Volcanic eruption on Zeriy mountain around Injibara

ኢትዮጵያ ዛሬ (ቅዳሜ ኅዳር ፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. November 12, 2016):- በእንጅባራ ከተማ በስተሰሜን ፭ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውና እንደዋ ቀበሌ ውስጥ ያለው ዝርይ የተባለው ፬፻ ሜትር ከፍታ እንዳለው የሚገመተው ተራራ፤ ከትናንት ኅዳር ፪ ቀን ከጠዋቱ ፬ ሰዓት ጀምሮ መጨስ መጀመሩንና ምክንያቱ እሳተ ገሞራ እንደሆነ ከአካባቢው የወጡ መረጃዎች ጠቆሙ። እሳተ ገሞራው ከፈነዳ አካባቢው በውሃ ሊጥለቀለቅ ይችላል የሚል ፍራቻ አለ።

በሥፍራው ያለውን ሁኔታ የተመለከቱ ወገኖች እንደሚሉት ከሆነ ተራራው ዙሪያውን በደን እና በአለት የተሸፈነ ሲሆን፣ ዙሪያውን በማያቋርጥ ጭስ ተከብቦ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ፤ ከፍተኛ የአለት መሰነጣጠቅ ድምፅ እየሰሙ መሆኑን ገልጠዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲህ ያለ ሁኔታ አይተው እንደማያውቁ የገለጡ ሲሆን፣ በትናንትናው ዕለት ምንም አይነት በሰውም ሆነ በንብረት ላይ የደረሰ አደጋ ባይኖርም፤ በተራራው አካባቢ በሚኖሩ አዕዋፋትና የዱር አራዊቶች ላይ ግን ጉዳት መድረሱን ነዋሪዎቹ አልሸሸጉም።

እንደአካባቢው ነዋሪዎች ገልጻ ከሆነ፣ ተራራው ከተቃጠለና እሳተ ገሞራው ከፈነዳ አካባቢው በውሃ ሊጥለቀለቅ ይችላል የሚል ስጋት አለ። በጉዳዩ ላይ እስካሁን በኦፊሴል የባለሙያዎች አስተያየት አለመሰጠቱን ለመረዳት ችለናል።

እሳተ ገሞራው ሊፈነዳ ይችላል ተብሎ እየተጠበቀ ቢሆንም፤ የክልሉና የፌዴራሉ መንግሥቶች ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ የአካባቢውን ሰዎች ከቦታው ለማሸሽ ያደረጉት እንቅስቃሴ አለመኖሩን ለመረዳት ችለናል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ