A sea of protesters in Debre Markos

የተቃውሞ ባሕር በደብረ ማርቆስ ከተማ (ፎቶ ከማኅበራዊ ትስስር ገጾች የተወሰደ)

ኢትዮጵያን የምንል ከኾነ ሰዎች በዘራቸው ሳይኾን በሰውነታቸው ለምን ይጐዳሉ ብለን በአንድ ላይ መጠየቅ አለብን

ያለአግባብ ለሞተው አማራ፤ የአማራ ሕዝብ ብቻ ድምፁን ማሰማት የለበትም፤ በለውጡ ዋዜማ በኦሮሚያ ክልል ቄሮ ወጣቶች ላይ ግድያ ሲፈጸም የአማራ ወጣቶች “የኦሮሞ ደም ደሜ ነው” ብለው የወጡትን ልብ ይሏል

ኢትዮጵያ ዛሬ (ርዕሰ አንቀጽ) - ሰሞኑን በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ተካሒደዋል። ዘር ላይ ትኩረት ያደረገ ግድያ እንዲቆም የተጠየቁባቸው ሰልፎች ከለውጡ ወዲህ እጅግ በርካታ ነዋሪዎች ለተቃውሞ አደባባይ የወጡበት ስለመኾኑ ይጠቀሳል።

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ዘር ላይ ያተኮረውን ጥቃት በመቃወም አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች ግድያና ስደት ይቁምልን ከሚል ጥያቄያቸው ባሻገር መንግሥት ንጹሐን ያለኃጢአታቸው በየቦታው መገደላቸውን ሊያስቆም ያለመቻሉንም በብርቱ ያወገዙባቸው ናቸው።

የሰልፉ ዓላማና መልእክት ጠብ የሚል ነገር የለውም። ክቡሩ የሰው ልጅ ደም በስመ ታጣቂ ደሙ ሲፈስ እየታየ ዝም መባል የለበትም። ግድያ ይቁም ማለት ተገቢ ጥያቄ ነው። በአብዛኛዎቹ ቦታዎች የተደረጉት ሰልፎች ሰላማዊ ኾነው መጠናቀቃቸውም ጥያቄን በአግባቡ የማቅረብ ልምምድን የሚያሳይ በመኾኑ፤ ይበል የሚያሰኝ ነው።

አልፎ አልፎ ወጣ ያሉ የሰልፎቹን ዓላማ የሚቃረኑ መልእክቶች ቢስተዋሉም፤ የሕዝቡ ጥያቄ ለዓመታት የተጠራቀመ ብሶት ውጤት መኾኑን ግን መረዳት ተገቢ ነው።

አሁንም ቢኾን በኢትዮጵያ ምድር በተለይ ዘርን መሠረት አድርጐ የሚፈጸሙ ግድያዎች ይቆሙ ዘንድ ሕዝብ ድምፁን ማሰማት አለበት። ነገር ግን አገሪቱ በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች በተወጣጠረችበት በዚህ ሰዓት የዜጐች አርቆ አሳቢነት በእጅጉ አስፈላጊ ነው።

ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥል ከተፈለገ ሰከን ብሎ ማሰብን ይጠይቃል። ግርግር ለሌላ ይመቻል እንደሚባለው አጋጣሚው አገርን የበለጠ እንዳያተራምስና የበለጠ ጉዳት እንዳያደርስ መጠንቀቅ አለበት። በዚህ ሰዓት በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በእጅጉ አሳሳቢ መኾኑ ባያጠያይቅም ከዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ለመውጣት የተሻለው የቱ ነው ብሎ በማየት የሚከፈለውን መሥዋዕትነት መቀነስ ያስፈልጋል።

በምንም መለኪያ በዚህ ሰዓት ይቺን አገር የሚያስተዳድረው ፓርቲና የፓርቲው መሪዎች ኃላፊነት ደግሞ በእጅጉ ከፍ ያለ በመኾኑ በታሪክ አጋጣሚ የተቀበሉትን ኃላፊነት፤ አሁንም በአግባቡ በመጠቀም የሕዝብን ጥያቄ በሚመልስ መልኩ ሊሠሩ ካልቻሉ፤ ሕዝቡን በማዳመጥ የሚያረጋጋ ተግባር ካልፈጸሙ የአገራችን እጣ ፈንታ አደገኛ ሊኾን ይችላል ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ብዙ ምርምር የሚያስፈልገው አይደለም። ሕፃን ልጅ እንኳ የሚመልሰው ጥያቂ ነውና።

በተለይ ጽንፍ ይዞ የሚደረግ የቃላት ተኩስ መፍትሔ ካለመኾኑም በላይ፤ ለአገር ውድቀት ምክንያት ይኾናል። ስለዚህ ማንኛውም እንቅስቃሴ የሰዎችን ሰከን ብሎ ማሰብ የሚጠይቅ ነው።

ከሰሞኑ የተቃውሞ ሰልፎች አንጻር ሌላው መጠቀስ ያለበት ጉዳይ ደግሞ፤ በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተካሔዱ ሰልፎች ዜጐች ያለአግባብ አይጨፍጨፉ የሚል ነው። ጥቃቱ በአማራ ሕዝብ ላይ ያነጣጠረ ነው ተብሎ ሰልፎቹ የተካሔዱትም በክልሉ ከተሞች ነው።

እንደ ሰብአዊ ፍጡር ግን ሰው ምንም ዘር ይኑረው ብሔር፤ በሰውነቱ ብቻ ያለአግባብ ሊገደል አይገባም። እንደ ኢትዮጵያዊ እናስብ ከተባለ፤ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሞቱት ሰዎች “አማራ” ብቻ በመኾናቸው የምንጮህላቸው መኾን አይገባም። ማሰብ ያለብን ንጹሕ ኢትዮጵያዊ ተጐዳ ብለን መኾን አለበት። የአንድ አገር ልጆች ነንና በየትኛውም ቦታ ሰው ሲሞት “ለምን ሞተ?” ብሎ መጠየቅ የአማራው ጥያቄ ብቻ መኾን የለበትም። ባለፉት 27 ዓመታት የተጋትነው የዘር ፖለቲካ ግን ይህን ክፉ ነገር አስተምሮናል።

ለአካባቢ ተወላጅ ሞት ብቻ ድምፅ የምናሰማ ከኾነ አደጋ ነው። ሰልፍ የምንወጣው የሰው ልጅ ያለአግባብ ተገደለብን ብለን መኾን አለበት። በለውጡ ዋዜማ በኦሮሚያ ክልል ቄሮ ወጣቶች ላይ ግድያ ሲፈጸም የአማራ ወጣቶች “የኦሮሞ ደም ደሜ ነው” ብለው የወጡትን ልብ ይሏል።

ስለዚህ ተቃውሟችንንም፣ ድጋፋችንንም በዘር ለይተን ከማድረግ እንቆጠብ። ያለአግባብ ለሞተው አማራ፤ የአማራ ሕዝብ ብቻ ድምፁን ማሰማት የለበትም። ያለአግባብ ለሚሞት ኦሮሞ፤ የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ተቆርቋሪ ኾኖ መውጣት የለበትም። በሌላውም ብሔር እንዲሁ። ኢትዮጵያን የምንል ከኾነ ሰዎች በዘራቸው ሳይኾን በሰውነታቸው ለምን ይጐዳሉ ብለን በአንድ ላይ መጠየቅ አለብን።

የአንዱ ጉዳት የእኔም ነው ካልተባለ፤ ሕወሓት ቀብሮልን የሔደው ፈንጅ ላይ እየቆምን እንዳንጠፋፋ ማሰብ ግድ ነው።

እንደ ኢትዮጵያዊ እናስብ!

አገራችንን ካጋጠማት ችግር ትወጣ ዘንድ ፈጣሪ ይርዳን!! (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ