በዘር ፖለቲካ የተጠለፉት አባገዳዎች

ዘር ተኮር ጥቃቱን በመቃወም ድምፃቸውን ያሰሙ የደብረ ማርቆስ፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን እና ደብረ ታቦር ነዋሪዎች
በዘር ተኮር ጥቃት ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አዛውንቶች በጠራራ ፀሐይ ሲጨፈጨፉና ከተማ እንዳልነበር ኾኖ ሲወድም አፋቸው ተለጉሞ የነበሩት አባገዳዎች፤ መፈክር ለመቃወም አፋቸው ተከፈተ
ኢትዮጵያ ዛሬ (ርዕሰ አንቀጽ) - ኢትዮጵያውያን በዚህ ወቅት አንገት የምንደፋበት እንደ አገርም ቁልቁል እየወረወረን ያለ ነገር ቢኖር በጐጥና በዘር ተከፋፍለን እንድንኖር የተቀደደውን ቦይ ተከትለን ከመጓዝ እምቢኝ አለማለታችን ነው።
በጐጥ እና በብሔር ተከፋፍለን ድንጋይ እንድንወራወር ያደረገን ኃይል ተወገደ ሲባል፤ እኛም ነቅተን ስለአንድነታችንና ስለጋራ አገራችን መዘመር ሲገባን፤ እኛም በቀደመው ቦይ የምንፈስ ከኾነ ሕዝብ ታግሎ ያስወገደው ሥርዓት በአካል ባይኖር እኛ ተግባሩን እየፈጸምን እያኖርነው ነው ማለት ነው። ለውጥ መጣ ሲባል እኛም መለወጥ ካልቻልን የሚለወጥ ምንም ነገር አይኖርም።
ዛሬም ሁሉም ፖለቲካ ክንውኑን የሚያስኬደው ዘርና ብሔር ቆጥሮ ነው። ይህ ከኾነ ከቀደመው ጊዜ በተለየ እየተጓዝን ያለመኾኑን ያሳየናል። እንደ ቀድሞ እየተኖረ፣ እንደ ቀድሞው ብሔሬ እና ሰፈሬ የሚለውን አጉል ዜማ እያቀነቀኑ፤ አገርን ማሳደግ፣ ኢትዮጵያን ማሻገር አይቻልም።
ዛሬ ንጹኀን የሚሞቱት በተደገሰልን የዘር ፖለቲካ ሸፍጥ መኾኑን እያወቅን እንኳን እየተማርንበት አለመኾኑ የዚህች አገር ነቀርሳ ኾኖ ቀጥሏል።
ፖለቲካው የእምነት ደጃፍ ድርሶ፤ ክብር የሚገባቸው እና ክብር የምንሰጣቸው የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች የዚሁ የዘር ፖለቲካ ሰለባ ኾነው ሲታዩ ደግሞ የአገር ሕመም ብሷል ማለት ነው።
ሰሞኑን በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል ዘር ላይ ትኩረት ያደረገውን ጥቃት በመቃወም የተካሔደው ሰልፍ ላይ ተሰማ የተባለው ያልተገባ ተግባርን ይዘው አባገዳዎች የሰጡትን መግለጫ ልብ ይሏል።
አብዛኛው ሰልፍ ሰላማዊ ቢኾንም፤ አንዳንድ ቦታዎች የብሔር ስም በመጥቀስ የተመለከትናቸው ጥቂት መፈክሮች በእርግጥም ተገቢ አልነበሩም። ምናልባትም ሰከን ብሎ ካለማሰብና ከስሜታዊነት የተንጸባረቀ ወይም ኾን ተብሎ ነገር ለማካረር እጅግ በጣም ጥቂቶች የፈጸሙት ነው ሊባል ይችላል።
ከዚህ አንጻር አባገዳዎች ሰጡ በተባለው መግለጫም እንዲህ ብሔርን ከብሔር ሊያጋጩ የሚችሉ መፈክሮች መታየታቸው ተገቢ አልነበረም ማለታቸውም ቢኾን ስሕተት የለውም። ችግሩ ግን እኒህ አባቶቻችንን ደፍረን ጥያቄ እንድናነሳባቸው የሚያደርግ ኾኖ መገኘቱ ነው። ይህም በኦሮሚያ በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ሲገደሉና ሲፈናቀሉ አንድም ቃል ሳይተነፍሱ፤ ዛሬ ተገቢ ያልኾነ መፈክር ታይቷል ብለው ይህንን ለማውገዝ ብቅ ማለታቸው እንደ አንጋፋ አባትነታቸው ትክክል ናቸው ተብሎ ስለማይታሰብ ነው።
ገዳዮቹ የራሳቸው ወገን የኾኑትን ኢትዮጵያውያንን በጠራራ ፀሐይ ሲደፉ አንድም ቃል ሳይናገሩ፤ ዜጐቻችን ናቸውና ለምን እንዲህ ይኾናል ብለው እንደ ሽማግሌነታቸው ድርጊቱን ሳያወግዙ እና በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ማለት በሚጠበቅባቸው ወቅት ምንም ሳይሉ አፋቸውን ዘግተው ተቀምጠው ሲያበቁ፤ መፈክርን ለማውገዝ ደፍረው መግለጫ ማውጣታቸው፤ የሃይማኖት አባቶቻችንም፣ የአገር ሽማግሌዎቻችንም ጭምር በዘር ፖለቲካ ስለመጠለፋቸው የሚያሳይ በመኾኑ የአገራችንን ሁኔታ በእጅጉ አሳዛኝ እያደረገው ነው።
መሬት ላይ ካለው እውነት አፈንግጦ ለመምከርና ለማሸማገል ዘር እና ብሔር እየጐተተን ለስንት የምንጠብቃቸው አባቶች ሚዛናዊ ዳኝነት ሲጠበቅባቸው እንዲህ ባለ ደረጃ ስናገኛቸው ምን ሊባል ይችላል?
የፖለቲካ ልሂቃኖች በጽንፈኝነት ሲያራግቡ የነበረው የዘር ፖለቲካ ለዚህች አገር ነቀርሳ ኾኖ ዛሬ ላለንበት ደረጃ እንዳደረሰን እየታወቀ፤ ጐንበስ የምንልላቸው የሃይማኖት አባቶቻችን በአንድ ወገን ብቻ ያዩትን ለመቃወም መነሳታቸው ተገቢ አይኾንም። ሽማግሌ ሚዛናዊና አስታራቂ መኾን ይገባው ነበር ብለን ደፍረን ለመናገር የምንገደደውም፤ የከፋ ነገር ቢመጣ እኒህ ሽማግሌዎች፤ “ነገር አብርዱ፤ አንተም ተው! አንተም ተው!” ብለው አገር በማረጋጋቱ ሒደት ተስፋ የሚደረግባቸው በመኾኑ ጭምር ነው። ነገር ግን እዚህ በተቃራኒ በኾነ መንገድ ካገኘናቸው፤ የብሔር ፖለቲካ ምን ያህል እየሸራረፈን እና እየደቆሰን መኾኑን የምናይበት ኾኗል።
ይህ ማለት ግን አባገዳዎቹ ያወገዙት መፈክር መታየት ወይም መሰማት ነበረበት ማለት አለመኾኑ ልብ ሊባል ይገባል።
ጥቂቶቹ አውቀውም ኾነ ሳያውቁ በፈጠሩት ስሕተት የሰልፎቹን ዓላማ ዋጋ እንዳይኖረው መሞከር ተገቢ አይደለም።
አወዛጋቢ የነበሩት መፈክሮች በእርግጥም ስሕተት እንደነበሩ በማመን የአማራ ክልል መንግሥት በግልጽ ማውገዙንም ካሰብን፤ እንደ ሽማግሌ ነገሩን የሚያበርድ ምክር በመለገስና ያለአግባብ የሞቱትን ዜጐችም በማስታወስ ሚዛናዊ መግለጫ ቢሰጥ ይመረጥ ነበር።
በተለይም ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ በአማራው ላይ በተነጣጠረው ዘር ተኮር ጥቃት ሕፃናትን፣ ሴቶችና አረጋውያንን ጨምሮ በዙኀን ሕይወታቸው ሲሰዋ፣ ንብረታቸው ሲወድም፣ በሰሜን ሸዋ ከተማ ሲወድም አንደበታቸው ተለጉሞ የነበሩት አባገዳዎች፤ ለክቡሩ የሰው ልጅ ሕይወት አላግባብ መጥፋት ድምፃቸውን ሳያሰሙ፤ ብሶተኞች አላስፈላጊ መፈክር አስምተዋል ብለው ለተግሳጽ ብቅ ማለታቸው፤ እንደ አገር ምን ያህል መጥፋታችንን ያሳያል።
ለማንኛውም በኢትዮጵያችን እንዲህ ባሉና በመሰል አመለካከቶች እንድትቀጥል ሊፈቀድ አይገባም።
በአካባቢ እሳቤና በሰፈር ልጅነት ላይ ተመሥርቶ ብቻ የሚሰጡ ማንኛውም አመለካከቶች ችግራችንን ያብሳሉ እንጂ አያሻሽልምና አሁንም ነገራችንን ሁሉ ከጋራ ጥቅማችንና አንድነታችን አንጻር እንቃኝ። እንንቃ! የዘር ፖለቲካን መሠረት ያደረገ አደገኛ ጨዋታችንን እናቁም። ምክንያቱም ማናችንንም አይጠቅምም!! (ኢዛ)