ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ዜና ማርቆስ አረፉ
Ethiopia Zare (እሁድ የካቲት 7 ቀን 2002 ዓ.ም. February 14, 2010)፦ በሲያትሉ ቅዱስ ገብርኤል መቀመጫቸውን አድርገው በተለያዩ ሀገራት ለሚገኙ የኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ምዕመናንን ሲያገለግሉ የነበሩት ታላቅ አባት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ዜና ማርቆስ ትናንት ቅዳሜ የካቲት 6 ቀን 2002 ዓ.ም. አረፉ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከልጅነታቸው ጀምሮ በመታዘዝ፤ ምዕመናንን በማገልገልና የሀገሪቱን አኩሪ ታሪክ በመጠበቅ የሕይወት ዘመናቸውን ሙሉ ለህዝብና ለሀገራቸው እንደኖሩ የሚነገርላቸው አባት ዕረፍት በሲያትልና በመላው ዓለም የሚገኙ ምዕመናንን ያስደነገጠ መሆኑ ታውቋል።
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ዜና ማርቆስ በአገልግሎት ዘመናቸው ችግሮችን አቻችለው በማሳለፍና ፍቅርን በመስበክ የሚታወቁ ሲሆን፤ የሀገርና የኃይማኖት ታሪኮችን በመጠበቅ በጽናት የቆዩ አባት ነበሩ። በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍላተ ሀገራት በመዘዋወር ከልጅነት ጊዜያቸው ጀምሮ የኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በተለያዩ የዓለም ሀገራትም በመዘዋወር ከፍተኛ ትምህርቶችን ወስደው ህዝባቸውን ለማገልገል እንደበቁም ለመረዳት ችለናል።
ብጹዕ አባታችን ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለኃይማኖት ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ እንዲሁም የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ ፓትሪያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ምክትል ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
አቡነ ዜና ማርቆስ ከሚወዷት ሀገራቸው በስደት ከወጡ በኋላም በተለያዩ ሀገራት በስደት የሚኖሩ ምዕመናንን በማሰባሰብና በማስተማር እንዲሁም አጥቢያ ቤተክርስቲያናትን በማሠራት ታላላቅ ስራዎችን ያበረከቱ አባት ነበሩ።
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ዜና ማርቆስ በቃላቸው መሰረት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ታላላቅ የኦርቶዶክስ ተዋኅዶ አባቶች፣ ጳጳሳትና ታላላቅ ሊቃውንት በተገኙበት ሽኝታቸው ወደ እየሩሳሌም ኪዳነ ምህረት ሊሆን እንደሚችል ምንጮች ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል በታላላቅ አባቶች የተዘጋጀውን የአባታችን ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ዜና ማርቆስን የሕይወት ታሪክ ይዘን እንደምንቀርብ እየገለጽን ላስተማሯቸው፣ ላገለገሏቸው፣ ለሚወዱት ህዝባቸውና ለመላ ቤተሰቦቻቸው ብርታትንና መጽናናትን ያገኙ ዘንድ እንመኛለን።



