የሲያትሉ ሰልፍ ዘገባ
ብርቱካን ሚደቅሳ ትፈታ! አቶ በቀለ ጅራታ ይፈቱ! ቴዲ አፍሮ ይፈታ!

Ethiopia Zare (ኀሙስ ጥር 7 ቀን 2001 ዓ.ም. January 15, 2009)፦ የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት ትላንት የሲያትል እምብርት ከሆነው ዌስት ሌክ ሴንተር የተጀመረውና በሲያትል የፌደራሉ መንግሥት መቀመጫ በሆነው ፌደራል ሐውስ የተጠናቀቀው የሲያትል፣ የቫንኩቨርና የፖርት ላንድ ነዋሪዎች ያካሄዱት ሰልፍ በስኬት መጠናቀቁ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ ውስጥ የፍትህ የበላይነት እንዲሰፍንና ሰብዓዊ መብት እንዲከበር በአጽንኦ የጠየቀው ይሄው ሠላማዊ ሰልፍ ላይ ከ200 ሰዎች በላይ የተሳተፉ ሲሆን፣ የተለያዩ ቀስቃሽ መፈክሮችንና ዜማዎችን በማዜምና በአዘጋጆቹ የተዘጋጀውን የተለያዩ የኢትዮጵያን ጠቅላላ ሁኔታ የሚገልጹ ጽሑፎችን ለሲያትል ነዋሪዎች በመበተን ያሳወቁ መሆኑ ታውቋል።
በአንዲት ካናዳዊት ወጣት አስተባባሪነት ለወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚላክ ካርድ ላይ ሰልፈኞቹ ወ/ት ብርቱካንን የሚያበረታቱ አጫጭር መልዕክቶችን ያስቀምጡና ለወ/ቷ ያላቸውን አክብሮት የገለጹ ሲሆን፣ በተጨማሪም ይህችው የቅንጅት መሪዎች በእስር በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያ የነበረችና የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርበት የምትከታተለው የውጭ ዜጋ ለተሰብሳቢዎቹ አጭር ንግግር አድርጋለች።

ሰልፈኞቹ የሲያትል ሴናተሮች ማለትም የሴናተር ማሪያ ካንትዌልና የሴናተር ፓቲ መሪ ተወካይ ለሆኑት ናቲ ካሚኖስና ሽላ ቤብ ደብዳቤ የሰጡ ሲሆን፣ ተወካዮቹ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን ሁኔታ በትኩረት እየተከታተሉ መሆኑን ገልጸው፤ መልዕክቱን ለመንግሥታቸው እንደሚያስተላልፉ ቃል በመግባት ሰልፈኞቹን ተሰናብተዋል።



