PM Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

"የመከላከያ ሠራዊቱ በኮማንድ ፖስት እየተመራ አገሩን የማዳን ተልዕኮ ተሰጥቶታል" ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

ኢዛ (ማክሰኞ ጥቅምት ፳፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 3, 2020)፦ ሕወሓት ትግራይ ውስጥ የሚገኘውን የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ካምፕ ማጥቃቱንና የዘረፋ ሙከራ ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ ሌሊት አስታውቁ። የመከላከያ ሠራዊቱ በኮማንድ ፖስት እየተመራ አገሩን የማዳን ተልዕኮ ተሰጥቶታል ብለዋለ።

በብዙዎች ዘንድ ሲጠበቅና ሰፈራ የነበረውና አይቀሬ መኾኑ የተገመተው የሕወሓትና የፌዴራል መንግሥቱ መካከል ግጭትና ጦርነት ዛሬ ማምሻውን እንደተጀመረ ተገምቷል። ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ያስተላለፉት ሙሉ መልእክት የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

ሕወሓት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል። ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል። ይህ ሠራዊት ከሃያ ዓመታት በላይ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅ የቆየ ሠራዊት ነው። በቦታው የሚገኘውም የትግራይን ሕዝብ ከጥቃት ለመከላከል ነው። ሕወሐት ግን እንደ ባዕድና እንደ ወራሪ ሀገር ሠራዊት ቆጥሮ፤ የመከላከያ ሠራዊቱን ለመምታትና ለመዝረፍ ተነሥቷል። በዳልሻሕ በኩልም ጦርነት ከፍቷል።

መንግሥት የትግራይ ሕዝብ እንዳይጎዳ በማሰብ፣ ጦርነት እንዳይፈጠር የትእግሥቱ ጫፍ ድረስ ታግሷል። ጦርነት የሚቀረው ግን በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ አይደለም።

የመከላከያ ሠራዊታችን በኮማንድ ፖስት እየተመራ አገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል። ቀዩ መሥመር የመጨረሻው ነጥብ ታልፏል። አገርና ሕዝብ ለማዳን ሲባል ኃይል የመጨረሻው አማራጭ ኾኗል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ እንዲከታተል፣ በየአካባቢው ሊከሠቱ የሚችሉ ትንኮሳዎች በንቃት እንዲቃኝና ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን እንዲቆም ጥሪ አቀርባለሁ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ