PM Dr. Abiy Ahmed and Canadian PM Justin Trudeau

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የካናዳውን ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትርሩዶን ሲቀበሉ (ጥር 29 ቀን 2012 ዓ.ም.)

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ የበርካታ አገራት መሪዎችን ሲቀበሉ ነበር

ኢዛ (እሁድ የካቲት ፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 9, 2020)፦ 33ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ ከዛሬ የካቲት 1 እስከ የካቲት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይካሔዳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በስብሰባው ላይ ተካፋይ የኾኑ አገራትን ሲቀበሉ ነበር።

ይህ ጉባዔ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ የሕብረቱ ሥራ አስፈፃሚ ስብሰባ ሲያካሒዱ ቆይተዋል።

በዚህ ጉባዔ ላይ ለመገኘት የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች ወደ አዲስ አበባ እየገቡ ነው።

ከአፍሪካ አገራት መሪዎች ሌላ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትርሩዶን ከትናንት ወዲያ ምሽት አዲስ አበባ ገብተዋል።

ይህንን ጉባዔ አስመልክቶ ጥር 29 ቀን 2012 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የሚከተለውን መልእክት አስተላልፈዋል።

“33ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ የፊታችን የካቲት 1 እና 2 በአዲስ አበባ ይካሔዳል። የአፍሪካ መዲና፣ የዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከልና የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ የኾነችው አዲስ አበባችን እንግዶቿን ለመቀበል ቀደም ያለ ዝግጅት አድርጋለች። ከመሪዎቹ ጉባዔ በፊት የሚደረገው የሕብረቱ የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባም በመካሔድ ላይ ነው።

“ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት፣ ለአፍሪካ ነፃነት ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተች፣ አፍሪካውያን አንድ ኾነው ጠንካራ ሕብረት እንዲመሠርቱ የማዕዘን ድንጋዩን ያስቀመጠች አገር ነች። አፍሪካውያን እኅቶቻችንና ወንድሞቻችን ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ወደ ሌላ አገር እንደሚመጡ አይሰማቸውም። የሚመጡት ወደ አገራቸው ነውና። የሚሰበሰቡት በአገራቸው ነውና። የሚመላለሱትም በሕዝባቸው መካከል ነውና።

“ይህ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የተሳካ እንዲኾን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለዘመናት ስታደርጉት የኖራችሁትን ኢትዮጵያዊ መስተንግዶ ከፍ አድርጋችሁ እንድትደግሙት እጠይቃለሁ። በጉባዔው ምክንያት መንገድ ቢዘጋጋ ለእንግዳ የሚሠጥ ኢትዮጵያዊ ቅድሚያ ነው ብለን በጸጋ እንቀበለው፣ አንዳንድ የተለመዱ እንቅስቃሴዎቻችን ቢስተጓጎሉ ‘ቤት ለእንግዳ!’ ብለን እንለፈው።

“በሆቴሎች የተሠማራችሁ አስተናጋጆች የኢትዮጵያ አምባሳደሮች መኾናችሁን አስቡ፤ በመንገድ ላይ የቆማችሁ ፖሊሶች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዝብ የመደባችሁ አስተናጋጆች መኾናችሁን እንዳትዘነጉ። ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ጉባዔው አዳራሽ የተመደባችሁ ባለሞያዎች የአገራችሁን ገጽታ የምታሳዩ መስተዋቶች እንደኾናችሁ ስነግራችሁ፤ በአገልግሎታችሁ በመተማመን ነው።

“ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጉባዔው ፍጻሜ ድረስ መላ ኢትዮጵያውያን በመስተንግዶና ለሚሠጡ መመሪያዎች በመተባበር የሚቻላችሁን ሁሉ እንድታደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ። ከሁሉም በላይ ድል አድራጊ ጸሎታችሁ እንዳይለየን አደራ እላለሁ።” (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ