ከኮሮና ቫይረስ ያገገሙ 25 ደረሱ
3ዲ (3D) ኮሮና ቫይረስ በምስል (© istock.com/Dr_Microbe)
ዛሬ አንድ የቫይረሱ ተጠቂ ተገኝቷል
ኢዛ (ዓርብ ሚያዝያ ፲፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 24, 2020)፦ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸው ከታወቁ ሰዎች ውስጥ ማገገም የቻሉት 25 ደርሰዋል። ዛሬ አንድ በቫይረሱ የተጠቃ ሰው መገኘቱን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በ24 ሰዓት ውስጥ የተደረገውን ምርመራ አስመልክቶ፤ ዛሬ ጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው 933 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸው አንድ ሰው ብቻ ቫይረሱ ተገኝቶበታል።
ዛሬ ዓርብ ሚያዝያ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. ቫይረሱ የተገኘባቸው አንድ ሰው የ60 ዓመት ወይዘሮ መኾናቸው ታውቋል። እኒህ ወይዘሮ ከእንግሊዝ መጥተው በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ ናቸው። ይህም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተመዘገቡት የቫይረሱ ተጠቂዎች 117 መድረሱን ያመለከተ ነው።
ትናንት ከተመረመሩት ውስጥ ቫይረሱ የተገኘበት ሰው አለመኖሩና ዛሬ ደግሞ አንድ ብቻ መገኘቱ፤ የቫይረሱን ሥርጭት መቀነሱንም ኾነ በሕብረተሰቡ ውስጥ የቫይረሱ ሥርጭት አለመኖሩን የሚያመለክት አለመኾኑን መረዳት ያስፈልጋልም ተብሏል። (ኢዛ)



