከጎሃ ጽዮን ደጀን ድረስ እየተሠራ ባለውና በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው የ40 ኪሎ ሜትር መንገድ ከአዲስ አበባ ደጀን ለመጓዝ 6 ሰዓታት ብቻ እንደሚፈጅ ታውቋል።
ድልድዩን የመረቀው ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ በቦታው ተገኝቶ ሲሆን፣ የዓባይ ድልድይ ስያሜ ”ሕዳሴ” መሆኑን ለመረዳት ችለናል።
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሣደር ኪኒቺ ኮማኖ እና ለጃፓን መሐንዲሶች ተወካይ ከጠ/ሚ/ር መለስ የምስጋና ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።



