አዲሱ የምርጫ ክልሎች ካርታ ይፋ ተደርጓል
የመጀመሪያ ነው የተባለው የምርጫ ክልሎች ካርታ
የደርግ የሕዝብ ቆጠራን፣ የኢሕአዴግን ክልል መሠረት ያደረገ ነው
ኢዛ (ቅዳሜ መጋቢት ፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 14, 2020)፦ ከጥቂት ወራት በኋላ ለሚካሔደው አገራ አቀፍ ምርጫ 2012፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የመጀመሪያ ነው የተባለውን የምርጫ ክልሎች ካርታን ዛሬ ይፋ አድርጓል።
ምርጫ ቦርድ ዛሬ ይፋ ባደረገው የምርጫ ክልሎችን የሚመለከተው ካርታ 547 የምርጫ ክልሎችን የያዘ ነው።
እያንዳንዱ ክልልና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች ለፌዴራል ምክር ቤት የሚኖራቸው የምርጫ ክልሎችን አሳውቋል።
በዚህም መሠረት ትግራይ 38፣ አፋር 8፣ አማራ 138፣ ኦሮሚያ 178፣ ሶማሌ 23፣ ቢንሻንጉል 9፣ ደቡብ 123፣ ጋምቤላ 3፣ ሐረሪ 2፣ ድሬዳዋ 2 እና አዲስ አበባ 23 ለፌዴራል ምክር ቤት የምርጫ ክልሎች ይኖራቸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በካርታ ይፋ የምርጫ ክልል ኖሮት እንደማያውቅና ይህ የመጀመሪያው የምርጫ ክልሎችን የሚያሳይ ካርታ እንደኾነ ካርታውን ይፋ በኾነበት ወቅት ተናግረዋል።
አሁን የተጠቀሱት የምርጫ ክልሎች በ1976 ዓ.ም. በደርግ ዘመን የተካሔደውን የሕዝብና ቤት ቆጠራ መሠረት ያደረግና በ1985 ዓ.ም. መካለላቸውንም ሰብሳቢው ጠቁመዋል። በዚሁ ካርታ ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሠጥተዋል። (ኢዛ)



