የኃይሌ ገብረሥላሴ እግሮችና የተዘረጉ እጆች

ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ አዳማ በሚገኘውና በቅርቡ ባስመረቀው ኃይሌ ሪዞርት
ትዕግሥት መንግሥቴ (ኢዛ)
ሰውየው በእግሩ ሮጦ ባገኛቸው ድሎች የአገሩን ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በማድረግ ኢትዮጵያውያንን አንገታችን ቀና አድርገን በእንባ ጭምር ደስታችንን እንድንገልጽ ያስቻለ ኢትዮጵያዊ ነው። ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በላቡ የአገሩን ስም በዓለም አቀፍ መድረኮች አስጠርቷል። ዛሬም ድረስ የኃይሌን የሩጫ ጥበብና ድል የሚያስታውሱ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ስሙን ሲያነሱ፤ ኢትዮጵያን እንዲጠቅሱ ግድ ይላቸዋል።
የአትሌቲክስ ሕይወት ገደብ አለውና ኃይሌ ዛሬ በውድድር ቦታዎች ባናየውም፤ ዘወትር የምናስበው የአገር ጀግና ኾኖ ቀጥሏል። ከሩጫው በመለስ ኃይሌን ደጋግመን የምናነሳባቸው በርካታ ተግባራት አሉት። የአገር ሽማግሌ ኾኖ ለሰላምና እርቅ ጐንበስ ማለቱን አንድ ልንል እንችላለን። የኢትዮጵያን አትሌቲክስ ለመደገፍ ሲያደርግ የነበረው ጥረት የኃይሌ ሌላ መገለጫ ነው። በነፃነት የመሰለውንና ያመነበትን ሐሳብ በመሰንዘርም ቢኾን የኃይሌ አስተዋጽኦ እንደ ምሳሌ የሚታይ ነው። “እባካችሁ አንድ እንሁን፣ ሰላም እንፍጠር” ብሎ በኢትዮጵያዊነት ስሜት በይፋ ሲናገራቸው የነበሩ ቁልፍ ነገሮች ብዙዎች የሚማሩባቸው ናቸው።
ታላቁ ሩጫን የመሰለ ድንቅ ሐሳብ ይዞ በመምጣት፤ ሩጫ የኢትየጵያ ባህል ስለመኾኑና በዚህም ኢትዮጵያን እያስተዋወቀ ያለበትን ተግባር በየጊዜው እያሳደገም ሔዶም በአፍሪካ ትልቁን የጐዳና ሩጫ አበርክቶልናል።
በአጠቃላይ ኃይሌ ኃላፊነት እንደሚሰማው አንድ ዜጋ ያደረጋቸውና እያደረጋቸው ያሉ ተግባራቱ ለብዙዎች የሚኾኑ፣ አገርና ዜጐችን በመጥቀም የሚገለጹ ናቸው።
ከሁሉም በላይ ግን በላቡ ያገኘውን ገንዘብ ለእኔ ብሎ ባለማስቀረት በኢንቨስትመንት መስኩ እያሳረፈ ያለው አሻራ ግን ፍጹም በተለየ ሊታይ ይገባል። ዛሬ ኃይሌ በተመረጡ የኢንቨስትመንት መስኮች እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ፤ ኢንቨስት በማድረግ ብቻ የሚገልጽ አይደለም። ከጠባብ አመለካከት ወጥቶ ሮጦ ያገኘውን ገንዘብ በአራቱም የአገሪቱ ክፍሎች የማዳረስ ሕልሙን እያሳካ ነው። ሁሉም የአገሬ ምድር ሁሉ የእኔ የኢትዮጵያዊው ነው ብሎ እየሠራ ስለመኾኑ እንገነዘባለን። ኃይሌ ሕንፃ በመገንባት አንድ ብሎ የጀመረው ኢንቨስትመንቱ ውጤታማ የተባሉ ቢዝነሶችን በመምረጥ እየሠራ ነው።
ዛሬ ኃይሌ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በሪል ስቴት፣ በእርሻ፣ በማዕድን፣ በተሽከርካሪ መገጣጠም፣ በኪነጥበብ ዘርፍ ውስጥ በመሰማራት፤ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እያፈሰሰ ለሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጐች የሥራ እድል በመፍጠር እየተጓዘ ነው። በሚዲያዎችና በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ኃይሌ ኢንቨስት አድርጓል።
ኃይሌና ዓለም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ኃይሌ ሪዞርት፣ ማራቶን ሞተርስ፣ ሃዮንዳይ መኪና መገጣጠሚያና በተለያዩ ስያሜዎች በሚጠቀሱ ኩባንያዎቹ ወደ አራት ሺሕ የተጠጉ ሠራተኞችንም ይዟል። በጥቂት ዓመታት ውስጥም የሠራተኞቹን ቁጥር አሥር ሺህ ለማድረስ እቅድ ይዟል።
የኃይሌን ኢንቨስትመንት ለየት ያደርገዋል ብለን ደፍረን የምንናገርበት ተግባሩ፤ በአገር ተስፋ ሳይቆርጥ መሥራቱና ኢንቨስትመንቱን በተለያየ የአገሪቱ ክፍሎች እያሰፋ ብቻ አይደለም፤ አጋጣሚ ኾኖ በሁለት አካባቢዎች የሚገኙ ኢንቨስትመንቶቹ እንዳልነበር ኾነው ሲወድሙበት፤ ተጐዳሁ ብሎ ሥራውን ያለመተዉ ጭምር ነው።
በደቡብ ክልል ቴፒ አካባቢ የሚገኘው የቡና እርሻውና የእርሻ መሣሪያዎቹ ወድመዋል። በሻሸመኔ ከአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ግርግር ሪዞርቱ እንዳልነበር ኾኖ ወደ 300 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ሲወድምበት፤ ያገዘው ባይኖርም ሥራውን ላለማቆም ኢንቨስትመንቱን ቀጥሏል። ከዚህ ውድመት በኋላ የአዳማን ሪዞርት እስከማስመረቅ ደርሷል።
ውጭ ባሉ ተግባራቱ እንድናስታውሰው ያደርገናል። በተለይ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ውስጥ እያሳደገው ያለው ቢዝነሱ በኩል፤ እግሮቹ አንድ ቦታ የተተከሉ ያለመኾንና ሁሉንም ክልሎች ታሳቢ ያደረገ ነው።
በሐዋሳ፣ ሻሸመኔ፣ ዝዋይ፣ ባሕር ዳር፣ አዲስ አበባ እያለ ሪዞርቶችን እያሰፋ ነው። አሁን ደግሞ ወልቂጤና ደብረ ብርሃን ቀጣዮቹ መዳረሻዎች ሲሆኑ፤ ላሊበላ፣ አክሱም እና ሌሎች የተመረጡ የክልል ከተሞች ላይ ዓይኑን ጥሎ ኃይሌ ሪዞርትን ይዞ ለመጓዝ እየተዘጋጀ ነው። ይህ ተግባሩ ዜጐች በፈለጉበት ቦታ ያለገደብ መሥራት የሚችሉ መኾኑን ያሳየ ምርጥ ኢትዮጵያዊ ያደርገዋል። ሁሉም አገሬ ነው ብሎ በመሥራትም ኃይሌ ምሳሌ ሊኾን መቻሉንም አሳይቷል።
ኃይሌን ጥሩ ሯጭ ብቻ ሳይኾን ምሳሌ የሚኾንበት ሌላው መገለጫው እንደ አንድ ጨዋ ኢንቨስተር ግብሩን በአግባቡ መከፈሉና ግልጽ የኾነ የሒሣብ አያያዝ በመተግበር መሥራቱ ነው። ምስጉን ግብር ከፋይ በሚል መሸለሙም ለዚህ ማሳያ ነው።
ሌላው በኢትዮጵያ እንደ ችግር የሚታየውና ምርት በማስመጣት ዕድሜያቸውን እንደጨረሱ ነጋዴዎች ያለመኾኑ ነው። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚኾነው ሃዮንዳይ የተባለውን ተሽከርካሪ በማስመጣት ሲሸጥ የነበረ ቢኾንም፤ አስመጥቶ በመሸጥ ብቻ ገንዘብ ከማግኘት፤ እዚሁ ገጣጥሞ የሞተር ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ በመነሳት፤ የሃዮንዳይ ተሽከርካሪዎችን እዚህ በመገጣጠም መሥራቱ ነው።
ይህንንም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ መገጣጠም ከፍ አድርጐታል። ሙሉ ተሽከርካሪ እዚህ የማምረት ውጥንም አለው። ኃይሌ በእርሻ ቡና ውስጥ አለ። በማዕድን ዘርፍ በወርቅ ላይ እየሠራ ነው። የተፈጥሮ ማራችንን ወደ ገንዘብ መቀየር አለብን ብሎም ገንዘቡን ኢንቨስት አድርጓል። በሌሎች ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ዝግጅቶች እንዳሉትም ይነገራል።
በተለይ ግን በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ ኢትዮጵያን ከማድረስ ባለፈ ድንበር ተሻግሮ ለመሥራት የሚያስችለውን እድል እያመቻቸም ነው። ኃይሌ ትናንትም በእግሩ አገሩን ያስጠራውን ድል፤ ዛሬ በእጁ ገንዘቡን እየመነዘረ የሚያደርጋቸው የኢንቨስትመንት ሥራዎች ለብዙዎቻችን አስተማሪ መኾን የቻሉ ናቸው ማለት ይቻላል። ዛሬ ኃይሌን በአትሌቲክሱ ብቻ የምናስታውሰው አይኾንም። ነገ ከነገ ወዲያ አሁን ካሉት ኢንቨስትመንቶቹ ባሻገር ሌሎችን በማከል ትልልቅ ኩባንያዎችን በመፍጠር ስመጥር ባለሀብትነቱን እንሰማለን። በቀየው ሳይወሰን ሁሉንም የአገሪቱን ክፍል በመድረስ ምሳሌ የሚኾን ኢትዮጵያዊ ባለሀብት ይኾናል። ከቢዝነሱ ባሻገር ግን ኃይሌ ሽማግሌም፣ አስታራቂም፣ በጐ አድራጊም መኾኑ ወደፊትም ኃይሌን ከትራኩ ውጭ ባሉ ተግባራቱ እንድናስታውሰው ያደርገናል።