ቫንኩቨር እየተሰናዳች ነው፤ ጀግናዋን ልታስብ፣ ለእስረኛዋ ልትመሰክር፣ የተገፉትንም ልትዘከር!
ቫንኩቨር እየተሰናዳች ነው፤ ጀግናዋን ልታስብ፣ ለእስረኛዋ ልትመሰክር፣ የተገፉትንም ልትዘከር
አሁን የምጣችን መሀል ላይ ነን። ይሄንን ለመረዳት ደግሞ “ጌታን መቀበል” የለብንም። ስለነጻነታችን፡ ሰዎች ይታሰራሉ። ስለ አንድነታችን ሰዎች ይገደላሉ። ስለ ፍትሀችንም ሰዎችም ይሰደዳሉ። አካላቸውም ተሰናክሎ ይቀራል። “እኛ ግን ምንም እንዳልተፈጠረ ሕይወታችንን እንቀጥላለን” ብለን ጽፈናል፤ ከዚህ በፊት። በርግጥ ክርስቶስ ስለሞተ፣ ነቢዩም ስላለፉ፤ አለም መሽከርከሯን አላቆመችም። እኛ ቫንኩቨራዊያን ግን ይሄንን መለወጥ፣ ይሄንን መገልበጥ፣ ይሄንን መነቅነቅ ሻትን። ሰዎች በተገደሉ፣ ሰዎች በተሰደዱ፣ ሰዎች በታሰሩም ጊዜ ሕይወታችንን ብቻ ከማሳደድ አለማችንን ብቻ ከማሽከረከር ባሻገር፤ አለማችንን የምናቆምበት፤ በጭፈራችን ውስጥ፣ በልደታችን ውስጥ፣ በስብሰባችን ውስጥ፣ በደስታችንም ውስጥ ሁሉ፤ እነዚህን የተሰዉትን፣ የታሰሩትን፣ የተሰደዱትን፣ አካላቸውም የተሰናከለውን የምናስብበት ቅጽበት እንደሚያስፈልግ አምነን። እነሆ ቫንኩቨር እየተሰናዳች ነው። ሙሽሮቿን ልታስብ፣ ሙሽሮቿን ልትዘከር። ለታሰሩት አጋርነቷን ልትገልጽ። የኢትዮጵያን ግዛት ካካለለው ሰፊው እስር ቤት ወደ ጠባቡ ቃሊቲ ወይንም ዝዋይ ያለፍትህና በበቀል የተዘጋባቸውን ልታስብ እየተዘጋጀች ነው።
አሁንስ የነኚህ ሰዎች ንቀት ጣሪያ ነካ። ቴዲ የመጀመሪያ አይደለም። ቴዲ የመጨረሻም አይደለም። ስንታሰር ኖረናል። ላልተወሰነ ጊዜም ስንታሰር እንኖራለን። ለዚህ ነው በምጣችን መሀል ላይ ነን ያልነው። እስራታችንን ለማሳነስ ከዚህ ከምእራቡ አለም የምንወረውረው ድንጋይ መለስ ዘንድ ባይደርስም እንኩዋን፤ የምንለግሰው ሞራል ግን ወዳጆቻችን ታጋዮቻችን ዘንድ ይደርሳልና፤ እዚያው ኢትዮጵያ ውስጥ የእስራታችንንም ቀንበር ለመስበር የሚታገሉትን ግን ከማሰብና ከማመስገን ከማበራታታም ወደኋላ አንልም። ታጋዮች ሲረሱ ያማቸዋል። ይጸጸታሉ። ቴዲ በዘፈኑ እንዲጸጸት አንፈልግም። ምነው ባልዘፈንኩ እንዲል አይሻም፡ ማህበረ-ቫንኩቨራዊያን። እንኩዋን ዘፈንኩ፤ እነሆ ትውልድ ሁሉ ያስታውሰኛል እንዲል እንጂ።የቴዲ መታሰር ልክ እንደ ኦባማ መመረጥ “Symbolic” ነው። የኦባማ መመረጥ ግን ለብዙዎች የባርነት ቀንበር የመሰበሩን፣ የቀለም መጋረጃ መቀደዱን፣ የእኩልነት ዳር መጀመሩን፣ የዘር መድለዎ ማብቂያ መቃረቡን፣ ያ ማርቲን ሉተር ኪንግ ያለመው የተራራ ጫፍ መድረሳቸውን ምሳሌ ያበስራል። የቴዲ አፍሮ መታሰርም፤ በተቃራኒው ቢሆንም ምሳሌያዊ ነው። ይሄ የተበላሸ ስርአት የሰዎችን ሀሳብ ለማፈን የት ድረስ እንደሚወርድ የሚያሳይ ነው። የነዚህን ሰዎች ቂመኝነትና በመንግስታችን ከመጣ ዘፋኝም ይሁን ቄስ፤ ለማኝም ይሁን መምህር፤ ህጻንም ይሁን አዋቂ አንተውም አመለካከት ያሳያል። ጠብ-መንጅ አነስተው ተኮሱብን፣ ቦንብ አፈነዱብን፣ ዘር አጠፉ ወይም ለማጥፋት ሞከሩ አንድ ነገር ነው። ሰው ዘፈነ ተብሎ እንዴት ይታሰራል። እንዴት ያለ የዴሞክራሲ ጥግ ላይ ደረስን ጎበዝ? “ደጉ ይገልጣልን ድጋሜ ገደሉት” አለ በቴዲ አፍሮ መታሰር ያዘነው አበበ በለው። ስለዚህም ነው የቴዲ መታሰር የዚህ ስርአት ወጥ መርገጥ ሌላ ምሳሌ ነው ያልነው። የታሰሩትን ማሰብ ደግሞ በሰማይም በምድርም መልካም ነው። ሰምታችሁ ጠግባችሁት ይሆናልና። ያንን የመጽሀፍ ጥቅስ አላነሳላችሁም። “ስታሰር አልጠየቃችሁኝም፣ ስታመም አልጎበኛችሁኝም፣ ስራብ አላበላችሁኝም …” ይመጣል።
ቴዲ አይሟሟም። ባይታሰር መልካም ነበር። ቢታሰርም ግን ቀድሞውን እስር ቤት ነው። የቴዲ ጀግንነቱም ኢትዮጵያዊነትንና ፍትህን የሚሰብኩ ዘፈኖችን መዝፈኑ ብቻ አይደለም። እነዚህን ሰዎች የሚናደፍ ዘፈን ዘፍኖ እዚያው እኛ በሰበብ አስባቡ ጥለናት ከሸሸነው ኢትዮጵያ ሙጭጭ ማለቱ ነው። ሰው ገደልክ ብለው ቢከሱትም እንኩዋን፤ እዚህ እምእራብ፣ ከእኛ ምኩራብ ሊቀር አልፈለገም። “ቀድሞውንም ከሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ጋር ታስሯል” አለ አንዱ ወዳጃችን። ልዩነቱ የአሁኑ እስር ቤት ጠበበ። ቴዲና ሀሳቡ፣ ቴዲና የዘመረለት ፍቅር፤ የዘመረለት የእኩልነትና የፍቅር ራእይ ግን አይታሰሩም። ያሳወቀኝ ያ ህዝብ ነው። ያከበረኝም ያ ምስኪን የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ከኢትዮጵያ ብርቅ ቀኟ ይራቀኝ ብሎ እዚያው አገሩ ከተመ። እስሩን አጠበቁበት። የሱንም የሌሎችንም ሞራል ለመንካት። የገረመንስ የዚህ ልዑል የሚባል የገብረማሪያም ሳይሆን የገብረ ሰይጣን ልጅ ነው። ልጆች የሉትም? ሚስት የለችውም? እቁብና እድር፤ ማሀበር የለውም? ጽዋም አይጠጣም? ነው ወይስ እቁቡን ወደነአላሙዲ አዞረ? መቼም እዚህ ቁጭ ብለን እንደው በደፉት አንልም። ግን ይሄ “ዳኛ” ሳይሆን መጋኛ ነው። ሽብርተኛ። ሕወሀት-ሰራሽ ሽብርተኛ። ሽብርተኛ ደግሞ በተገኘበት ዋጋ ይሰጠዋል። ይሄን መጋኛ በጸበልም ይሁን በመስቀል ለሚያጋጭልን ኢትዮጵያ ዛሬም ባይሆን አንድ ቀን ሽልማት ትሰጣለች።
ይህ የእስራት ጥግ ነው። እስከዚያው ግን ቴዲንም ይሁን ሌሎች ንጹሀንን ያሰሩ፣ የገደሉ፣ ያሰቃዩ፣ ወይንም በዚህ የመግደልና የማሰቃየት ሂደት የተባበሩ በሙሉ ለፍርድ እስኪበቁ፤ እነሆ የሁለት ሺህ አስር የኦሊምፒክ አዘጋጅ፤ ታላቋ ቫንኩቨር እየተሰናዳች ነው። ቅዳሜ December 27th 2008 ቴዲንና መሰል የህሊና እስረኞችን ለማሰብ፤ ለህሊና እስረኛዋ፣ ለሙሽራዋ አጋርነትዋን ልትገልጽ ላይ ታች እያለች ነው። ሁላችሁም ተጋብዛችኃል። ያደረሳችሁ ሁሉ ኑ። ኑ እና በቴዲና መሰል ዘፈኖች እንጫወት። እንድትመጡም ብቻ አይደለም አሁን ባያደርሳችሁም በያላችሁበት ሰልፋችሁን፣ ዝክራችሁን፣ እንደቴዲ ዘፈን “ኡኡታችን” እስኪሰማ ኡኡታችንን እንድንቀጥልም ጭምር እንጂ። በድግሳችሁ ሁሉ ቴዎድሮስን አሰቡት። ይሄ ምክንያትም ነው። እንደ ኦባንግ፤ እንደ ኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ያሉ ድርጅቶችን ለመርዳት መልከም አጋጣሚም ነው። ያም ብቻ አይደለም። ሕዝባዊ ወያነ አርነት ትግራይ እንዲህ ያለውን ስራ እስከገፉበት፤ እኛም አንተኛም፤ ብንተኛም አናንቀላፋም፣ ብንጨፍርም ቴዲንና መሰል የህሊና እሰረኞችን አንረሳቸውም ለማለትም ጭምር ነው። ቫንኩቨራዊያን። በቴዲም ይሁን በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እስራቱ በጠበቀ ቁጥር እኛም ቴዲንና መሰል እስረኞችን የጀግና ማእረግ እንሰጣቸዋለን። የአርበኝነት። የትግላችን ፊታውራሪነት። ቫንኩቨራዊያን።



