በንቁጣጣሽ! ምን ቀጠፈሽ? (ወለላዬ)
ወለላዬ ከስዊድን
ዘመን ፊትሽ ተከምሮ

እየታየ ሥራሽ አምሮ
እንቁጣጣሽ አንድ ብለሽ
አርባ ድረስ ዕድሜ ቆጥረሽ
እንደ ቤቶች የሳቅ ተውኔት
እንደ ጨቤ ስካር ሕይወት
ሞት ራሱን ያሾፍሽበት
ለምንድነው? በይ ንገሪኝ
እባክሽን አደብቂኝ
ባንቺው ቀዬ የተወለድኩ
ፊደል በጄ እዛው የያዝኩ
መስፍን ሜዳ የተራገጥኩ
በጨበጣ ብይ ያስቆጠርኩ
ቲቸር ታዬ ያስተማሩኝ
ገብሬ ኩርኩም ያቀመሰኝ
የሲሚንቶ ጭስ ያወዛኝ
ቅዱስ ያሬድ ተሳልሜ
ከሽፋ ቤት ተሰይሜ
ያቶ ማሞን ኪኒን ቅሜ
እዛው ኖሬ እዛው ያደኩ
የቃጠሎው ቀን የተረፍኩ
እኔ እማውቅሽ የማታውቂኝ
የሰፈርሽ አንድ ሰው ነኝ
ይሄን ሁሉ ዘርዝሬልሽ
ጥያቄዬን ስጠይቅሽ
ዝም አትይም መቼም ከፍተሽ
ፊት ለፊትሽ ተስፋሽ ሞልቶ
እየታየ ዝናሽ ጎልቶ
እንደጸደይ ባገር ፈክተሽ
በህዝብ ፊት ደምቀሽ ታይተሽ
በአዲስ ዓመት በንቁጣጣሽ
በዕለቱ ለት ምን ቀጠፈሽ?
መታሰቢያነቱ ለአርቲስት ሰብለ ተፈራ ይሁንልኝ!



