ሕወሓት በደንሻ በኩል ጦርነት ከፍቷል
ሕወሓት
በዳንሻሕና በሌሎች ሁለት አካባቢዎች ሕወሓት ሊያደርስ የነበረው ጥቃት መክሸፉን አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ
ኢዛ (ረቡዕ ጥቅምት ፳፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 4, 2020)፦ በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የአገር መከላከያ ካምፕ ላይ ሕወሓት ጥቃት ማድረሱንና በዳንሻሕ በኩል ጦርነት መክፈቱ ተገለጸ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የቀዩ መስመር የመጨረሻው ነጥብ አልፏል አሉ። የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በደንሻና በሌሎች ሁለት አካባቢዎች ሕወሓት ሊያደርስ የነበረው ጥቃት መክሸፉን ገለጹ።
ትናንት ምሽት ላይ በሕወሕት የተፈጸመው ጥቃት በትግራይ ክልል የሚገኘውን የሰሜን ዕዝን ለመዝረፍ ሙከራ የተደረገበት ጭምር መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል የሚገኘው ጥቃት የተፈጸመበት ሠራዊት ከሃያ ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅ የቆየ ሠራዊት መኾኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ የትግራይን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል ነው ብለዋል።
ሕወሓት ግን እንደ ባዕድና እንደ ወራሪ አገር ሠራዊት ቆጥሮ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምታትና ለመዝረፍ መነሳቱንና በዳልሻሕ በኩል ጦርነት መክፈቱንም አስታውቀዋል።
የአገር መከላከያ ሠራዊት በኮማንድ ፖስት እየተመራ አገሩን የማዳን ተልእኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ እንደተሰጠው ዶ/ር ዐቢይ ተናግረዋል።
የቀዩ መስመር መጨረሻ ታልፏል በማለትም አገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ መኾኑንም አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩልም በአማራ ክልል በኩል በደንሻ አካባቢ በሕወሓት የፈጸመውን ጥቃት በአማራ ክልል ልዩ ኃይል የክሸፈ ስለመኾኑ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገልጸዋል። ቀጣይ ጥቃት በአካባቢው በኩል እንዳይፈጸም ለክልሉ የጸጥታ ኃይል ትእዛዝ መሰጠቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገልጸው፤ በደንሻና በሌሎች ሁለት አካባቢዎች ከሕወሓት በኩል የተሰነዘረ ጥቃት መክሸፉንም አስታውቀዋል። (ኢዛ)



