በትግራይ ክልል ያለው እንቆቅልሽ ምንድን ነው?
 
		ሕወሓት ሥልጣን ከመቆናጠጡ በፊት የነበረ የኢትዮጵያ ካርታ
ከምርጫ ወደ ተኩስ አቁም እወጃ
ኢዛ (ማክሰኞ ሰኔ ፳፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 29, 2021)፦ ያሳለፍነው ሳምንታት የአገሪቱ ወቅታዊ አጀንዳ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ነበር። በሰዓታት ልዩነት የሚነገረውና የሚዘገበውም ይኸው የምርጫ ሒደትና ከዚሁ ጋር የተያያዙ ኹነቶች ነበሩ። ትናንት ምሽት ላይ የተሰማ አንድ ዜና ግን የምርጫ ወሬውን ሸፋፍኖ ትኩረቱ ሁሉ ወደ ሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ኾኗል። በተለይ በትግራይ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አዋጅ መባሉ ለብዙዎች ዱብ እዳ ነበር።
ይህ ዜና ያልተጠበቀ ቢኾንም ይህንን እወጃ ተከትሎ በሽብርተኝነት የተፈረጀው የሕወሓት ታጣቂዎች ቡድን አባላት ወደ መቀሌ እየገቡ ስለመኾኑ በተለያየ መንገድ እየተገለጸ ነው።
መንግሥት ወደዚህ እርምጃ የገባው ለምንድነው? የሚል ጥያቄ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰማ ሲሆን፤ አንዳንዶችም የመንግሥት እርምጃ ትክክል ነው የሚል ትንታኔ እየሰጡበት ነው። በሽብርተኝነት ከተፈረጀው የሕወሓት ቡድን አባላት እየተሰማ ያለው፤ ታጣቂዎቹ ወደ መቀሌ መግባታቸውንና የከተማው ነዋሪዎችም የክልሉን ባንዲራ በመያዝ ደስታቸውን በጐዳና ላይ መግለጸቸውን የሚያትት ነው።
መንግሥት በመቀሌ ያለውን የመከላከያ ኃይል ከመቀሌ ማስወጣቱና የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ በቀጣይ ምን ይኾናል የሚለው ነገር፤ አሁንም ትልቅ መነጋገሪያ ኾኗል። መንግሥት የተኩስ አቁሙን ያደረገው “የመኸር እርሻ ጊዜው እስኪጠናቀቅ” የሚል ቢኾንም፤ በአንጻሩ የሕወሓት ቡድን መቀሌንና ሌላውን ክልሉን በመያዝ በራሱ መንገድ እንዲጓዝ እድል የሚሰጠው እንደኾነ እየተነገረ ነው።
ትግራይ እንደ አንድ የኢትዮጵያ ክልል ትቀጥላለች አትቀጥልም የሚለውም ጥያቄ አሁን እየኾነ ካለው ነገር ጋር ሲተያይ፤ ክልሉ በሽብርተኝነት በተፈረጀው ሕወሓት እጅ እንዲወድቅ የሚያደርግ ነው።
በአንጻሩ ግን የመንግሥት ውሳኔ ትክክል መኾኑን ከሚያመለክቱ መረጃዎች መገንዘብ እንደሚቻለው የጦርነቱ መቀጠል አገሪቷን የበለጠ ዋጋ እያስከፈላት በመኾኑ፤ ይህንን ጉዳይ ለማቆም የሔደበት መንገድ አግባብ እንደኾነ ያመለክታል።
በትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገ ሲሆን፤ አሁንም ጦርነቱ ከቀጠለ ከፌዴራል መንግሥቱ ተጨማሪ ወጪ በማውጣት መቀጠል እንደሌለበት የሚገልጹ ወገኖች፤ የመንግሥት እርምጃ ትክክል ነው እያሉ ነው።
ኾኖም ግን ከዚህ በኋላ ያለው ቀጣይ ክስተት ግን ምን ይኾናል የሚለው ለብዙዎች እንቆቅልሽ ኾኗል።
 
የተናጠል የተኩስ አቁም እወጃው የተለያየ ምልከታዎች እየተሰነዘሩበት ሲሆን፣ ውሳኔው የውጭ መንግሥታትንም አስተያየታቸውን እንዲሰጡ አድርጓል። ቻይና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደውን እርምጃ አወንታዊ ሲል የተናጠል የተኩስ አቁሙን እወጃ ደግፏል። በተመሳሳይ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስም ተመሳሳይ ድጋፏን ሰጥታለች፤ መፍትሔው ፖለቲካዊ ነውም በማለት አስታውቃለች።
የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም የተኩስ አቁሙን አወንታዊ ብለውታል።
አሜሪካ በበኩሏ የተኩስ አቁም አዋጁን እንደምትደግፍ ገልጻ፤ ነገር ግን የተኩስ አቁሙ ውጤት የሚያመጣ ከኾነ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንደምትጥል መግለጿ ታውቋል።
እንዲህ ያሉ ምልከታዎች እየተሰነዘሩ ሲሆን፣ ከወደ መቀሌ የሚሰማው ግን የፌዴራል የጸጥታ ኃይል ከወጣ በኋላ ዘረፋ ተባብሷል። ሰዎችም እየተገደሉ ነው እየተባለ ነው።
በጥቅል ግን የትናንቱ የመንግሥት ውሳኔ አሁንም ብዥታ እንደተፈጠረ ነው። (ኢዛ)



