የኢትዮጵያን ፈተና ያበዛው የቴሌብር አገልግሎት
 
		የኢትዮ ቴሌኮም ሠራተኞች ከዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ ጋር በቴሌብር የማስመረቂያ መርኀ ግብር ላይ፣ ማክሰኞ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም.
ኢትዮ ቴሌኮምን በትሪሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያሽከረክር ተቋም ያደርገዋል
ቴሌብርን ከንግድ ባንክ ጋር በመኾን ይጀምራል
ቴሌብር እንደአገር ዱላ እንዲበዛበት ያደረገ ነው
ኢዛ (ረቡዕ ግንቦት ፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. May 12, 2021)፦ ኢትዮ ቴሌኮም በኢትዮጵያ ከፍተኛውን የገንዘብ እንቅስቃሴ ያከናውናል ተብሎ የሚጠበቀው “ቴሌብር” የተሰኘ ዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት ትናንት ማክሰኞ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ አደረገ። መጀመሪያ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመኾን ሥራውን እንደሚጀምር ተጠቆመ። ይህ አገልግሎት ኢትዮጵያ አሁን እያረፉባት ላሉት ዓለም አቀፍ ተጽእኖዎች ምክንያት እንደኾነም ተገለጸ።

ይህ ሁሉን አካታች የገንዘብ ማስተላለፊያ መገበያያ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት መተግበሪያ በትናንትናው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት በይፋ መጀመሩ ታውቋል።
የኢትዮ-ቴሌኮም ይህ አገልግሎቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የሚባለውን የገንዘብ እንቅስቃሴ የሚያሳልጥ ተቋም የሚያደርገው ይኾናል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ “ቴሌብር” የተሰኘው አገልግሎት ኩባንያውን ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን በሁለት እና በሦስት እጅ ያሳድጋል ተብሎ ይታመናል። ዶ/ር ዐቢይም ቴሌ ይህንን መጀመሩ አሁን እያገኘ ካለው የትርፍ መጠን በእጅጉ ብልጫ ያለው ትርፍ የሚያገኝበት እንደሚኾን በትናንቱ ፕሮግራም ላይ ገልጸዋል።
ከፍተኛ የኾነ የገንዘብ እንቅስቃሴ ይደረግበታል የተባለው “ቴሌብር”፤ ይህንን አገልግሎቱን አሁን ላይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመኾን የሚሠራው መኾኑን የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ያገኘው መረጃ ያስረዳል።
እንደ መረጃው ከኾነ አሁን ላይ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመኾን የገንዘብ እንቅስቃሴውን የሚያካሒድ ቢኾንም፤ ከሌሎች ባንኮች ጋርም በመተሳሰር የሚተገበረው ይኾናል ተብሏል።
ቴሌብር የሚሰጣቸው አገልግሎቶች
በሞባይል ስልክ ተጠቅሞ ገንዘብ ለማዘዋወር፣ ገንዘብ ለመቀበል፣ ግብይት ለመፈጸምና ሌሎች የገንዘብ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን የሚያስችለው ይህ አገልግሎት፤ ከውጭ የሚላክ ገንዘብን ከገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ጋር በመኾን ወደ ሥራ ያስገባል ተብሎ ይጠበቃል።

ከዚህ ሌላ በ“ቴሌብር” በባንኮች የሚፈጸሙ ክፍያዎችን ለመክፈል የሚያስችል መኾኑም ተጠቅሷል። በባንክ አካውንት ያለን የገንዘብ መጠን ለማወቅ እና ከየትኛውም ቦታ ኾኖ በሞባይል ስልክ ወጪና ገቢን ለመከታተል የሚያስችል ነው። የሞባይል የአየር ሰዓት ለመሙላት፣ ጥቅል የሞባይል አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል ነው።
የውኃ፣ የመብራትና የመሳሰሉ የአገልግሎት ክፍያዎችንም በ“ቴሌብር” መክፈል እንደሚቻል ታውቋል።
በቴሌብር ይንቀሳቀሳል ተብሎ የሚገመተው የገንዘብ መጠንና የደንበኞች ቁጥር
የዚህን አገልግሎት መጀመር አስመልክቶ የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዳመለከቱት፤ አገልግሎቱ በሚጀመርበት የመጀመሪያው ዓመት 67 ሚሊዮን ብር በቴሌ ብር የሚንቀሳቀስ መኾኑን የገለጹ ሲሆን፤ ከአምስት ዓመት በኋላ ደግሞ የተጠቃሚዎቹን ቁጥር በማሳደግ በ“ቴሌብር” ከ3.5 (ከሦስት ነጥብ አምስት) ትሪሊዮን ብር በላይ የሚንቀሳቀስ እንደሚኾን ያላቸውን ግምት ሰጥተዋል።
በአምስት ቋንቋዎች አገልግሎት የሚሰጥ ነው። ይህ አገልግሎት የፋይናንስ ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያዘምን ጭምር ያመለከቱት የኢትዮ ቴሌኮም ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፤ በመጀመሪያው ዓመት 21 ሚሊዮን ደንበኞች የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚ ይኾናሉ ብለዋል። ከዚህም ውስጥ 12.5 (አሥራ ሁለት ነጥብ አምስት) ሚሊዮን ደንበኞች መደበኛ ተጠቃሚ ይኾናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አክለዋል።

አገልግሎቱ በተጀመረበት የመጀመሪያው ዓመት 710 ሚሊዮን ትራንዛክሽን በቴሌ ብር እናንቀሳቅሳለን ብለው እንደሚያምኑ የገለጹት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ በአንድ ዓመት 69.10 (ስልሳ ዘጠኝ ነጥብ አንድ) ቢሊዮን ብር በቴሌ ብር እንደሚንቀሳቀስ ተገምቷል። ከአምስት ዓመት በኋላ 33 ሚሊዮን ደንበኞች ማፍራት ይቻላልም ብለዋል።
በቴሌብር ምክንያት ዓለም አቀፍ ጫናዎች በኢትዮጵያ ላይ መበርከታቸው
አገልግሎቱን በይፋ ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የቴሌ ብር ሥርዓት መጀመር የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተለያዩ ሚዲያዎች ኢትዮጵያ ላይ እየተፈጸመ ያለው ጫና አንዱ ምክንያት ይኸው ከ“ቴሌብር” ጋር የተያዘ መኾኑን ገልጸዋል።

ይህንን ሲያብራሩ “ኢትዮጵያ በንግድ በኩል የቴሌኮም ገበያውን እከፍታለሁ እያለች፤ በሌላ በኩል ደግሞ ዋናውን ሁለት ሦስተኛ ትርፍ የሚያስገኘውን ዘርፍ ለራስዋ ቴሌኮም ሰጠች በሚል ነው” ብለዋል።
ይህንን ጉዳይ አንዳንዱ በግልጽ የሚናገረው ሲሆን፤ አንዳንዱ ደግሞ ይህንን ትቶ በሌላ መንገድ ዱላውን ያሳርፋል በማለት ተናግረዋል። “ይህ ዱላ እንዳያርፍብን የፈቀድንበት ዋናው ምክንያት፤ ከብሔራዊ ጥቅም ጋር በቀጥታ የሚያያዝ ስለኾነ ነው” በማለትም አክለዋል።
እንደ አገር በዚህ ረገድ አቅም ካልፈጠርንና ሁሉን ነገር ክፍት ካደረግን፤ ለውድድር የሚያመች ልምድ ስላልነበረን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ታስቦ አሁን ለሁለት የቴሌኮም ፍቃድ ሲሰጥ የሞባይል ባንኪንግ ያለመካተቱን ተናግረዋል።
ይህ ባለመኾኑ የኢትዮጵያ መንግሥት በትንሹ 500 ሚሊዮን ዶላር ማጣቱንም ገልጸዋል። ስለዚህ የዲፕሎማሲውን ጫና መቋቋም ባንችል ኢትዮ-ቴሌኮም 500 ሚሊዮን ዶላር ማምጣት ይጠበቅበታል በማለት፤ አሁን ኢትዮጵያ ላይ እያረፈ ያለው ጫና አንዱ ምክንያት ይኸው የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቱ የቴሌኮም ዘርፉን ለውጭ በማስተላለፍ በተጀመረው እንቅስቃሴ እንዳይካተት የመደረጉ ምክንያት እንደኾነም አብራርተዋል።
የሞባይል ባንኪንጉ ለአንድ ዓመት ብቻ በኢትዮ-ቴሌኮም የሚያዝ ሲሆን፤ ከዚያ ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ይኾናል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ በሌላ በኩል ግን ኢትዮ-ቴሌኮም እንዲህ ያለውን የመንግሥት የፖሊሲ ውሳኔ መጠቀም የሚችለው ለአንድ ዓመት ብቻ መኾኑን ተናግረዋል።
በአንዱ ዓመት ውስጥ ግን ኢትዮ-ቴሌኮም አቅሙን አጐልብቶ ከሌሎች ተወዳዳሪ ኩባንያዎች ጋር መወዳደር የሚችልበትን አቅም መፍጠር እንደሚኖርበት አመልክተዋል።
በዚህ ገለጻቸው የሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቱ ለውጭ ኩባንያዎችም ክፍት ሊኾን እንደሚችል የሚያመለክት ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
ኢትዮ-ቴሌኮም በአሁኑ ጊዜ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የሞባይል ስልክ ደንበኞች አሉት። (ኢዛ)



