በኮሮና ወረርሽኝ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥጋትና ተማፅኖ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ
ክልሎች የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ እየወሰኑ ነው
የፓርቲና ሌሎች ስብሰባዎች ክልከላ ተጥሏል
በአማራ ክልል ዛሬ በተገኙት በቫይረሱ ከተጠቁ ሰዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው 24 ሰዎች
ወደ ክልሎች የሚገቡ ሰዎች ሪፖርት የማድረግ ግዴታ ተጥሎባቸዋል
በጡረታ የተገለሉ የጤና ባለሙያዎችና የጤና ተማሪዎች ለግዳጅ ተዘጋጁ ተብሏል
ኢዛ (ሰኞ መጋቢት ፳፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 30, 2020)፦ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 23 ስለመድረሱ ሲገለጽ ይህ መረጃ እንደ ቀድሞዎቹ ተመሳሳይ ሪፖርቶች በጤና ሚኒስትርና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኩል የተነገረ አልነበረም።
የዛሬውን (ሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2012 ዓ.ም.) መረጃ በቅድሚያ ያሳወቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ናቸው። ከሌሎች ቀኖች በተለየ በዛሬው ዕለት የክልል መንግሥታት ከቫይረሱ ሥርጭት ሥጋት ጋር በተያያዘ የትራንስፖርት አገልግሎቶችን ለማቋረጥ ስለመወሰናቸው ያሳወቁበት ነው። ይህንን መረጃ ዛሬ በሠጡት መግለጫ “በእኛ ሁኔታ ቁጥሩ እየጨመረ መምጣቱን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች እየወጡ ነው። ዛሬ ጠዋት ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ በሽታ ከመረመርናቸው ከ800 በላይ ከሚኾኑት 23 ሰዎች በዚህ በሽታ መጠቃቱ ተረጋግጧል” በማል ነበር የገለጹት።
ከእነዚህ ውስጥ ሁለት ሰው ያገገሙ ሲሆን፣ ምንም ሰው አለመሞቱንም ገልጸዋል። ይሁንና ከንክኪና ከመራራቅ ጋር የሚሠጠውን መመሪያ መቀበል የሚያረካ ደረጃ ላይ አለመኾኑንም አስታውሰዋል።
“ብዙዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በከፋ ሁኔታ ከተገለጠ አሁን ባለው ዲሲፕሊን እንዴት መከላከል ይቻላል የሚል ሥጋት አላቸው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የተሻሉ የሚባሉ አገሮች አደጋውን መከላከል ስላልቻሉ በኢትዮጵያ ሁኔታ ነገሩ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳይኾንብን ማኅበረሰቡ ከምንም በላይ የመተግበር ስሜቱን መግዛት አለበት ብለዋል።
ይህንን በሽታ ለመከላከል ብቸኛው መንገድ ራስን ማሸነፍ እና ርቀትን መጠበቅ እንደኾነ በማስገንዘብ፤ ሁሉም ዜጋ በከፍተኛ ኃላፊነት በመተግበር ኢትዮጵያን ከሚገጥማት አደጋ መከላከል በከፍተኛ ትሕትና በድጋሚ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አቀርባለሁ በማለት ለዜጐች ጥሪ አቅርበዋል።
በአሁኑ ወቅት ይህንን ወረርሽኝ ለመከላከል እየተደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡበት መልእክት ነበር። ከዚህ መልእክት በኋላ በሰዓታት ልዩነት የጤና ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ ከትናንት በሁለት ጨምሮ ዛሬ 23 የደረሱት የቫይረሱ ተጠቂዎች የ37 እና የ32 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሴትና ወንድ ናቸው።
እነዚህ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሁለቱ ግለሰቦች በአማራ ክልል የባህር ዳር እና የአዊ ዞን አዲስ ቅደም ነዋሪዎች መኾናቸውን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
አዲሱ የቫይረሱ ተጠቂዎች የ37 ዓመቷ ሴት መጋቢት 10 ከዱባይ የገቡ ሲሆን፤ ሁለተኛው የ32 ዓመቱ ወጣት ደግሞ መጋቢት 12 ከአሜሪካ የገቡ መኾናቸውን ጠቅሷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ ከወትሮው ለየት ባለ ሁኔታ የተለያዩ ክልሎች በየክልላቸው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እንዲቋረጥ ውሳኔ ያሳለፉ መኾናቸውን እያሳወቁ ነው። በዚሁ መሠረት የደቡብ፣ የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የሐረሪና የቤንሻንጉል ክልሎች ይገኙበታል።
የደቡብ ክልል ከዛሬ ጀምሮ ከየትኛውም አካባቢ ወደ ደቡብ ክልል የሚደረግ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ ስለመወሰኑ ገልጾ፤ የሕዝብ ትራንስፖርት በክልሉ ወሰን ተሳፋሪን ሳያራግፍና ሳይጭን ማለፍ የሚችል መኾኑን ገልጿል። ነገር ግን ሌሎች የትራንስፖርት እንቅስቃሴ የተከለከሉ መኾኑን ገልጿል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በበኩሉ ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች አንድ ሰው ብቻ ጭነው እንዲንቀሳቀሱ፣ የሕዝብ ማመላለሻዎች መጫን ከተፈቀደላቸው ግማሹን ያህል ብቻ እንዲጭኑ ውሳኔ አስተላልፏል። ከዚህም ሌላ ጭፈራ ቤቶች፣ ፑል ቤቶችን ጨምሮ ሰዎች የሚሰበሰቡባቸው የመዝናኛ ቦታዎች እንዲዘጉ ወስኗል።
ከክልሉ አሶሳ ከተማ ኦሮሚያን አቋርጦ ወደ አዲስ አበባ የሚሔደው የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርትና ከአሶሳ ከተማ ወደ አማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ የቤንሻንጉል ክልል ትእዛዝ አስተላልፏል። ከዚህም ሌላ በክልሉ የስደተኛ መጠላያዎች የሚገኙ ስደተኞች ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴዎች ራሳቸውን እንዲገድቡ ትእዛዝ ሠጥቷል።
የሐረሪ ክልል ከነገ ማክሰኞ መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሌሊቱ 6 ሰዓት ጀምሮ በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ተፈጻሚ የሚኾኑ ገደቦችን ጥሏል። በዚህም መሠረት ማንኛውም ዐይነት የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ እንዳይግቡ፣ የከተማ ታክሲዎችም ምንም ዐይነት አገልግሎት እንዳይሠጡ አግዷል።
ከሐረሪ ክልል ከከተማ ወደ ገጠርም ኾነ ከገጠር ወደ ከተማ በሚካሔዱ የትራንስፖርት ጉዞዎች ተሽከርካሪዎች መጫን ከተፈቀደላቸው ግማሽ እንዲጭኑና በተሳፋሪዎች መካከል ርቀት ሠጥተው አገልግሎት እንዲሠጡ፤ የግል አውቶሞቢሎች ከሦስት ሰው በላይ እንዳይጭኑ፤ ለማኅበረሰቡ ኑሮ አስፈላጊ የኾኑ ግብአቶችን የሚያመላልሱ የጭነት መኪኖች ከሹፌርና ከረዳት በስተቀር ሌላ ሰው ሳይጭኑ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ አስታውቋል።
የኦሮሚያ ክልልም የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ ወስኗል። ማንኛውም ፓርቲ ስብሰባ እንዳያካሒድ ማሳሰቢያ የሠጠ ሲሆን፣ ሰላማዊ ስብሰባና መሰል ጥሪ የሚያደርግ ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም የኦሮሚያ ክልል አስታውቋል። የምሽት ቤቶች፣ ጫት ቤቶችና ሺሻ ቤቶችም እንዲዘጉ ወስኗል።
ጡረታ የወጡ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም የጤና ትምህርት በመከታተል ላይ ያሉ ተማሪዎች መንግሥት ለሚያደርግላችሁ አገርን የማዳን ጥሪ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጥሪ አቅርቧል። ሌሎች ለቫይረሱ መከላከያ ይረዳሉ የተባሉ ውሳኔዎችንም መወሰኑን ይፋ አድርጓል።
የአማራ ክልል የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ ውሳኔ ያሳለፈው ትናንት ቢሆንም፤ ዛሬ እንዲተገበር ተደርጓል። ከዚህም ሌላ ቫይረሱን ለመከላከል ያስችላሉ የተባሉ ውሳኔዎችም የተላለፉ ሲሆን፤ በክልሉ በኩል ዛሬ ከተላለፉ ተጨማሪ ውሳኔዎች ውስጥ ባለፉት ሦስት ሳምንታት ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የገቡ በያሉበት ቦታ ለጤና ተቋም ሪፖርት እንዲያደርጉ የሚል ይገኝበታል።
ከዚህም ሌላ የክልሉ ነዋሪዎች እንደ ሁኔታው ታይቶ በክልሉ ውስጥ የሚደረግ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ሊቆም ስለሚችል በቋሚ መኖራያቸው በመኾን የመንግሥትን ውሳኔ እንዲጠብቁም አሳስቧል። (ኢዛ)



