በአውሮጳ የኢትዮጵያዊያን የስፖርት ውድድርና የባህል ፌስቲቫል በስዊድን ይካሄዳል
መንግሥቱ ወርቁ በክብር እንግድነት ይገኛል
Ethiopia Zare (እሁድ ሐምሌ 6 ቀን 2000 ዓ.ም. July 13, 2008)፦ ስድስተኛው የአውሮጳ የኢትዮጵያዊያን የስፖርትና የባህል ፌስቲቫል ሐምሌ 25 እና 26 (August 1 እና 2) በስዊድን ርዕሰ ከተማ ስቶክሆልም እንደሚከናወን የውድድሩ አዘጋጅ ማኅበር ለኢትዮጵያ ዛሬ ገለፀ።
በዚህ ታላቅ የስፖርት በዓል ላይ ከ12 የተለያዩ የአውሮጳ አገሮች የሚመጡ 20 የእግር ኳስ ቡድኖች ተሳታፊ እንደሚሆኑ እና ሁሉም ቡድኖች በስቶክሆልም መሃል ከተማ በሚገኙ የተለየዩ ሆቴሎች ቦታ መያዛቸውን በስዊድን የኢትዮጵያ ስፖርትና የባህል ፌስቲቫል አዘጋጅ ማኅበር ተወካይ አቶ መኮንን ደመቀ ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጿል።
በዚህ ውድድር ላይ ከስዊድን 3 ቡድኖች፣ ከእንግሊዝ 3 ቡድኖች፣ ከጀርመን 5 ቡድኖች፣ ከሆላንድ 2 ቡድኖች እና ከጣሊያን 2 ቡድኖች የሚመጡ ሲሆን፤ ስዊዘርላንድ፣ ቤልጅየም፣ ፈረንሣይ፣ ኖርዌይ እና ፊንላንድ አንድ አንድ የእግር ኳስ ቡድን ይዘው በውድድሩ ላይ ይሳተፋሉ።
ውድድሩ የሚከናወነው ”ስካርፕኔክስ ስፖርትፌልት” (Skarpnäks Sportfält) ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ነው። ከእግር ኳስ ውድድሩ በተጨማሪ የአትሌቲክስ፣ የሴቶች የመረብ ኳስ እና የገመድ ጉተታ ውድድር የሚካሄድ ሲሆን፣ የራስ ቴአትር የባህል ተወዛዋዦችም በሜዳው ላይ ለህዝቡ ድንቅ ትርዒቶችን እንደሚያቀርቡ ታውቋል።
ለዚህ የስዊድን ታላቅ ውድድር በክብር እንግድነት የ3ኛው አፍሪካ ዋንጫ የኢትዮጵያ ባለውለታ እና የኢትዮጵያ የኳስ ዶክተር በሚል ስም የሚታወቀው አቶ መንግሥቱ ወርቁ በመገኘት ለአሸናፊው ቡድን ዋንጫ እንደሚሸልሙ አቶ መኮንን ገልጿል። ስለበዓሉ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት http://www.ethiosweden.se ይጎብኙ።



