Ethiopia Zare's weekly news digest, week 42nd, 2012 Ethiopian calendar

ከሰኔ 15 - 21 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ አርባ ሁለተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከሰኔ 15 - 21 ቀን 2012 ዓ.ም.) ሳምንት የአገሪቱ መሪ አጀንዳ ኾኖ የሰነበተው የህዳሴ ግድብና ከዚሁ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ከአገር አልፎ የዓለምን ዓይንና ጆሮ የያዘ ነበር ማለት ይቻላል። ኢትዮጵያ የግድቡን የውኃ ሙሌት ለመጀመር የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ባለችበት ወቅት በሦስቱ የተፋሰሱ አገራት መሪዎች በአፍሪካ ሕብረት በኩል እንዲሸማገሉ ግብጽ ፍቃደኛ መኾንዋን ማሳወቋና ብዙም የተጠበቀ አልነበረም። ኾኖም ግብጽ ወደ ዳር ስትገፋው የነበረው የአፍሪካ ሕብረትን አወያይነት ተቀብላ ውይይት መደረጉ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የሳምንቱን ዜና ኾኖ ታይቷል።

ይሁንና ግብጽ ከውይይቱ በኋላ በፕሬዝዳንቷና በአገሬው ሚዲያዎች የተስተጋባው ዜና ሌላ ውዥንብር መፍጠሩ እንደገና ጉዳዩን የዓለም ዜና ጭምር እስከማድረግ ደርሷል። በተለይ ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ ጋር ስለ ውኃ አሞላሉ ስምምነት ሳታደርግ ውኃ ላለመሙላት ተስማምታለች የሚለው ዜና በአገር ቤትም በውጭም ቁጣ ቀሰቀሰ። ነገሩ ሲፈተሽ ግን እንደተባለው ስምምነት አለመደረጉ ነው። የአፍሪካ ሕብረትም፣ ኢትዮጵያም በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የመስጠታቸው እና እውነታው እንዲገለጥ ማድረጋቸው እፎይታ ሰጥቷል።

ከዚሁ ግድብና ወቅታዊ ክስተቶች ጐልተው የወጡበት ሳምንት ነው ማለት ይቻላል። ለህዳሴ ግድብ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ድምፅም የተሰማበት ሳምንት ነበር። በተለይ የቀድሞ የአሜሪካ ባለሥልጣናት አሜሪካ በህዳሴ ግድብ ላይ ገለልተኛ እንድትኾን አጥብቀው ጠይቀዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያየ መንገድ እየተስተጋባ ያለው የትግራይ ክልል የራሴን ምርጫ አካሒዳለሁ ብሎ መነሳት ከምርጫ ቦርድ ይሁንታ የማይሰጠው መኾኑ በይፋ የተገለጸ ቢኾንም፤ ሕወሓት ግን አካሒዳለሁ በሚለው ጸንቶ ባለሥልጣኖቹም ለምርጫ ቦርድ መልስ በሚመስል መለኩ የሰጡት አስተያየት ከሳምንቱ ትኩረት ከተሰጠው ዜና ውስጥ ይካተታል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ደግሞ ወደ ትግራይ የተከለሉ የአማራ አካባቢዎች ምርጫ ማድረግ አይገባም ብሎ ይፋዊ መግለጫ አውጥቷል።

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ይጠቀምበት የነበረው ቀዩ መጽሐፍ በአዲስ ስለመተካቱና በዚሁ ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ መኮንኖች ጋር ያደረጉት ውይይት ዐበይት ሳምንታዊ ክንውን ተደርጐ ይጠቀሳል። የቀዩ መጽሐፍ ቅኝት ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋር እንዲቆራኝ ተደርጎ የቆየ ነበረና ይህንን የሚተካ አዲስ ስትራቴጂ ተቀርፆ መቅረቡ የተገለጹበት ነው። የአገር መከላከያ በአልሸባብ ላይ የወሰደው እርምጃን የተመለከተው ዘገባም ከሳምንቱ ትኩረት ካገኙ ወሬዎች መካከል ይጠቀሳል።

በኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝ ዛሬም እየተስፋፋበት መኾኑ እየታየ ነው። በየዕለቱ የሚወጡ መረጃዎች ይህንኑ ያንጸባርቃሉ። በዚህ ሳምንት በአጠቃላይ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ከ5 ሺሕ በላይ የዘለለበት ሲሆን፣ የሟቾችም ቁጥር ከቀደሙት ጊዜያት ገዝፎ የታየበት ኾኗል።

ከኢኮኖሚ አንፃር አዲስ አበባ የኤሌክትሪክ አውቶቡስ ተጠቃሚ የሚያደርጋት ግንባታ ይፋ የተደረገበት ሳምንት ነው። ኢትዮ ቴሌኮምን ወደ ግል ለማዛወር መንግሥት እየሔደበት ያለው መንገድ አግባብ አይደለም በማለት ኢዜማ ቆምጨጭ ያለ መግለጫ ማውጣቱም ተጠቃሽ የሳምንቱ ጉዳይ ነበር። እንዲህና በይበልጥ በህዳሴ ግድብ ላይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተመለከተው ጥንቅር በኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዝግጅት ክፍል እንዲህ ይቀርባል። መልካም ንባብ!

የግብጽ ሰሞናዊ ሴራና የኢትዮጵያ አቋም

በህዳሴ ግድብና በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ከመቼውም ጊዜ በላይ ውጥረት የነገሠበት ጊዜ ቢኖር ይህ ያሳለፍነው ሳምንት ነው ማለት ይቻላል። በግብጽ አደነቃቃፊነት ሲታጐሉ የነበሩ ድርድሮች ብዙ አድክመዋል። ግብጽ እንዲህ ባለው መንገድ መጓዝ የሌለባት በመኾኑ የሦስትዮሽ ድርድሩ ውጤት አመጣ አላመጣ፤ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ዙር የውኃ ሙሌት እንደምትጀምር ለዚህም ዝግጅቷን እንዳጠናቀቀች በመግለጽ አቋሟን አሳወቀች።

በዚህ መኻልም ቢኾን ተደጋጋሚ ድርድሮችና ውይይቶች ተካሒደዋል። ውይይቱ መስመር እየያዘ ነው ሲባል ግብጽ ድርድር በማቋረጥ ጉዳዩን ለተመድ በማቅረብö ሌላ ጊዜ ደግሞ አዲስ ሐሳብ በማምጣት የምትሸርባቸው ሴራዎች ሊያዝና ሊጨበጥ አልቻለም። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን፤ ኢትዮጵያ የሚደረገውን ሁሉ እያሳወቀች አቋሟንም እያንጸባረቀች ጉዳያችን በሦስታችን እና በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት እንዲቋጭ ብትልም፤ ግብጽ ካለችበት አህጉር ርቃ ጉዳዩ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኘው የመንግሥታቱ ድርጅትና ከአሜሪካ በቀር ሌላ አላይም ብላ የአፍሪካ ሕብረት ጣልቃ እንዳይገባ ያላደረገችው ጥረት የለም።

በዚህ ሳምንት ግን ከዚህ የተለየ ነገር ኾነ፤ የአፍሪካ ሕብረት ከሦስቱ አገራት ጋር በጉዳዩ ላይ መከረ፤ ግብጽ እጅ ሰጠች። የኢትዮጵያም ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ስኬት አገኘ። የአፍሪካ ሕብረትም በተመድ ሲታይ የነበረው የሦስቱ አገራት ጉዳይ በአዲሱ እጅ መኾኑን እወቁ ብሎ ገለጸ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ አቅጣጫዎች ያደረገችው ሙከራ ያልተሳካላት ግብጽ፤ ከሰሞኑ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት የተደረገው ውይይተ ካበቃ በኋላ ማንም ምንም ሳይል ኢትዮጵያ የውኃውን ሙሌት ለማዘግየት ተስማማች ብላ ገለጸች። እንደ አልጀዚራ ያሉ የመገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያ የውኃ ሙሌቱን ለማራዘም ተስማማች የሚለውን ዜና አጮሁ። ይህ ዜና ግን ብዙዎችን አስቆጣ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጣት ተቀሰረ፤ እንዴት ይሆናል? ተባለ። ብዙም ሳይቆይ ግብጽ እንዲስተጋባ ያደረገችው ዜና ጠማማ ስለመኾኑ በግልጽ ታየ። በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት ያልተሳካላት ግብጽ ከሰሞኑ በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት የተደረገው ውይይት እና ስምምነት ላይ የተደረሰበት “በሁለት ሳምንታት ውስጥ ተደራዳሪዎቹ መፍትሔ የሚኾን ስምምነት ያደርጋሉ፤ እስከዛው ኢትዮጵያ እስከ የውኃ ሙሌቱን አትጀምርም” የሚል አንደምታ ያለው ቢኾንም፤ በግብጽ መረጃ ሰጪነት የተለቀቀው ዜና ስምምነት ሳይካሔድ ውኃ እንደማይሞላ ኢትዮጵያ መስማማቷን ነበር።

ይህ አስደንጋጭ ወሬ ኾን ተብሎ እንዲሠራጭ መደረጉ ግልጽ ነበርና ኢትዮጵያ ምላሽ ሰጠች። መረጃው ትክክል ያለመኾኑንና የድርድሩ መንፈስ ምን እንደነበር አስታውቃ፤ ምንም ይሁን ምን ውኃው ይሞላል አለች።

ባለፉት ቀናት አነጋጋሪ ስለነበረው ጉዳይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትም ኢትዮጵያ ቀሪዎቹ ሁለት ሳምንታት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡን ቀሪ ሥራዎች በማጠናቀቅ የውኃ ሙሌት ሥራውን ትጀምራለች በማለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ጽሕፈት ቤቱ አሁን ባወጣው መግለጫ ላይ እንደገለጸው፤ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት ትናንት ባደረጉት ስብሰባ በግድቡ ሙሌትና አስተዳደር ላይ የሚደረገው ድርድር በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት እንዲጠናቀቅ ስለመስማማቱም አትቷል።

አያይዞም “ኢትዮጵያ በቀሪዎቹ ሁለት ሳምንታት የግድቡን ቀሪ ሥራዎች በማጠናቀቅ ሙሌት ትጀምራለች” በማለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋ። “በእነዚህ ሁለት ሳምንታት አገራቱ ከስምምነት ላይ ለመድረስ ወስነዋል” ሲል ነው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መግለጫ የአፍሪካ ሕብረት ጉዳዩን መመልከት መጀመሩን፤ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንደገለጠ፤ የአፍሪካ ሕብረት እና የመሪዎች ጉባዔ ቢሮ አባላት ድርድሩን እንደደገፉ፣ ኢትዮጵያ ሱዳን እና ግብጽ ከቃላት ጦርነት መካረር እና አላስፈላጊ መግለጫዎች እንዲቆጠቡ አቅጣጫ ተቀምጦ ልዩ የመሪዎች ስብሰባ ተጠናቋል ሲልም ይኸው መግለጫው አስታውቋል። (ኢዛ)

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የአፍሪካ ሕብረትና ውሳኔው

በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከሰሞኑ ይፋ ከተደረጉ መረጃዎች ውስጥ የአፍሪካ ሕብረት ከሦስቱ የተፋሰሱ አገር መሪዎች ጋር የተደረገው ውይይት ካበቃ በኋላ የሰጠው መግለጫ ነው። በዚህ መግለጫው በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረገው ድርድር ወደ አፍሪካ ሕብረት መመለሱን በማድነቅ፤ ይህንን ጉዳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲያውቅለት ማድረጉ ነው።

በአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ሰብሳቢነት በሦስቱ አገራት መሪዎች መካከል የተደረገው ውይይት መልካም ነገሮች የታዩበት መኾኑንና የአፍሪካ ጉዳይ ወደ አፍሪካ መመለሱ መልካም ተግባር መኾኑን ሕብረቱ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።

የሦስቱ አገራት መሪዎች በትብብር መንፈስ ሰላማዊ፣ ለድርድር የተመቹ እና ሁሉንም አካላት አሸናፊ የሚያደርጉ ሐሳቦችን የሚጠቅሰው መግለጫው እንዲህ ባለው ሁኔታ ውይይቱ መካሔዱ ሕብረቱን ያስደሰተ ነው ብሏል።

በመሪዎቹ ውይይት መሠረት ሦስቱም አገራት ግድቡን በተመለከተ ይነሱ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል በዘጠና በመቶው ላይ ስምምነት ስለ መድረሳቸውም የጠቀሰው ይኸው መግለጫ፤ በቀሪ ነጥቦች ላይ ሦስቱም አገራት ሰላማዊ የኾነ እልባት ለመስጠት ቁርጠኛ መኾናቸውን የሚያመላክት ነው ብሏል።

ስለዚህ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የግድቡን ጉዳይ በተመለከተ ሕብረቱ ጉዳዩ አድርጎ እንደያዘው እንዲታወቅለት ያመለከተው የአፍሪካ ሕብረት በመኾኑም ሕብረቱ በጀመረው መንገድ እንደሚቀጥል አመልክቷል።

ሦስቱ አገራት በሁለት ሳምንታት ውስጥ ድርድራቸውን ለመቋጨትና ሁሉንም ወደሚያግባባ ስምምነት ለመድረስ መስማማታቸውንም የሕብረቱ መግለጫ አስታውሶ፤ በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የሚደረገውን ድርድር ሊጎዳ የሚችል ምንም ዐይነት መግለጫም እንዳይሰጡ ወይም ተጻራሪ ድርጊቶችን እንዳይፈጽሙ፤ ኃላፊነት ሊሰማቸው እንደሚገባ ያሳሰበበትም መግለጫ ነበር። ይሁን እንጂ ከውይይቱ በኋላ ግብጽ በተናጠል የሰጠችው መግለጫ ሁኔታውን በርዞታል። (ኢዛ)

የአሜሪካ ባለሥልጣናት በህዳሴ ግድብ ላይ እየተነጋገሩ ነው

በዚህ ሳምንት የህዳሴ ግድብን የተመለከቱ በርካታ ክስተቶች የታየበት ነው። በተለይ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የአሜሪካ መንግሥት የያዘውን አቋም በእጅጉ የሚኮንን በጋራና በቡድን የሚያስተጋቡ ቢቢቢ አሜሪካ በመድሎ ከያዘችው የግድቡ ድርድር ገለል ብላ ለእውነተኛ ድርድር ድጋፍ እንድታደርግ የአገሪቱ የቀድሞ ባለሥልጣናት ማሳሰባቸው ነው።

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ አሜሪካ ገለልተኛ እንድትኾንና ግልጽና ፍትሐዊ የሽምግልና ሒደት አንድትከተል በግልጽ የጠየቁት ደግሞ አምባሳደር ሱዛን ራይስ፣ አምባሳደር ጀንዳይ ፍሬዘር እና አምባሳር ኸርማን ኮኸንን ጨምሮ ሰባት የቀድሞ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ናቸው። እነዚህ የቀድሞ ባለሥልጣናት ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በጻፉት ደብዳቤ አሁን ላይ ግድቡ ላይ እየተካሔዱ ያሉ ውይይቶች ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሳቸውን አስታውሰው።

ዋሽንግተን ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ በገለልተኝነት ልትንቀሳቀስ ይገባታል በማለት ያላቸውን አቋም አንጸባርቀዋል። አሜሪካ ግልጽና ፍትሐዊ የሽምግልና ሒደት የተከተለ አካሔድ ሊኖራት እንደሚገባም ያመለከቱት አምባሳደሮቹ፤ አሜሪካ አውቃም ይሁን በስሕተት ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ ለግብጽ መወገኗ በጉዳዩ ላይ ለመድረስ ለታሰበው ስምምነት በምታደርገው ጥረት ላይ ሚናዋን እንደሚገድበውም ሳያስገነዝቡ አላለፉም።

ከግድቡ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ማድረግም ኾነ የሚደረጉ ድጋፎችን ማገድ ጉዳዩን አስቸጋሪ ከማድረጉም በላይ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚደረገውን ጥረት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው በማመልከትም የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ኢትዮጵያ እና ግብጽን እንዲያደራድሩ በደብዳቤያቸው እስከመጠቆም ደርሰዋል።

ሱዳን ከኢትዮጵያ እና ግብጽ ጋር ያላትን ግንኙነት ሚዛን ጠብቃ ለመሔድ በምታደርገው ጥረት፤ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለች የጠቆሙት እኒሁ የቀድሞ የአሜሪካ ባለሥልጣናት፤ ኾኖም ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ መፍትሔ ለመፈለግ ግን የተሻለ ቦታ ላይ እንደምትገኝ አመልክተዋል።

አሁን በግድቡ ላይ አሜሪካ የያዘችው ገለልተኛ ያልኾነ እና ለግብጽ ያደላ አቋም፤ በሱዳንም በጦሩ እና በሲቪል አስተዳደሩ መካከል ክፍተት በመፍጠር የአገሪቱን ሽግግር በማደናቀፍ ሰላምን የሚያናጋ መኾኑን ጭምር በዚሁ ደብዳቤያቸው አመልክተዋል። ህዳሴ ግድብ ድርድር ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መግባቱን በመጠቆምና በማስታወስም የአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም እንዲጠበቅ፣ በአካባቢው ጸጥታ እና መረጋጋት እንዲሰፍን አሜሪካ በዚህ ሒደት ውስጥ ገለልተኛ እንድትኾን እና እውነተኛ ድርድር እንዲካሔድ መደገፍ እንደሚኖርባትም አሳስበዋል። እንዲህ ያሉ ሰሞናዊ አቋሞች ኢትዮጵያን የሚደግፉ ስለመኾናቸው የተለያዩ ትንታኔዎችም እየተሰጠባቸው ነው። (ኢዛ)

የምርጫ ቦርድ ውሳኔና የሕወሓት የሙጥኝ አቋም

የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ምርጫ ለማድረግ የወሰነው ውሳኔ ከወቅታዊ አገራዊ የፖለቲካ ትኩሳቶች መካከል አንዱ ኾኖ ቀጥሏል። የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ይህንን የክልሉን ጥያቄ የሚያስተናግድበት የሕግ አግባብ እንደሌለ ጠቅሶ ምላሽ የሰጠበት ጉዳይ ቢኾንም፤ ሕወሓት ምርጫውን አካሒዳለሁ ብሎ የሙጥኝ ብሏል። በሕገመንግሥቱ በየትኛውም ክልል ምርጫ የማስፈጸም ሥልጣን ያለው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ቢኾንም፤ የትግራይ ክልል የምርጫ ቦርድን ሥልጣን ጉዳዩ ያለ አይመስልም።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ክልል ምርጫ ማድረግ እንደማይችል ምርጫው ለማካሔድ ቦርዱ ድጋፍ ይስጠኝ ብሎ የጠየቀውንም ጥያቄ ውድቅ አድርጓል። ከዚህ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ በኋላ ከወደ ትግራይ የሚሰጠው የትግራይ ምርጫ ቦርድ እናቋቁማለን እና ምርጫውን ለማድረግ የሚከለክለን ምድራዊ ኃይል የለም የሚሉ ሐሳቦች በተለያዩ የክልሉ ኃላፊዎች ሲሰነዘር ሰንብቷል። በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡት ግን አቶ ጌታቸው ረዳ ናቸው። አቶ ጌታቸው በአገር ደረጃ ምርጫው የተራዘመበትን ምክንያትና አካሔድ ኮንነው፤ በክልል ደረጃ የእርሳቸው ፓርቲ ምርጫውን ለማድረግ ስለመቁረጡና በቅርቡ ለምርጫ ቦርድ ላቀረቡት ጥያቄ ከምርጫ ቦርድ የተሰጣቸው ምላሽ ምርጫውን ላለማካሔድ እንደማያግዳቸው ያመለከቱበትን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ ጌታቸው በተለይ ከቪኦኤ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ፤ የምርጫ ቦርዱ ውሳኔ በሚዲያ ነው የሰማነው የሚሉት ለሚካሔደው ምርጫ የሎጂስቲክስም ይሁን ሒደቱን መምራት እንዲችል ነው ጥያቄ ያቀረብነው የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ በኮቪድ ምክንያት አልችልም ብዬ ወስኛለሁ፤ በዚያ ላይ ደግሞ ፌዴሬሽን ምክር ቤትም እንደዚህ እንደዚህ ብለዋል የሚል መልስ መስጠቱን ጠቅሰዋል። “ስለዚህ ምርጫ ቦርድ አላካሒድም ካለ፣ ማካሔድ አለብኝ የሚል የትግራይ ክልል መንግሥት ምክር ቤት ውሳኔ ሕገ መንግሥቱን ጠብቆ የተደረገ ውሳኔ የሚተገበር መኾኑን ነው የተናገሩት። ከምንም በላይ የትግራይ ክልል ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የማይገፈፍ መብት ስለኾነ ያንን ለማረጋገጥ የሚያስችል ምርጫ ለማድረግ የተወሰነው ውሳኔ ተግባራዊ ወደ ማድረግ ይካሔዳል ማለት ነው” ብለው ምርጫው አይቀሬ መኾኑን የሚያመለክት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

የትግራይ ክልል መንግሥት ምርጫ ለማድረግ የሚያስፈለጉት ሁሉንም ሕጋዊ ዝግጅቶች ማድረግ ይኖርበታል። ምርጫን በወቅቱ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝግጅቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ የሚገደዱ ስለመኾኑም በዚሁ ቃለምልልሳቸው ላይ አመልክተዋል።

እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ ምርጫ ቦርድ ደግሞ የመምረጥና መመረጥን መብት ሰጪ አይደለም ነው የሚሉት። “ምርጫ ቦርድ ቢሮክራቲክ ተቋም ነው። ምርጫ የሚያካሒድ ተቋም ነው እንጂ፣ የምርጫ መብትን የሚያረጋግጥ፣ የሚሰጥም የሚደግፍም ተቋም አይደለም።” በማለትም ይኼ ተቋም በማያሳምኑ ምክንያቶች፣ ምክንያቶቹ የሕግ ልባስ ቢሰጥበትም ባይሰጥበትም ይህንን የማይገሰስ መብት ተግባራዊ የማድረግ ጉዳይ ላይ ወገቤን በሚልበት ሰዓት የመብቱ ባለቤቶች ሕገ መንግሥቱ ያረጋገጠላቸውን መብት ይጠቀማሉ። አያይዘውም ከምንም ነገር በላይ ተፈጥሮአዊ የኾነ ፖለቲካዊ መብታቸው ሳይሸራረፍ የራስን ዕድል በራስን የመወሰን ጥያቄ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል እርምጃ መውሰዳቸው ግዴታ ነው የሚኾነው። ዝም ብሎ መብት ኤክሰርሳይስ የማድረግ ጉዳይም ያለመኾኑንም አክለው ተናግረዋል።

ስለዚህ ምርጫ ቦርድ እኔ ነኝ ብቸኛ አስፈፃሚ ነኝ ሲል፤ ለማስፈፀም ፈቃደኛ እስከኾነ ድረስ ነው ብቸኛ አስፈፃማነት መብት የሚኖረው። የመምረጥ መብት ከምርጫ ቦርድ ሕልውና በላይ ነው። ከማንም በላይ ግን ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ከምርጫ ቦርድ በላይ ነው በማለት ምርጫው በክልሉ የሚደረግ ስለመኾኑ አቶ ጌታቸው ያስረዳሉ። ለዚህም ክልሉ የክልሉን የምርጫ ቦርድ እንደሚያቋቁሙም ጠቅሰዋል። (ኢዛ)

የትግራይ ክልል ምርጫና የአብን አቋም

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሕወሓት ሊያደርግ ያሰበው ምርጫ ተቀባይነት የለውም ሲል በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥትን በተመለከተ የሚያራምደውን ወጥ አቋም በተለያዩ ጊዜያት በግልጽ ማሳወቁን ያስታወሰው መግለጫ፤ የአብን አቋም የአማራ ሕዝብ ሕገ መንግሥቱን በማርቀቅም ይሁን በማጽደቅ ሒደቶች በሴራ የተገለለ እና እንዳይሳተፍ የተደረገ በመኾኑ፤ ሰነዱም በአማራ ጠል ትርክት የተቃኘ፤ ኋላ ቀር፤ ለአገር አንድነት እና ደኅንነት የሥጋት ምንጭ በመኾኑ ሊቀየር (ሊሻሻል) ይገባዋል የሚል እንደኾነም ገልጿል።

ሕወሓት መራሹ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት፤ በክልሉ ውስጥ ምርጫ ለማድረግ የሰጠው ውሳኔ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን እንደኾነ ገልጾ፤ እርምት ሲጠይቅ፤ በዚህ አንድምታ እና ተግባቦት መነሻነት መኾኑ ሊታወቅ ይገባል በማለት፤ በታሪክ በአማራው ክፍል በጎንደር ክፍለ አገር ሥር የነበሩት ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት እንዲሁም በወሎ ክፍለ አገር ሥር ያሉት እና ሌሎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲጠቃለሉ በተደረጉ አካባቢዎች ምርጫ እንዳይካሔድ አቋሙን አሳውቋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በሕወሓት ኃይል ተዘርፈው ወደ ትግራይ በተካለሉት የአማራ ርስቶች ዙሪያ ያሉትን የወሰን ጥያቄዎችን በተመለከተ መላውን የአማራ ሕዝብ እንዲሁም ፍትሕ እና አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን ከጎኑ በማሰለፍ፤ በተዛማጅ የሕግ እና የፖለቲካ ትግሎች ዳር እንደሚያደርስ በመግለጽ አቋሙን አሳውቋል።

ከዚህም ሌላ ሕወሓት ከዚህ ኃላፊነት ከጎደለው በአገር አንድነት እና ሉዓላዊነት ላይ አደጋን ሊያስከትል ከሚችል እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲታቀብ እያሳሰብን፤ የአገሪቱ መንግሥት ይሄን ያልተገራ፤ የማን አለብኝነት ሕገወጥ ሒደት በሕግ አግባብ እንዲያስቆም በዚሁ መግለጫው ጠይቋል። (ኢዛ)

አዲሱ የመከላከያ ስትራቴጂ ሰነድ

አዲሱ የመከላከያ ሠራዊት ግንባታ ስትራቴጂ የቀድሞው ስትራቴጂ የነበረበትን ክፍተት በሚሞላ መልኩ የአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት መዋቅር እና አሁናዊ አገራዊ ሁኔታ መሠረት በማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀውን የዘመነ ሠራዊት ለመገንባት በሚያስችል መልኩ የተዋቀረ እንደኾነ የኢፌዲሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ አስታወቁ።

ስትራቴጂው በዓለም ደረጃ መልካም ስምና ዝናን የገነባው ሠራዊቱ የመጣበትን ጠንካራ መንገድ አጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችል እና የሕዝብና አገር ወገንተኝነቱን አጥብቆ እንዲሔድ የሚያደርግ እንደኾነም ገልጸዋል።

የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ለመከላከያ ሠራዊት ጄኔራል መኮንኖች የስትራቴጂ ሰነዱን በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል። ወቅታዊ አገራዊ ፈተናዎችን ባገናዘበ መልኩ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ የወታደራዊ አቅምን መሠረት አድርጎ የተዘጋጀው ሰነዱ ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የኾነና ለሕዝብና አገር ዘብ የቆመ ሠራዊት ለመገንባት ያግዛል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የካቲት ወር 2012 ዓ.ም. ላይ የታተመው ረቂቅ የስትራቴጂክ ሰነዱ በሒደት እየዳበረ ሁሉም ዜጋ በቀላሉ እንዲረዳው እንዲያውቀውና በጊዜ ሒደት ከወቅቱ ጋር እየተናበበ እንዲሻሻል ተደርጎ የሚቀረጸ ሲሆን፣ በአዲስ መልክ ለማዘጋጀት ያስፈለገው ሠራዊቱን ለማዘመን በማለትም ነው ብለዋል።

ይህን ሰነድ በድጋሚ በትኩረት ለመመልከት ያስፈለገበት አምስት መሠረታዊ እውነታዎች አሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነዚህን አመክንዮዎች በመለየት ሰነዱ እንዲሻሻል ተደርጓል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው እንዳነሱት የሠራዊት ግንባታ ስትራቴጂው የአገሪቱን ሉዓላዊነት ባስከበረ መልኩ ሕዝቦቿ የሚተማመኑበት ዳር ድንበሯን የሚያስከብርና ዓለም አቀፍ ተቀባይነቷ እንዲጨምር በሚያስችል መልኩ እንደተሰናዳም አስረድተዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱ ለፓርቲ፣ ለብሔርና ለቡድን የወገነ ሳይሆን፤ አገራዊ ሉዓላዊነትን መሠረት አድርጎ በሕገ መንግሥቱ የሚመራ ኾኖ አገራዊ ቀጣይነትን ማረጋገጥ አለበት ብለዋል። (ኢዛ)

የኮሮና ቫይረስ የሚያዙም የሚያገግሙም እየጨመሩ ነው
የሟቾች ቁጥርም መቶ ሊደፍን ነው

በኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝ አሁንም በየዕለቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየተያዙ ስለመኾኑ በየዕለቱ የሚወጣው ሪፖርት እያሳየ ነው። ጐን ለጐንም የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መኾኑንም የሚያመላክት ሲሆን፣ ከቫይረሱ የሚያገግሙ ሰዎች ቁጥርም ከፍ ማለቱ እንደ መልካም ዜና የሚታይ ነው።

ይሁን እንጂ የአዳዲስ ተጠቂዎች ቁጥር በየዕለቱ ከፍና ዝቅ እያለ የዘለቀ ሲሆን፣ የአዳዲስ የተጠቂዎች ቁጥር በመቶዎች የሚቆጠር ኾኖ መዝለቅ ከጀመረ ሳምንታት ተቆጥረዋል። እስከ ሳምንቱ መጨረሻ እሁድ ሰኔ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በአጠቃላይ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 5,689 ደርሷል።

ይህ ሳምንት በአንድ ቀን 250 የሚኾኑ የቫይረሱ ተጠቂዎች የተገኙበት በመኾንም ይለያል። ይህንን ሳምንት የተለየ የሚያደርገው በየቀኑ ከቀደሙት ጊዜያት በተለይ በርከት ያሉ ሞት የተመዘገበበት ነው። በእሁድ የጤና ሚኒስቴር መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ በቫይረሱ መጠቃታቸው ታውቆ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 98 ደርሷል። በጽኑ ሕመም ላይ የሚገኙ ደግሞ 33 መኾናቸውን አሳውቋል።

በአንፃሩ ደግሞ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ በመልካም እየታየ ሲሆን፣ በእሁድ ሪፖርት መሠረት በአንድ ቀን 117 ሰዎች ማገገም በመቻላቸው እስካሁን ከበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 2,132 መድረሱን አመልክቷል። የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች ቁጥር ደግሞ 246,911 ደርሷል።

ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ በዚህ ሳምንት አስገራሚ የተባለው ዜና በቫይረሱ ተጠቅተው በየካ ሆስፒታል የሕክምና እርዳታ ሲደረግላቸው የቆዩ የ114 ዓመት አዛውንት ከበሽታው አገግመው መውጣታቸው ነው። (ኢዛ)

የአዲስ አበባ ፈጣን አውቶቡስ መንገድ ግንባታ

አዲስ አበባን የፈጣን አውቶቡስ ባለቤት የሚያደርጋት ከጀሞ 2 እስከ ጄኔራል ዊንጌት ድረስ የሚዘልቀው የፈጣን አውቶቡስ መንገድ (BRT) ግንባታ ተጀመረ።

በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ግንባታው የተጀመረው ይህ የፈጣን አውቶቡስ መንገድ 20 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ ወደ ሁለት አቅጣጫ የሚዘረጋ ነው። የፈጣን አውቶቡስ መንገዱ አዲስ ከተማ፣ ልደታ፣ ቂርቆስና ኮልፌ በመሳሰሉ ቦታዎች የአውቶቡስ መቆሚያዎች ይኖሩታል። በቀጣይም ከ20 በላይ የአውቶቡስ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክቶች መታቀዳቸውን ኢንጂነር ታከለ ኡማ በምረቃ ሥርዓቱ ላይ ተናግረዋል።

ኢንጂነር ታከለ የከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት ችግርን ለመፍታት የብዙኀን ትራንስፖርት ማዘመንና ማሳደግ ላይ እንደሚያተኩር የጠቀሱ ሲሆን፣ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና በተቀመጠላቸው የጥራት ደረጃ እንደሚጠናቀቁም አስታውቀዋል።

የአውቶቡስ የፍጥነት መንገዱ ፕሮጀክት የፈረንሳይ ኩባንያ የሚያከናውነው እንደሚኾንም ለማወቅ ተችሏል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ