የሶማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባን በተመለከተ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (ምርጫ 2013)
ኦብነግ፣ ነፃነት እና እኩልነት፣ ኢዜማ እና የግል እጩ ተወዳዳሪዎች ለቦርዱ አቤቱታዎች አቅርበዋል
ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ 2013 የመራጮች ምዝገባ ሒደት ላይ ከፍተኛ አቤቱታ የቀረበበት በሶማሌ ክልል እየተከናወነ ያለው የመራጮች ምዝገባ ሒደት ነው። በዚህ ሒደት ላይ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ለቦርዱ አቤቲታዎችን ያቀረቡ ሲሆን፤ (ኦብነግ፣ ነፃነት እና እኩልነት፣ ኢዜማ እና የግል እጩ ተወዳዳሪ)፣ ሕጋዊ ያልኾነ የምዝገባ ሒደትን የሚያሳዩ ምስሎች እና ቪዲዎችም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲታዩ ነበር፤ ቦርዱም በሚዲያ ሞኒተሪንግ ክፍሉ ተሰበስቦ ቀርቦለት እነዚህን ምስሎች እና ቪዲዮዎች ተመልክቷል።
ከፓርቲዎች በተለያየ ጊዜ በጋራ እና በተናጠል የቀረቡለት አቤቱታዎች ያተኮሩባቸው አንኩዋር ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፤
1. የመራጮች ምዝገባ ካርዶች የማይገባቸው ሰዎች እጅ ገብቷል፣ ከምርጫ ጣቢያ ውጪ ካርዶች ሲታደሉ ነበር።
2. ያልተሞሉ የመራጮች ምዝገባ ካርዶች ለዝቅተኛው መንግስት እርከን (ቀበሌ ወረዳ ሠራተኞች) እና እጩዎች ተሰጥተዋል
3. የመራጮች ምዝገባ ሒደቱን የገዥው ፓርቲ የዝቅተኛ እርከን ሠራተኞች ከፍተኛ ጣልቃገብነት ነው የሚሠራው፣ በዚህም ምክንያት የመራጮች ምዝገባ በቦርዱ ቁጥጥር ስር አይደለም
4. የምርጫ አስፈጻሚዎች ከመንግስት አስተዳደር እርከን ሠራተኞች እና እጩዎች ጋር በዝምድና እና በተለያዩ መንገዶች የተያያዙ በመኾናቸው የገለልተኝነት ጥያቄ አለ
5. የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ዜጎች እንዳይመዘገቡ ክልከላ ተደርጎባቸዋል፣
6. የመራጮች ካርድ የወሰዱ ዜጎች እጅ ተመልሶ ተሰብስቧል
7. የመራጮች ካርድ ብሉ ቦክስ በምርጫ ጣቢያዎች ሲደርስ በተገቢው መንገድ ሳይታሸግ ነው ይህም በመካከል እንደተከፈተ ያሳያል… የሚሉ ናቸው። ለነዚህ አቤቱታዎች ዝርዝር የጽሁፍ አቤቱታ፣ የፎቶ፣ የቪዲዮ እና ሌሎች ማስረጃዎች ይኾናሉ የሚሉ ሰነዶችን አቅርበዋል።
አቤቲታዎቹን መሰረት በማድረግ ቦርዱ የሚከተሉትን ተግባራት አከናውኗል።
- አቤቱታ ካቀረቡ የፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር በማእከልም በክልሉም ውስጥ ውይይት አከናውኗል።
- በቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ የሚመራ አጣሪ ቡድን ወደ ክልሉ በመላክ ምርጫ ጣቢያዎችን፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችን እና ሌሎች አካላትን አነጋግሯል።
- የቀረቡ አቤቱታዎችን እና ሰነዶችን በማየት ስብሰባ አከናውኖ የሚከተሉትን ዋና ዋና ውሳኔዎች ወስኗል።
የሶማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ ውሳኔ
1. የመራጮች ምዝገባ ሒደቱ ላይ የቀረቡትን ዝርዝር አቤቱታዎች በስፋት መርምሯል፤ በማስረጃነት የቀረቡለትን ከ150 በላይ የኾኑ ባዶ እና ምዝገባ የተፈፀመባቸው የመራጭ ካርዶችን በመራጮች ምዝገባ ሲስተሙ ላይ ካለው ዳታ ጋር አገናዝቦ ተመልክቱዋል፤ የቀረቡ የቪዲዮ ማስረጃዎች (ትርጉም) እና ምስሎችን ከአቤቱታው ጋር አገናዝቧል።
በእነዚህ ሒደቶች ከተመለከታቸው ዝንባሌዎች (trends) በአቤት ባዮቹ የተጠቀሱት ብልሹ አሠራሮች ተፈፅመው ሊኾን እንደሚችል ግንዛቤ በመውሰድ፤ይህ ሁኔታም በሒደቱ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ የሚፈጥር መኾኑን እነዲሁም መጣራትን ለመጀመር በቂ የኾነ መረጃ እንዳለ በመገንዘብ ከፍተኛ የኾነ የመራጮች ምዝገባ ሒደት የአሠራር መዛባት አቤቱታ የቀረበባቸው በሶማሌ ክልል የሚገኙ የሚከተሉት የምርጫ ክልሎች ላይ የመራጮች ምዝገባ በጊዜያዊነት አንዲቆም ወስኗል።
እነዚህም
- የምርጫ ክልል አራቢ (ለክልል ምክር ቤት አውበሬ እና ደንበል ከተማ ምርጫ ክልሎችን የሚያካትት)
- ምርጫ ክልል ደግሃመዶ
- የምርጫ ክልል ጎዴ (ለክልል ምክር ቤት አዳድሌ፣ ቤርአኖ፣ ደናን፣ ምሥራቅ ኢሚ፣ ኤልወይኔ፣ ጎዴ፣ ጎዴ ከተማ የምርጫ ክልሎችን የሚያካትት)
- የምርጫ ክልል ጂጂጋ 1 (ለክልል ምክር ቤት ጂግጂጋ፣ ጂግጂጋ ከተማ፣ ቱሉ ጉድሌ ምርጫ ክልሎችን የሚያካትት)
- ምርጫ ክልል ቀብሪደሃር (ለክልል ምክር ቤት ደበወይን፣ ቀብሪደሃር፣ ቀብሪደሃር ከተማ፣ መርሲን፣ ሼኮሽ እና ሺላሎ ምርጫ ክልሎችን የሚያካትት)
- ምርጫ ክልል ቀላፎ (ለክልል ምክር ቤት ፊርፊር እና ቀለፎ የምርጫ ክልሎችን የሚያካትት)
- ምርጫ ክልል ዋርዴር (ለክልል ምክር ቤት ደራቴሌ እና ዋርዴር ምርጫ ክልሎችን የሚያካትት)
2. ከላይ በተጠቀሱት የምርጫ ክልሎች ላይ ያለው የመራጮች ምዝገባ ሒደት በጊዜያዊነት ሲቆም አስፈጻሚዎች እና የሚመለከታቸው የቦርዱ ኦፕሬሽን ሠራተኞች የሚወስዱትን እርምጃ አስመልክቶ መመሪያ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በዚያ መመሪያ መሰረት ተፈጻሚ ይኾናል።
3. ከላይ በተጠቀሱት የምርጫ ክልሎች ላይ ያለውን የመራጮች ምዝገባ ሒደት የሚያጣራ ቡድን ቦርዱ የሚያቋቁም ሲሆን፤ በዚህም የማጣራት ሒደት ውስጥ የአቤቱታ አቅራቢ የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ የቦርዱ ሠራተኞች እና ገለልተኛ ባለሞያዎች የማጣራት ሒደቱን እንዴት ሊያከናውኑት እንደሚገባ የሚመራ የቴክኒክ ዝርዝር መመሪያን አዘጋጅቶ ወደተግባር የሚገባ ይኾናል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ሚያዝያ 30 ቀን 2013 ዓ.ም.



