የቀድሞ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ዘላለም ተሾመ

(አድማስ ዜና) በአትላንታ ከተማ ለበርካታ ዓመታት፣ ከዚያም ደግሞ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በዲሲ መኖሪያውን አድርጎ የቆየውና የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋችና ከዚያም በፊት የመብራት ኃይል ክለብ ተጫዋች የነበረው ዘላለም ተሾመ ማረፉ ተነገረ።
ዘላለም ላለፉት ጥቂት ወራት በካንሰር ሕመም ተጠቅቶ በሕክምና ቆይቷል። ከዚያም ሕክምናውን በጸበል ለመከታተል ወደ ኢትዮጵያ ቢጓዝም፤ እዚያ በደረሰ በማግስቱ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል። የቀብር ሥነ ሥርዓቱም ዛሬ መፈጸሙ ተነግሯል።
ዘላለም ተሾ፣ አሜሪካ ከመምጣቱ በፊት ለኬንያው ጉርማህያ ክለብም በፕሮፌሽናልነት ተጫውቷል። አሜሪካ ከመጣ በኋላ በተለይ በአትላንታ ቆይታው፣ ወጣቶችን ኳስ በማሰልጠን፣ በተለያዩ ድርጅቶች መካከልም ዓመታዊ የእግር ኳስ ግጥሚያ በማዘጋጀት ትልቅ ስፖርታዊ መነቃቃትን ፈጥሮ ነበር።
ወደፊትም ብዙ ለመሥራት ዕቅድ እንደነበረው በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ቀርቦ የተናገረበት ጊዜ ሩቅ አልነበረም። ዘላለም ተሾመ ከእግር ኳስ ተጫዋችነቱ በተጨማሪ ሙዚቃም በመጫወት ከመታወቁም በላይ አንድ የሙዚቃ ሲዲ አሳትሟል። አድማስ ሬዲዮ ለስፖርት ፕሮግራሙ መግቢያ የሚጠቀምበት ሙዚቃም የዘለላም መሆኑ ይታወቃል።
ለቤተሰብና ለመላው አድናቂዎቹ በሙሉ መጽናናትን እንመኛለን። ነፍስ ይማር።



