የእሳት ነበልባል

የእሳት ነበልባል (ፎቶው ከሸዋ ሮቢትም ኾነ ከአጣየ ጋር ግንኙነት የለውም)

ሕዝብ እየጠየቀ ያለው መንግሥት የማንን ጎፈሬ እያበጠረ ነው እነዚህ ኃይሎች በጠራራ ፀሐይ እንዲህ ያለውን ድርጊት እየፈጸሙ ያሉት? “መንግሥት” ካለ ለዚህ ጥያቄ ምላሹ ምንድነው?

ኢትዮጵያ ዛሬ (ርዕሰ አንቀጽ) - ከሳምንታት በፊት በተደራጁ ታጣቂዎች አጣየና ሸዋ ሮቢት ላይ የተቃጣው ግድያና ጥቃት አሁንም ሰፍቶ አጣየና ሸዋ ሮቢት ከተማን እያወደመ ስለመኾኑ እየተነገረ ነው።

በአጣየና ሸዋ ሮቢት ቤቶችና ቤተእምነቶች እየተቃጠሉ፣ ንብረት እየወደመም መኾኑን የሚገልጹት መረጃዎች ከየአቅጣጫው እየተሰሙ ነው።

ያልታጠቁና ንጹሕ ሕዝብ እየተገደለ፣ የተረፈውም ሕይወቱን ለማትረፍ ባገኘው መንገድ እየተሰደደ፣ ፍዳው እየበዛበት ነው። መንግሥት ከሳምታት በፊት አጣየና ሸዋ ሮቢት ላይ የግፍ ጭፍጨፋ ሲፈጸም ነገሩን ለማረጋጋት ተብሎ የክልልና የጸጥታ ኃይሎች ወደ አካባቢው ሔደው አጣየና ሸዋ ሮቢትን እያረጋጉ ነው በተባለ በጥቂት ሳምንታት ወይም በቀናት ልዩነት የአጣየና የሸዋ ሮቢት ጐጆዎችና ቤተእምነቶች እየነደዱ ነው ለምንድነው የሚባለው?

ይህ አካሔድ እንዲህ በዋዛ የሚታይ አይደለም። አገር ሲወድም መንግሥት አለ ወይ? የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ ደጋግመን እንድናነሳ ያደርገናል። እንደ አጣየና ሸዋ ሮቢት ባሉ ከተሞች ውስጥ የተፈጸመ ጭካኔ የተሞላባቸው ድርጊቶች በኦነግ ሸኔና በሌላም ወገን ላይ እያላከኩ መርዶ ነጋሪ እየተኾነ መሔድ አያዋጣም።

የጥቃቱ አድራሾች ስም ካላቸው ይታወቃሉ፤ ከታወቁ ነጋ ጠባ ዜጐችን መግደል፣ ንብረታቸውን ማቃጠል እንዲህ ቀላል የኾነላቸው አጋዥ ስላላቸው ነው የሚለውን መደምደሚያ ሕዝብ እንዲይዝ አድርጎታል።

አሁን ባለው የክልልም ኾነ የፌዴሪል መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በየመንደሩ እየዞሩ ሰዎች የገድሉ ታጣቂ ኃይሎችን ለመደምሰስ የሚያስችላቸው መኾኑ እየታወቀ፤ እነዚህ አካላት ላይ እርምጃ ለመውሰድ የዚህን ያህል መዘግየቱ ድርጊቱን እንደመደገፍ የሚቆጠር ተደርጐ ይወሰዳል።

ምክንያቱም ዛሬ ጥቃት አድራሾች ናቸው የተባሉ ቡድኖች የለበሱት ወታደራዊ ልብስ፣ እየተጠቀሙበት ያለው መሣሪያ እና ይህንኑ መሣሪያ ይዘው ሲንቀሳቀሱ የማርያም መንገድ እየተሰጣቸው እንጂ በምንም ሁኔታ በዚህ ደረጃ ጥቃት እየፈጸሙ ሊቆዩ እንዴት ይችላሉ?

ዜጐች በገዛ አገራቸው የሚኖሩበት ቤት፣ የሚሠሩበት ተቋም፣ ልጆቻቸው የሚማሩበት ትምህርት ቤት፣ ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበት እና የሚለማመኑበት ቤተ እምነት ጭምር በእሳት እየነደደ ዜጐች ፈጽሞ ደኅንነት ላይ አይደሉም። ከዚህ ፍዳቸው የሚያስጥላቸው ከመንግሥት ሌላ ኃይል አይኖርም። በዚህ ሰዓትም መንግሥት የዜጐቹን ደኅንነት ከመጠበቅ እና ከማስጠበቅ ሌላ ምንም ሊያስቀድም አይችልም። ሥራውም ይህ ነው።

ስለዚህ ችግሩ መንግሥት ጋር ጭምር ስለኾነ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ካልተቻለ፤ አደገኛ ብቻ ሳይኾን መንግሥት አለ ወይ? የሚለውን ጥያቄ ደጋግመን እንድናነሳ ያስገድደናል። ሕዝብ እየጠየቀ ያለው መንግሥት የማንን ጎፈሬ እያበጠረ ነው እነዚህ ኃይሎች በጠራራ ፀሐይ እንዲህ ያለውን ድርጊት እየፈጸሙ ያሉት? “መንግሥት” ካለ ለዚህ ጥያቄ ምላሹ ምንድነው? (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ