ቆምጨጭ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሎ - ፪
 
		የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጋር ዛሬ (ማክሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም.) ውይይት ሲያደርጉ
- በኢትዮጵያ አንገቴ ይቀላል እንጂ አይደረግም
- የሰብአዊ መብት ጥያቄዎችና የሕወሓት ጉዳይ ያበቃለት መኾን
ኢዛ (ረቡዕ መጋቢት ፲፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 24, 2021)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የትናንት ማክሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በፓርላማ ውሏቸው ቆምጨጭ እና ቆጣ በማለት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ መስጠታቸውን በክፍል አንድ መዘገባችን ይታወሳል። በዚህኛው ሪፖርታዥ ደግሞ በሰብአዊ መብት ጥያቄዎች፣ በሕወሓት ጉዳይ ማብቃት ላይ እና በአሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት ጫና ለመፍጠር በሚያደርጉት ሙከራ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሾች እና ማብራሪያዎች አጠናክረናል።
በኢትዮጵያ አንገቴ ይቀላል እንጂ አይደረግም
በትግራይ ክልል ከተወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጋር ተያይዞ ለኢትዮጵያ መንግሥት እንደፈተና ተቆጥሮ የነበረው የሕወሓት ቡድን በውጭ ሠርቷል የተባለው ዲፕሎማሲያዊ ተግባር ነው። ሎቢስት በመግዛት ጭምር የኢትዮጵያን መንግሥት ለማጠልሸትና አገሪቱ ማዕቀብ እንዲጣልባት የተደረገው ጥረት ተጠቃሽ ነው።
አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት ከዚህ አንጻር የተንሸዋረረ አመለካከት ይዘው ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረግ ሲያወጡዋቸው የነበሩት መግለጫዎች ለኢትዮጵያ የተመቸ አልነበረም።
እነዚህ አገራት በትግራይ ክልል ተፈጸመ ያሉትን ተግባር በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመሥርተው የሚያስተጋቡት ነው ቢባልም፤ ከኢትዮጵያ አንጻር በቂ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ባለመሠራቱ የኾነ ነው ተብሎም ሲሰነዘር የነበረው ትችት ከእውነት የራቀ ነው የሚባል አይደለም።
ከሁሉም በላይ ግን በትግራይ ክልል የተደረገውን ሕግ የማስከበር ዘመቻ ተከትሎ እንደ አሜሪካና አንዳንድ የአውሮፓ አገራት፤ በትግራይ ክልል ጉዳይ አስጨንቆናል (concern አለን) ብለው ሲያስተጋቡ የነበሩት መልእክት ከእጅ ጥምዘዛ ጋር የተያያዘ ስለመኾኑ በግልጽ የታየበት ነው ማለት ይቻላል።
በማክሰኞው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ውሏቸው ይህንኑ ያረጋገጠ አንደበታቸውን ሰምተዋል። ኮንሰርን አለን ብለው የሚለፍፉቱ የምዕራብያውያን አንዳንድ ባለሥልጣናት እውነታውን ትተው የተንሸዋረረ መንገድ መርጠው፤ ኢትዮጵያን ለማስጐንበስ ያደረጉት ጥረት ኢትዮጵያን ያለማወቅ ስለመኾኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረግጠው ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከአንዳንድ አክቲቪስቶችና አንዳንድ አካላት አሁን ያለውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ከአገር መበታተን ሥጋት ጋር ሲያያይዙት ይታያል።
ኢትዮጵያ እንደ ሶሪያ እና የመን ትኾናለች፤ እንደ ሊቢያ ውጥንቅጧ ይወጣል የሚለው አስተያየታቸው በተደጋጋሚ ሲነሳ የሚሰማ ቢኾንም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ ይህንን አመለካከት ውኃ የማይቋጥር መኾኑን የተለያዩ ምሳሌዎችን ጠቅሰው አስረድተዋል። እንዲህ ያለ ሥጋት ያላቸውን ወገኖች የፓልም እና የፓፓያ ዛፍ ለዩ ነበር ያሉት።
የኢትዮጵያና የሶሪያ ሁኔታ ፈጽሞ እንደማይገናኝም በመግለጽ፤ የኢትዮጵያ ሁኔታን ካለማወቅ የመነጨ መኾኑንም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ትበታተናለች የሚለው አመለካከት በተለይ በዚህ ወቅት ፈጽሞ የማይኾን መኾኑን እና ኢትዮጵያ ትበታተናለች የሚለው አመለከከት ጊዜው ያለፈበት፤ ፈጽሞ ትበተናለች የሚለው የማይኾን መኾኑን ነው። አሁን ላይ 0.01 በመቶ እንኳን እድል የሌለ መኾኑን ቆምጬጭ ባለ አገላለጽ አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለእነዚህ የውጭ ሰዎች የምላቸው ብለው እንደገለጹትም፤ የፓፓያ ዛፍ እና የፓልም ዛፍ አይቀላቀልባችሁ፤ ይመሳሰላሉ እንጂ አንድ አይደሉም። ኢትዮጵያንና የመንን፣ ኢትዮጵያንና ሶሪያን፣ … የሚያገናኝ ነገር የለም።
ኢትዮጵያ የራስዋ መልክ ቅርፅ እና ማንነት አላት። ለሚያጋጥማት ነገር የምትፈታበት መንገድም በዚያ ላይ የተመሠረተ ነው። እኛ የሞራል ልእልና ያለን ሰዎች ነን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሞራል የእውነት ልእልና ስላለ ነው ኦፕሬሽን ያሸነፍነው። ወደ ፊትም የምናሸንፈው ብለው አክለዋል።
የኢትዮጵያ ታሪክ የገባቸው እንዳሉ ሁሉ እጅ ለመጠምዘዝ የሚፈልጉም እንደነበሩ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለውጭ አገራትና ሰዎች ባስተላለፉት መልእክት “እንድታውቁት የምፈልገው በኢትዮጵያ ክብርና ጥቅም ከመጣችሁ አንገቴ ይቀላል እንጂ አይኾንም የሚል ነው። በመጠምዘዝ የሚኾን ነገር የለም። ተላላኪ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ አይፈጠርም” በማለት ነበር።
የሰብአዊ መብት ጥያቄዎችና የሕወሓት ጉዳይ ያበቃለት መኾን
በትግራይ ክልል ተፈጽሟል ተብሎ ስለሚነገሩ ጉዳዮችም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ ውጊያ ጥፋት ነው ብለዋል። ብዙዎችን የሚጐዳ በመኾኑ በትግራይ ክልልም የደረሱ ጥፋቶች ስለመኖራቸው አመልክተዋል። የሚወራው፣ የሚጋነነውን፣ የሚዋሸው እና ፕሮፖጋንዳው ቀርቶ፤ ሴት በመድፈር፣ ንብረት በመዝረፍ ጥፋቶች እንደተካሔዱ መረጃዎች የሚያመለክቱ መኾኑንም ገልጸዋል።
እንዲህ ባለው ጉዳይ ከአገር መከላከያ ሠራዊት ጋር ሳምንት የፈጀ ግምገማ ማካሔዳቸውን ገልጸው፣ በትግራይ ክልል የተካሔደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ሦስት ዓላማዎች እንደነበሩት በማስታወስ፤ አንደኛው ወንጀለኞችን ለሕግ ማቅረብ ነው።
ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያን አምነው ለአገር ክብር የቆሙ ወታደሮቻችንን ከእግት ማስለቀቅ ነው። ሦስተኛው ዓላማ የትግራይ ክልል ሕዝብ፤ ሕዝባችን ስለኾነ ራሱ የሚፈልገውን ኃይል በምርጫ እንዲያስተዳድር ማድረግ ነው።
የሕወሓት ጉዳይ ግን ያበቃለት እና እንደ ዱቄት የተበተነ መኾኑን በመግለጽ፤ የሕወሓት ጉዳይ ያበቃለት ስለመኾኑም ለፓርላማ አሳውቀዋል።
ከትግራይ ክልል ወቅታዊ አንጻር ካነሱዋቸው በርካታ ነጥቦች ውስጥ ሌላው ነጥብ፤ ሕወሓት ሽምቅ ውጊያ ውስጥ እገባለሁ ለሚለው የሰጡት ምላሽ፤ ጥቅም የሚባል ነገር እንደማይኖር ነው። ዘመኑ ለሽምቅ አይኾንም። ዓለም መቀየሩን ማስተዋል ነው። ያኔ የነበረው የነበረው ፖለቲካ ከባቢ ዛሬ ተለውጧል፤ አያዋጣም ብለዋል።
ሕወሓት እንደ ተቋም የሚያደርገውን ነገር አጥፍተነዋል ያሉት፤ ነገር ግን የሚፈለጉት ወንጀለኛ ግለሰቦች ሲገኙ ለሕግ ይቀርባሉ በማለት የገለጹት ዶክተር ዐቢይ፤ “የአገር መከላከያ ሠራዊት አባል ኾኖ በትግራይ እኅቶቻችን ላይ መድፈርን፣ መዝረፍን የፈጸመ ማንኛውም ወታደር በሕግ ይጠየቃል” ብለዋል።
አያይዘውም “ወታደሮቻችንን ጁንታውን ምቱ እንጂ፤ ሕዝባችንን አጐሳቁል አላልንም። ይጠየቃል” በማለት የመንግሥታቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።
በአካባቢው የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥቃቶችም የተለያየ ደረጃ የሚቀርብ ስለመኾኑ ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ተግባር የተሳተፈ ግን ተጠያቂ መኾኑን ያረጋገጡበትም ነበር። (ኢዛ)



