በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እና በብልጽግና ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ እየተሰማ ነው
 
		በአማራ ክልል በጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ እና በፓርቲያቸው ላይ ተቃውሞ እየበረታ ነው
በኢትዮጵያ ተደጋግሞ የተከሰተውና በተለይም የዘር ጥቃት ጭፍጨፋዎች ልክ አጣ ያሉ ወገኖች “አሁንስ በዛ!” በማለት ድምፃቸውን በአደባባይ ማሰማት ጀምረዋል
ሪፖርታዥ ኢዛ (ሰኞ ሚያዝያ ፲፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 19, 2021)፦ በሰሜን ሸዋ እና በአጣየ አካባቢ የደረሰው ጥፋትና ውድመት እስካሁን በውል ያልታወቁ ሰዎችን ሕይወት ሲያጠፋ፤ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በተለይ በአጣየ የዜጐች ቤት እና ንብረት በእሳት ተበልቷል። በለስ ቀንቷቸው ሕይወታቸውን ለማዳን በእግርና በተሽከርካሪዎች ተጭነው የወደመ ቤታቸውን አመድ እየተረማመዱ በገዛ አገራቸው ለመሰደድ ግድ ኾኖባቸዋል።
በታጠቁ ኃይሎች ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖቻቸውን አፈር ሳያቀምሱ፤ የዘመናት ሀብታቸውን ተነጥቀው የተሻለ ወዳሉት ሌላኛው የአገሪቱ ክፍል ለስደት የበቁት ዜጐች ቁጥር በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ኾኗል። ተከላካይ አጥተው ለሞት የተዳረጉት፣ ንብረታቸውን ያጡትና መሰደድ የቻሉትን ለመደገፍ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ቢጀመሩም፤ በኢትዮጵያ ተደጋግሞ የተከሰተውና በተለይም የዘር ጥቃት ጭፍጨፋዎች ልክ አጣ ያሉ ወገኖች “አሁንስ በዛ!” በማለት ድምፃቸውን በአደባባይ ማሰማት ጀምረዋል። ዛሬ በደሴና በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተው እስከ ዛሬ ብዙም ባልተለመደ እና መንግሥትን በአደባባይ ያወገዙበትን ትእይንተ ሕዝብ አካሒደዋል። ይኽ የተቃውሞ ድምፅ መሰማት የጀመረው በትናንትናው ዕለት ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም የተቃውሞ ድምፃቸውን አሰምተዋል።
በአጣየና በሰሜን ሸዋ የተፈጸመውን እጅግ ዘግናኝ የኾነውን ድርጊት መንግሥት ሳይከሰት በቁጥጥር ሥር ማዋል ይገባዋል የሚል እምነት ያላቸው ወገኖች ከወትሮው በተለየ ጠንከር ያለ ተቃውሞ እየቀረቡ መምጣታቸው፤ ሁኔታውን አሳሳቢ ከማድረጉም በላይ መንግሥት ላይ ጫና እያሳደረ ስለመምጣቱ እየተነገረ ነው።
በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ላይ እየተሰማ ያለው ተቃውሞ ከሌሎች ጊዜያት የተለየ መኾኑን ለመገንዘብ የተቻለ ሲሆን፤ ከተሞች ከወደሙ በኋላ እየተወሰደ ያለው የመንግሥት እርምጃ የዘገየ ነው በሚል እየተተቸም ነው። በተለይ የአጣዬ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት ከኾነ፤ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትነት ከመጡ ወዲህ ይኽኛው ጥቃት ለስድስተኛ ጊዜ መኾኑን አስረድተዋል።
በተለይ በደሴ ከተማና በአማራ ክልል ከተሰሙ የተቃውሞ መፈክሮች ውስጥ “ዐቢይ ሌባ፣ ብልጽግና የአማራን ሕዝብ አይወክልም፣ ብልጽግና የውሸትና የፈጠራ ታሪኮች ይከልከሉ፣ ውሸታምና አስመሳይ መንግሥት ይውረድ፣ የሕዝብ ስቃይ የማይሰማው መንግሥት አንፈልግም፣ አማራን እየገደሉ ኢትዮጵያን መግዛት የከሰረ ፖለቲካ ነው፣ መንግሥት የጥላቻ ፖለቲካን አስወግድ፣ ፍትሕ ለአማራ ሕዝብ፣ …” የሚሉ ይገኙበታል።
የሰሞኑን ጥቃት ተከትሎ ሸዋ ሮቢት እና አጣየ አካባቢዎች በኮማንድ ፖስት ሥር እንዲኾኑ መወሰኑና መከላከያ መግባቱን ተከትሎ በአካባቢው የተኩስ ድምፅ የቆመ መኾኑ ቢነገርም፤ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለሕግ ማቅረብ እስካልተቻለና ዜጐች የሚካሱበት ሁኔታ በቶሎ ቢፈጸም እንኳን አሁን እየተሰማ ያለው የሕዝብ አስተያየት እና ተቃውሞ ነገሩን ይቅር ለማለት የሚከብድ ነው የሚል አመለካካቶች እየተንጸባረቁ ነው።
ይህ ብቻ ሳይኾን የሰሞኑ የሕዝብ ቁጣ በአጣየና በሸዋ ሮቢት አካባቢ የተፈጸመው ሰሞናዊ ድርጊት የወለደው ብቻ ሳይኾን፤ ተጠረቃቅሞ አሁን ላይ የደረሰ ስለመኾኑ በጉዳዩ ዙሪያ እየተሰጡ ያሉ አስተያየቶች ያመለክታሉ።
ገዳይና አሳዳጁን እንኳን በቅጡ ለማወቅ ባልተቻለበት ሁኔታ በአጣየና በአካባቢው የተፈጠረው ዘግናኝ ድርጊት፤ ነገ ተሻግሮ ሌሎች አካባቢዎችን ላለመድረሱ ማረጋገጫ እንኳን የለንም የሚል የሕዝብ አመለካከትን በማሳደሩ፤ ነገሩን የበለጠ አሳሳቢ እያደረገው ነው። ወትሮም ብዙ ችግሮች ያሉበትን ፖለቲካ እየወጠረው ከመኾኑም በላይ፤ በቅርቡ በሚካሔደው ምርጫ 2013 ላይም ጥቁር ነጥብ እየጣለ ነው።
በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የምርጫ ጣቢያዎች መራጩን ለመመዝገብ የተቸገሩበት አንዱ ምክንያት የጸጥታ ችግር መኾኑ እየተገለጸ ሲሆን፤ የተመዝጋቢዎች ቁጥር በተፈለገው ደረጃ እንዳይገኝ የሰሞኑ ድርጊት አበርክቶ አድርጓል እየተባለ ነው።
ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ምርጫ ይታዘባሉ ተብለው ከሚጠበቁት አንዱ የኾነው የአውሮፓ ሕብረት ዛሬ ሰኞ ሚያዝያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በጉዳዩ ላይ መግለጫ አውጥቷል። የአውሮፓ ሕብረት ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ ወደ ኢትዮጵያ የምርጫ ታዛቢ ከመላካችን በፊት አገሪቱ አሁን ያለችበትን ሁኔታ በቅርብ ማጤን አለብን ከማለቱም በላይ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ከምርጫው በፊት የብሔራዊ መግባባት መድረክ ለመፍጠር ቁርጠኝነት ማሳየት ይኖርበታል በማለት ገልጿል። ይህ የአውሮፓ ሕብረት አቋም ምርጫው ላይ ያለውን ለየት ያለ አቋም የሚያንጸባረቀ ነው የሚል ግምት አሳድሯል።
የሰሞኑ ክስተት በዜጐች ላይ ካደረሰው ጥፋት ባሻገር፤ አሁን ያለውን የፖለቲካ አካሔድ ሊቀይረው ይችላል የሚል ትንታኔ እንዲሰጥበት እያደረገ ነው። ከመንግሥት ወገን በተለይ በአጣየና በሸዋ ሮቢት አካባቢ የደረሰውን ውድመት ተከትሎ የጸጥታ ኃይል ወደ አካባቢው ገብቷል።
ባለፉት ሁለት ቀናት ተኩሱ የቆመ ቢኾንም፤ በከተማዎቹ ላይ ዘርን መሠረት ያደረገ ጥቃት ያደረሱት ታጣቂዎች እስካሁን በአካባቢው መሽገው እንደሚገኙ ታውቋል። በዚህም ምክንያት አሁንም ሕብረተሰቡ በሥጋት ላይ ይገኛል። ከዚህም ሌላ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ፣ ከአካባቢው የሸሹ ወገኖች እና ቤቶቻቸው የተቃጠሉባቸው የከተማዎቹ ነዋሪዎች ወደ ከተማዎቹ አልተመለሱም።
የሰሞኑን ግጭት እንቆቅልሽ ያደረገው ደግሞ ጥቃት አድራሾቹ በትክክል እነማን ናቸው? የሚለውን የለየ አለመኾኑ ነው። አንዳንድ መረጃዎች የጥቃቱ አድራሾች ኦነግ ሸኔዎች አይደሉም ሲሉ፤ ሌሎች ደግሞ የጥቃቱ አድራሾች ሌሎች ታጣቂዎች ናቸው የሚሉም አሉ።
የአማራ ክልላዊ መንግሥትም እነዚህን በጠላትነት የፈረጃቸውን ታጣቂዎች ለማጽዳት ከፌዴራል ጋር በመቀናጀት እየሠራ መኾኑን አስታውቋል። ለተጐጂዎቹም ከየአቅጣጫው እርዳታ እየተደረገ መኾኑም ተገልጿል።
ከሰሞኑ በአጣየና በሸዋ ሮቢት የደረሰውን የሕይወትና የንብረት መውደም አስመልክቶ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባዔ፤ ለሕይወት መጥፋቱና ለንብረት መውደሙ የመንግሥት ቸልተኝነት ነው ብሏል። መንግሥት የዜጐችን ደኅንነት እንዲያስጠብቅ ጭምር ያሳሰበው ጉባዔው፤ እንዲህ ያለው ጥቃት የመጀመሪያው አለመኾኑን አስታውቋል።
ጥቃት የሚካሔድባቸው አካባቢዎች ተለይተው የሚታወቁ በመኾኑ በአካባቢዎቹ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ አስፈላጊ የጸጥታ መዋቅር በመዘርጋት ሕዝቡን መጠበቅና መከላከል እንደ አንድ መፍትሔ መወሰድ አለበትም ብሏል።
ጉባዔው አጽንኦት ሰጥቶ ከሁሉም በላይ ለችግሩ ምንጭ የኾነው ሕገመንግሥቱና የአገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት መስተካከል አለበት በማለት አቋሙን አንጸባርቋል። (ኢዛ)



