አዲስ አበባ ውስጥ ሴት የፓርላማ አባል ተገደሉ
መንግሥት በተፈጥሮ ነው የሞቱት ቢልም፤ ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ይጠረጠራል
ኢትዮጵያ ዛሬ (ረቡዕ ኅዳር ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. Nov. 16, 2016)፦ የተከበሩ የፓርላማ ተመራጭ ወ/ሮ አዲሴ ዘለቀ አዲስ አበባ በሚገኘው ጽሕፈት ቤታቸው ትናንት ተገድለው እንደተገኙና ዛሬ እንደተቀበሩ ለኢትዮጵያ ዛሬ የደረሰው ዘገባ አስረዳ። የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ”ባጋጠማቸው ድንገተኛ ሕመም” ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን ቢዘግቡም፤ ወ/ሮ መገደላቸውን የሚጠቁሙ ያልተጣሩ ፍንጮች እንዳሉ ከደረሰን ዘገባ ለመረዳት ችለናል።
ወ/ሮ አዲሴ ዘለቅ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቡት የባህር ከተማ አስተዳደርን በመወከል ሲሆን፣ ህወሓት መራሹ መንግሥት በአማራ ሕዝብ ላይ ሲያደርስ የነበረውን ግፍ ይቃወሙና ይተቹ እንደነበር የደረሰን ዘገባ ይጠቁማል።
የወ/ሮ አዲሴ አሟሟት በትክክል ምክንያቱ ያልታወቀ ቢሆንም፤ ወ/ሮዋ በመንግሥት ደህንነቶች ሳይገደሉ እንዳልቀሩ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ወገኖች ያላቸውን ጥርጣሬ ለኢትዮጵያ ዛሬ አልሸሸጉም።
የወ/ሮ አዲሴ ዘለቅ የቀብር ሥነሥርዓት በዛሬው ዕለት ባህር ዳር በሚገኘውና ድባንቄ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ እንዲሁም ከፍተኛ የብአዴን ባለሥልጣናት በተገኙበት ተፈጽሟል። ወይዘሮዋ ከዚህ ዓለም የተለዩት በ፵፰ ዓመታቸው ሲሆን፣ የሁለት ልጆች እናት መሆናቸውን ለመረዳት ችለናል።



