ኮሮናን ለመከላከል የወጣው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስተካከያ ተደረገለት
የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ
የለይቶ ማቆያ ቀናት በግማሽ ቀነሰ፤ የቀብር ሥርዓት እንዲፈጸም ተፈቀደ
ኢዛ (ዓርብ ሰኔ ፲፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 19, 2020)፦ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በመንግሥት በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በአስገዳጅነት እንዲተገበሩ ከተደነገጉ መመሪያዎች አንዳንዶቹ እንዲሻሻሉ ተወሰነ። አስገዳጁ የለይቶ ማቆያ ጊዜ በግማሽ ቀነሰ።
በዚሁ ጉዳይ መግለጫ የሰጡት የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት፤ በተለያዩ ምክንያቶች ለሞት የሚዳረጉ ዜጎችን ሥርዓተ ቀብር ለመፈጸም፤ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ሕብረተሰቡ የቀብር ሥርዓት እንዲፈጽም መፈቀዱ አንዱ ማሻሻያ ነው።
ይህ ማሻሻያ ከዚህ ቀደም የአስከሬን የላቦራቶሪ ውጤት ከመምጣቱ በፊት፤ የቀብር ሥነ ሥርዓት መፈጸም አይቻልም የሚለውን መመሪያ ያሻሻለ መኾኑን የሚያመለክት ነው። ይህ መመሪያ በዚህ መልኩ ቢሻሻልም፤ በቀብር ስፍራ ላይ 50 ሰዎች ብቻ መገኘት አለባቸው የሚለው ያልተቀየረና የጸና ስለመኾኑም አስታውቀዋል።
ከዚህም ሌላ ግለሰቦች በኮሮና ቫይረስ ቢያዙ የሚያገለግላቸው ቤተሰብ አባላትና ራሳቸው ፍላጎት ከግምት በማስገባት ተፈፃሚ የሚኾን ስለመኾኑም የዶክተር ሊያ ማብራሪያ ያስረዳል።
ሌላው ማሻሻያ የተደረገበት ጉዳይ የግለሰቦችን አኗኗር ሁኔታ በተቀመጠው መመሪያ መሠረት አግባብ ከኾነ በቤታቸው እንዲቆዩ እንደሚደረግ ነው።
ከዚህ በፊት ከነበረው አሠራር በተለየ ተፈፃሚ ይኾናል የተባለው ማሻሻያ፤ ከውጭ የሚገቡ ሰዎች በተለይም ወደ አገር ከገቡ በኋላ ባላፉት ሦስት ቀናት ውስጥ ከመጡበት አገር ተመርምረው ነፃ መኾናቸውን የሚያሳይ መረጃ ይዘው ከመጡ፤ ናሙና ተወስዶ በቤታቸው 14 ቀናት እንዲቆዩ የሚደረግ መኾኑን ነው። ከዚህ ቀደም ከውጭ የመጡ በቀጥታ በኳራንታይን ይቆዩ እንደነበር ይታወሳል።
ከውጭ የሚመጡ ሰዎች ከቫይረሱ ነፃ መኾናቸውን የሚያረጋግጥ ሪፖርት ይዘው የማይመጡ ሰዎች ደግሞ፤ ናሙናቸው ተወስዶ ለሰባት ቀናት በለይቶ ማቆያ እንደሚቆዩ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህ ማሻሻያ ከዚህ በፊት 14 ቀን የነበረውን አስገዳጅ የለይቶ ማቆያ አሠራር ወደ ሰባት ቀን ዝቅ የተደረገ መኾኑን የሚያመለክት ነው። (ኢዛ)



