በጎዋ ካትሪን አረፉ
ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን
የፌስቱላ ኢትዮጵያ መሥራች ናቸው
ኢዛ (ሐሙስ መጋቢት ፲ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 19, 2020)፦ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ችግር በመፍታትና “ፌስቱላ ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ ያለው ግብረሰናይ ድርጅት በማቋቋም ከ60 ዓመታት በላይ የፌስቱላ ሕክምና የሠጡት ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን አረፉ።
በኢትዮጵያውያን ዘንድ በዚህ በጎ ተግባራቸው የሚታወቁት ዶ/ር ካትሪን በ96 ዓመታቸው ያረፉት ትናንት መጋቢት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው።
ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ሴቶች የፌስቱላ ሕክምና በመሥጠት ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ግልጋሎት የሠጡት በጎ አድራጊዋ፤ በኢትዮጵያ ላበረከቱት ለዚህ ተግባር የተለያዩ እውቅናዎች ተሠጥቷቸዋል።
ከዚህም ውስጥ የኢትዮጵያ የክብር ዜግነት ይጠቀሳል። ከዚህም ሌላ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የክብር ዶክትሬት ሠጥቷቸዋል። (ኢዛ)



