Ethiopia Zare (ቅዳሜ ግንቦት 1 ቀን 2001 ዓ.ም. May 9, 2009)፦ በኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካዊ እስር፣ የመብት ጥሰት፣ በጋዜጠኞች ላይ ወከባና ግድያ እንደሚፈፀሙ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በ2008 ዓመታዊ ሪፖርቱ ገልጿል። መንግሥት ሪፖርቱን “ከእውነት የራቀ ነው” በሚል በዝርዝር በማየት የማስተባበያ ሪፖርት አዘጋጅቶ በቁጥጥሩ ስር በሚገኘው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ዝግጅቶች አቅርቧል።

 

ለምሳሌም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ውስጥ አለ ያለውን የሰብዓዊ መብትን ረገጣ በመስማልከት ከጠቀሳቸው ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምዕራብ ሸዋ ዞን አልፈታ ወረዳ ደንዲ ምርጫ ጣቢያ ሕብረትን ወክለው በመወዳደር ተመርጠው ፓርላማውን የተቀላቀሉና በምክር ቤቱም ውስጥ የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ ጉቱ ሙሊሳ ይገኙበታል።

 

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እኚህ ግለሰብ መደብደባቸውን በሪፖርቱ ያካተተ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሰሞኑን በሪፖርቱ ላይ በሠራው ማስተባበያ አቶ ጉቱ ሙሊሳ ተፈልገው መጥፋታቸውንና የዝግጅት ክፍሉ ወደ ቤታቸው ሲሄድ ወንድማቸውን አግኝተው ማነጋገራቸውን በመግለፅ፣ ወንድማቸው ነው የተባለው ግለሰብ በቴሌቭዥን ቀርቦ “ወንድሜ አልተደበደበም ሐሰት ነው።” በማለት የሰጠው ማስተባበያ በቴሌቭዥን ተላልፏል።

 

የፓርላማው አባል አቶ ጉቱ ይህን “ፍፁም ሐሰትና አሳፋሪ የሆነ ዘገባ” ሲሉ ሁኔታውን እንዲህ ያስረዳሉ፤ ከፓርላማ መደበኛ ስብሰባ አንድም ቀን ሳልቀር ፓርላማው የሰጠኝ ቤት ውስጥ እየኖርኩ እንደሌለሁ እና ተፈልጌ እንደጠፋሁ በማስመሰል እንዲሁም የማላውቀውን ሰው በቴሌቭዥን አቅርበው ወንድሙ ነው አልተደበደበም ብለው የተሳሳተ መረጃ ለመስጠት መሞከራቸው አሳዝኗቸዋል።

 

በደተበደብኩበት ወቅት የደረሰብኝ ጉዳት እየታየ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ቀርጾኝ ነበር ያሉት አቶ ጉቱ፤ በዚህ ሣምንት የም/ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ በልዩ ልዩ የሥራ ጉብኝት ሲያደርግ እኔም አብሬ ስለነበርኩ ተቀርጾ ሲተላለፍ እንደነበረ እየታወቀ ጠፉ አልተገኙም ብሎ ዜና መሠራቱ የሚገርም ነው ብለዋል።

 

አቶ ጉቱን የሚያውቋቸው ሌሎች የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት በበኩላቸው ኢቴቪ የሠራው ዜና እጅግ አሳፋሪ ዜና መሆኑን ገልጸው፤ የአቶ ጉቱን ቤተሰቦችና ወንድሞች እናውቃቸዋለን ወንድሙ ነኝ ብሎ የቀረበውን ግለሰብ ያየነው በቴሌቭዥን ነው፤ ወንድሙ አይደለም። አደጋ በደረሰበት ወቅትም ተደብድቦ ተፈንክቶ እጁ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶ ታሞ ተኝቶ አይተናል። በአቶ ጉቱ ላይ የተሰራው ዜና የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርን ያልጠበቀ ነው ብለዋል።

 

ሆን ተብሎ ለማሸማቀቅ ከተቻላቸውም አስበርግጎ ከሀገር ለማስወጣትና ለማደናገር እንዲሁም በመረጠው ህዝብ አመኔታ እንዲያጣ የሚደረግ ሙከራ ነው በማለት ቅሬታቸውን ገልፀዋል። ሆኖም ግን የመረጠው ህዝብ የኦህኮን አባላትን መንፈሠ ጠንካራነት በትክክል ስለሚያውቃቸው ከንቱ ልፋት ነው ብለዋል።

 

በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በተከታታይ ሲሰራጩ በሰነበቱት ዘገባዎች፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው የ2008ቱ ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካዊ እስር፣ የመብት ጥሰት፣ በጋዜጠኞች ላይ ወከባና ግድያ ተፈጽሟል በማለት ኢትዮጵያን የወነጀለበትን መወንጀሉን አስመልክቶ፤ በኢቲቪ የተላለፉት ዘገባዎች ሪፖርቱ ኢትዮጵያን ለማጥቃት የታሰበ፣ ሐሰተኛና ከእውነት የራቀ ብለውታል።

 

ሪፖርቱን አስመልክቶ የአሜሪካ ኤምባሲ ቃል አቀባይ፣ በየዓመቱ የሚወጣው የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ሀገሮች የሚመለከትና ከ1970ዎቹ ጀምሮ እንዲህ አይነቱ ሪፖርት እንደሚቀርብ ገልጾ፣ ለእውነተኛነት መደረግ ያለባቸውን ጥንቃቄዎች በማሟላት የሚዘጋጅ ሪፖርት ነው ብሎታል።

 

መንግሥት የሪፖርቱን ሐሰተኝነት መግለጹን በማስመልከትና በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ላይ ያቀረበውን ውንጀላ በሚመለከት ደግሞ፣ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የሚወጡት ዓመታዊ ሪፖርቶች ከፍተኛውን የትክክለኛ እውነት ደረጃ የጠበቁ እንዲሆኑ አስፈላጊው ጥረት እየተደረገ የሚዘጋጁ መሆናቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

 

የኤምባሲው ቃል አቀባይ አክለውም በ1977 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ.) በኮንግረሱ በፀደቀው ሕግ መሰረት በመላው ዓለም የሚገኙ ሀገሮች ዓመታዊ የሰብዓዊ መብት አያያዛቸው ይገመገማል። አሜሪካም በየጊዜው በራሷ ላይ በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ሪፖርት ይቀርብባታል ብለዋል።

 

የሰብዓዊ መብት ጉዳይ በሁሉም ሀገራት ጥበቃ ማድረግን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው በማለት የገለጹት የኢምባሲው ቃል አቀባይ፣ የአሜሪካ መንግሥት በሰብዓዊ መብት ጉዳይ ላይ ጠንካራ አቋም አለው፣ ሰብዓዊ መብትን ለማስፋፋት ከሚደረጉ ጥረቶች አንዱ በየዓመቱ ሪፖርት ማውጣት ነው ብለዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ