የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት ላይ ያለ ይለፍ መታደም እንደማይቻል ተገለጸ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ
ፓትሪያርኩ ደመራ ከአምስት ሺህ ባልበለጡ ሰዎች ይከበራል አሉ
ኢዛ (ረቡዕ መስከረም ፲፫ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 23, 2020)፦ በመስቀል ደመራና በኢሬቻ በዓል ላይ ይለፍ ያልያዘ እንደማይታደምና የበዓሉ ተሳታፊ የሚኾኑ ባጅ የተሰጣቸው ብቻ መኾኑን ፖሊስ አስታወቀ።
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ጥንቃቄ ለማድረግ በሁለቱም በዓላት ውስን ሰዎች እንዲገኙ በተደረገው ስምምነት መሠረት የሁለቱም በዓላት ታዳሚዎች የይለፍ ካርድ (ባጅ) መያዝ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ ይህንን መተላለፍ እንደማይቻልም ታውቋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ በእነዚህ በዓላት ላይ ሌሎች ክልከላዎችን የጣለ ሲሆን፤ ክልከላዎችን በተላለፉት ላይ እምርጃ እንደሚወሰድና የፍተሻና የአሰሳ ሥራዎችም ይሠራሉ ተብሏል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ እንዳስታወቁትም፤ የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል ከአምስት ሺህ ባልበለጡ ሰዎች የሚከበር መኾኑን ነው። የፊታችን ቅዳሜ መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም. የደመራ በዓልም በመስቀል አደባባይ የሚከበር ይኾናል። (ኢዛ)



