Total coronavirus cases in Ethiopia, 2020-04-22

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (ረቡዕ ሚያዝያ 14 ቀን 2012 ዓ.ም.፤ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ)

ሁለት አዳዲስ በቫይረሱ የተጠቁ ተገኝተዋል፤ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 21 ደርሷል፤ በአፋር ክልል በቫይረሱ የተጠቃ የመጀመሪያው ሰው ተገኘ

ኢዛ (ረቡዕ ሚያዝያ ፲፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 22, 2020)፦ እስካሁን በየዕለቱ በተደረጉ የላብራቶሪ ምርመራዎች ከአንድ ሺሕ በላይ ምርመራ ከተደረገላቸው ሰዎች ውስጥ ሁለት አዳዲስ የኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል።

የጤና ሚኒስቴር ዛሬ ረቡዕ ሚያዝያ 14 ቀን ይፋ ባደረገው ሪፖርት፤ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 1073 የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጐላቸው፤ ሁለት አዳዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸው በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙትን ሰዎች ቁጥር 116 አደርሶታል።

ከመረጃው መረዳት እንደሚቻለው በ24 ሰዓት ውስጥ ከአንድ ሺሕ በላይ ምርመራ የተደረገበት ሲሆን፤ እስካሁን ይህንን ያህል ምርመራ የተደረገበት ዕለት አለመኖሩን ያመለክታል።

በዛሬው መረጃ መሠረት በቫይረሱ ከተጠቁት አንዱ በአፋር ክልል ገዋኔ ከተማ ነዋሪ የኾነ የ22 ዓመት ወጣት ነው።

ሁለተኛው ደግሞ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የኾኑና የአሜሪካን ዜግነት ያላቸው የ54 ዓመት ጐልማሳ ናቸው። እኒህ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ከአሜሪካን መጥተው በለይቶ ማቆያ ውስጥ የነበሩ ናቸው።

በአፋር ክልል ቫይረሱ የተገኘበት ወጣት የውጭ ጉዞ ታሪክ የሌለው ነው። በመረጃው መሠረት በአሁኑ ወቅት 90 የሚኾኑ ሰዎች በለይቶ ማቆያ ሕክምና ላይ ናቸው። አዳዲስ ያገገሙ ሰዎች ደግሞ አምስት በመገኘታቸው በአጠቃላይ እስካሁን ያገገሙ ሰዎች 21 ደርሰዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ማምሻውን እንደተገለጸው ከጅቡቲ በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ አፋር ክልል የገቡ 336 ሰዎች በአስገዳጅ የለይቶ ማቆያ እንዲገቡ መደረጉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል።

ከእነዚህ ውስጥ 226ቱ በሰመራ ዩኒቨርሲቲና 110ሩ ደግሞ በድንበር አካባቢ በተዘጋጁ የለይቶ ማቆያ ገብተው የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነው። እስካሁን የ30ዎቹ ናሙና ተወስዶ የምርመራ ውጤታቸው እየተጠበቀ ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ