ሕብረት ሠላሙ

በኢትዮጵያውያን የታወቁ፤ ሶስት ጳውሎሶች አሉ። ዋነኛው፤ የኢየሱስ ክርስቶስ ባለሙዋል፤ ዝነኛው፤ ተአምረኛው፤ ሰማእቱ፤ ድንቅ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ነው። ሁለተኛው፤ ሰሞኑን በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን "ብሩክ" በመሰኘት የተወደሱት፤ ፖፕ ጳውሎስ ሲሆኑ ሶስተኛው ደግሞ የኛው፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሪ፤ አቡነ ጳውሎስ ናቸው።

ሓዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፤ የኢየሱስ ክርስቶስን ትምሕርት በዓለም እንዲሰራጭ ካደረጉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና ሐዋርያዎች አንዱ ከመሆኑ በላይ፤ ለእምነቱ ራሱን መስዋእት ያደረገ ታላቅና ቅዱስ መንፈሳዊ አባት በመሆኑ፤ በከፍተኛ ደረጃ የሚከበር ትምሕርቱም የመጽሓፍ ቅዱስ አካል ሆኖ የሚገኝ ሰው ነው።

እስቲ የሌሎቹን ሁለት መንፈሳዊ መሪዎች፤ ጳዎሎሶች፤ ሁኔታ እናስተያየው።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪ የነበሩት፤ ፖፕ ጳውሎስ፤ ሕይወታቸውን በሙሉ ለእውነተኛ ክርስቲያናዊ ተግባር ያሰማሩ፤ በጠንካራ መንፈሳቸውና እጅግ አስደናቂ አገልግሎታቸው ደረጃ በደረጃ እያደጉ ፖፕ እስከ መሆን የደረሱ አባት ነበሩ። ከታወቁባቸው ታላላቅ መንፈሳዊ ገድሎች፤ ፖላንድ በኮሙኒስቶች በምትሰቃይበት ጊዜ የፈጸሙዋቸው ትግሎች፤ እንዲሁም ከአምላክ በተሰጣቸው ፀጋ ሰዎችን ከልዩ ልዩ ደዌዎች መፈወሳቸው፤ እንዲሁም፤ ብዙ ሐገሮች በመጉዋዝ ክርስቲያኖች እንዲቀራረቡ፤ እንዲተጋገዙና እምነታቸውን እንዲያጠናክሩ ያደርጉ የነበረውና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የበለጠ እንድትጠናከር ያከናወኑት ከፍተኛ ጥረት ነበር። በሕዝብ መሐል ሲጉዋዙም በክፍት መኪና እንጂ ጥይት በማይበሳው እጅግ ከፍ ያለ ወጪ በሚያስከፍል መኪና ውስጥ እየተደበቁ አልነበረም። ለእግዚአብሔር ያደሩ፤ መንፈሳዊ አባት ስለ ነበሩ፤ አንድ አክራሪ እስላም በጥይት ቢመታቸውም፤ ሕይወታቸው ተርፎ፤ ወንጀለኛውን ሰው አቅርበው ይቅር ያሉ ታላቅ ክርስቲያን ነበሩ። በተጨማሪም፤ ሊነገርላቸው የሚገባ ጉዳይ፤ ለዚህ ዓለም ጥቅም ያልዋሉ አባት ስለ ነበሩ፤ በሙስና የተዘፈቁ፤ በመብለጭለጭ የቅንጦት ኑሮ የሚወዱ አልነበሩም። በሌላ በኩል፤ አንድ ሳይጠቀስ መታለፍ የማይገባው ጉዳይ፤ ናዚ ጀርመኒ በአይሑዶች ላይ እልቂት ስትፈጽም፤ የቫቲካን መንግሥት ተቃውሞ ባለማሰማቱዋ ፖፕ ፖል አይሑዶችን ይቅርታ ሲጠይቁ፤ የኢጣልያን ፋሺሽቶች ከቫቲካን ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ላይ ለደረሰው የጦር ወንጀል ይቅርታ ሳይጠይቁ ቀርተዋል። ከዚህ ሌላ፤ ፖፕ ፖል ታላቅ መንፈሳዊ አባት እንደ ነበሩ ዓለም ያወቀላቸው ሰው ነበሩ።

የኢትዮጵያው አቡነ ጳውሎስስ?

የኢትዮጵያው "ፓትሪያርክ"፤ አቡነ ጳውሎስ፤ ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት ታላላቅ ጳዎሎሶች የተለዩ ናቸው።

(ሀ) በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሕግ መሠረት፤ የባላይ ባለሥልጣኑ ፓትሪያርኩ ሳይሆኑ ቅዱስ ሲኖዶሱ ነው። ቢሆንም፤ እጅግ በሚያሳዝን፤ በሚያሳስብና በሚያሳፍር ሁኔታ፤ "አቡነ" ጳውሎስ፤ በወያኔ ድጋፍ፤ የሲኖዶሱን ውሳኔዎች በመናቅ የቤተ ክርሲቲያኑዋን ሕግ እየጣሱ ነው። ለዚሁም አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ፤ "አቡነ" ጳውሎስ ለራሳቸው ያሠሩት ሐውልት እንዲፈርስ ያሳለፈው ውሳኔ ተንቆ ይገኛል። በዚህ አጋጣሚ፤ አንዳንድ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤ በ"አቡነ" ጳውሎስ አማካኝነት ብዙ ወከባ፤ የሚኖሩባቸው ክፍሎች እስከ መሰበር ድረስ፤ጥቃት ቢደርስባቸውም፤ በእምነታቸው በመጽናት፤ ባለፈው ጉባኤያቸው፤ ብዙ ለቤተ ክርስቲያን የሚጠቅሙ ውሳኔዎች ማሳለፋቸው፤ የሚያስመሰግናቸው መሆኑን መግለጽ ይገባል። ውሳኔዎቹ ሥራ ላይ ሳይውሉ ቢቀሩ፤ ተጠያቂነቱ የ"አቡነ" ጳውሎስ እንደሚሆን አይጠረጠርም። በመጨረሻም፤ "አቡነ" ጳውሎስ፤ በፈጸሙት ሕጸጽ ምክንያት ከ"ፓትሪያርክ" ማእረጋቸው እንዲሻሩ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ መወሰኑ አይቀሬ ሊሆን ይችላል። የቅዱስ ሲኖዶሱን ውሳኔዎች አክብረው ቢገኙ ግን ከታሪክ ነቀፋና ከውግዘት ፍርድ ሊድኑ ይችላሉ።

(ለ) ምንም ሳይሠሩ "ብፁእ ወቅዱስ" ተብለዋል። የማእረጋቸው ስያሜም በጣም ረጅም ነው። "መልከ-ጥፉን ......" እንደሚባለው ነው።

(ሐ) በተለይ ከሥራ ውጤታቸው ጋር ሲመዛዘን፤ የኛው ጳውሎስ፤ አንዳችም ቁም-ነገር ያለው የሥራ ውጤት ሳያሳዩ፤ እጅግ አሳፋሪ በሆነ መንገድ ለራሳቸው ሐውልት አሠርተዋል።

(መ) የዚህን ዓለም ጥቅምና ሥልጣን ከምንም በላይ ይወዳሉ። የርሳቸው አለኝታም እግዚአብሔር መሆኑ ያጠራጥራል። ምክንያቱም፤ እንደሚባለው፤ በመደጋገም የሚያነበንቡት፡ "መለስ ካለ ምንም አልሆንም" እያሉ ነው! ከኮሙኒስቱ መለስ ዜናዊ፤ ቤተ ክርስቲያን ድርሽ ብሎ ከማያውቀው፤ የክርስቶስ ጠላት ጋር እጅና ጉዋንት ሆነው፤ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን በቤተ ክሕነት ውስጥ በመሰግሰግ፤ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን፤ ካሕኖችና ምእመናን ፍዳ እያሳዩ ነው።

(ሠ) ሕይወታቸውን ለምንኩስና ኑሮ መድቤያለሁ ያሉት "አቡነ" ጳውሎስ ሥልጣን ሲጨብጡ የመጀመሪያ ተግባራቸው ያደረጉት፤ እርዳታ በማጣት የተቸገሩትን ደብሮች፤ ገዳሞችና የአብነት ትምሕርት ቤቶች መደገፍ ሳይሆን፤ ከልክ ባለፈ የቅንጦት ተግባር መዋዠቅ ነበር። ከነዚሁ ውስጥ ሊጠቀሱ የሚገባቸው፤ አስፈላጊ ያልሆነ የተንዛዛ ቤተ መንግሥት ማሠራታቸው፤ በወርቅና ሌላ ጌጣ ጌጥ እንዲሁም በነጭ ሐርና በተንቆጠቆጠ ቀሚስ እያሸበረቁ መታየታቸው የማያሳፍራቸው መሆኑ፤ በብዙ ሚሊዮን በተገዙ መኪናዎች መጠቀማቸው፤ በእውነተኛ ሱባኤ ፈንታ ለዓለማዊ መዝናናት ቅድሚያ የሚሰጡ መሆናቸው፤ ወዘተ. ወዘተ. አሉ።

(ረ) በቤተ ክርስቲያኑዋ፤ አስተማማኝ ቁጥጥር ስለ ሌለ፤ ሙስና ተንሰራፍቶባት ይገኛል። ለዚሁም አስከፊ ሁኔታ ዋናው ተጠያቂ፤ መሪው፤ "አቡነ" ጳውሎስ ናቸው። ከየደብሩ ከሚገኘው ገቢ በግድ የሚሰበስበው ገንዘብ ለርሳቸውና ለጥቂት የወንጀል ተባባሪዎቻቸው የግል ጥቅም እየዋለ ነው። መንግሥት ተብዬውም የጥቅሙ ተጋሪ ስለ ሆነ ጆሮ ዳባ ብሎዋል። የቤተ ክርስቲያኑዋ ንብረቶች እንደ ወ/ እጅጋየሁ ባሉ ተጠቃሚዎች በርካሽ ኪራይ እየተቸበቸቡ፤ ለግለ ሰቦቹና ለ"አቡነ" ጳውሎስ ከፍተኛ ጥቅም እያስገኙ ነው።

(ሰ) ቤተ ክርስቲያንዋ፤ ለተቸገሩ ሰዎች መጠጊያ በመሆን ፋንታ መጠቂያ ሆናለች። ለምሳሌ ያህል፤ ባሕታዊ ፈቃደ ሥላሴ የተባሉ መነኩሴ በ"ፓትሪያርኩ" አጃቢዎች መገደላቸው፤ ቤተ ክርስቲያን ተጠግተው የነበሩ ተማሪዎች "ፓትሪያርኩ" በጠሩዋቸው ፖሊሶች መደብደባቸውና መታሰራቸው፤ በየደብሩ፤ ተቃውሞ ያሰሙ ምእመናን በታጣቂዎች መደብደባቸውና መንገላታታቸው፤ ወዘተ. ሊጠቀሱ ይችላሉ።

(ሸ) አክራሪ እስላሞች ደብሮችን ሲያቃጥሉ፤ እንዲሁም ካሕናትንና ምእመናንን ሲገድሉ፤ "አቡነ" ጳውሎስ አንዳችም ድምፅ ሳያሰሙ ቀርተዋል።

(ቀ) ኢየሩሳሌም የሚገኘው ታሪካዊ የኢትዮጵያ ገዳም ጥገና በማጣት በመፍረስ ላይ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም "አቡነ" ጳውሎስ ምንም እርምጃ አልወሰዱም።

(በ) በቫቲካን ተደግፎ የነበረው የፋሺሽት ጦር በኢትዮጵያ ውስት ከፈጸማቸው ወንጀሎች ውስጥ የደብረ ሊባኖስ ገዳም መነኮሳትን መጨፍጨፉ፤ አቡነ ጴጥሮስንና አቡነ ሚካኤልን መግደሉ፤ እንዲሁም 2፣000 ቤተ ክርስቲያኖችን ማውደሙ እየታወቀ፤ እስካሁን ድረስ፤ "አቡነ" ጳውሎስ፤ ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ በማድረግ ፋንታ ከፖፕ ቤኔዲክት ጋር መሞደሞዱን እየቀጠሉ ነው።

ከላይ በተዘረዘሩትና በሌሎችም ምክንያቶች፤ የ"አቡነ" ጳውሎስ ጉዳይ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስና ምእመናን በጥልቀት ተመርምሮ አስፈላጊው እርምጃ በአስቸኩዋይ መወሰድ ይኖርበታል።


ሕብረት ሠላሙ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ