“ሒደት ነው”
ሩት አማኑኤል
ተደጋግሞ የሚነገር አንድ ጉዳይ አለ። ዴሞክራሲ ሒደት ነው፤ መልካም አስተዳደር በሒደት የሚመጣ ነገር ነው፤ የዴሞክራሲ ተቋማትን መገንባት ሒደት ነው ወዘተ. ይባላል። ለጽሑፌ መነሻ የሆነኝ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ንግግር ነው።
አቶ ኃይለማርያም ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር (እሑድ ኅዳር 19 ቀን 2008 ዓ.ም.) ባደረጉት ቃለምልልስ ስለመልካም አስተዳደር ተጠይቀው ሲመልሱ ”... የመልካም አስተዳደር ችግር በሒደት እየተገነባ የሚሄድና አፈታቱም ቢሆን ኅብረተሰቡ ራሱ ተሳትፎበትና ባለቤት ሆኖበት የሚፈታ ጉዳይ እንጂ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ስለተሰበሰቡ ብቻ የሚፈታ ተደርጎ መውሰድ የለበትም።” ብለው ነበር።
ይታያችሁ፣ ኢሕአዴግ ከአጼ ኃይለሥላሴ አገዛዝ ቀጥሎ ለረዥም ጊዜ አገሪቱን የገዛና አሁንም በሥልጣን ላይ ያለ አገዛዝ ቢሆንም ባለፉት ሃያ አራት ዓመታት ውስጥ የዴሞክራሲ ጭላንጭል እየሰፋና እያበበ ከመሄድ ይልቅ እድገቱ ቁልቁል ሆኖ ሳለ ስለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሒደትነት ሲነገረን። አዎ፣ ዴሞክራሲ ሒደት ነው። ሒደት ነው ማለት ግን ተጀምሮ በየጊዜው እያደገና እየጠነከረ ይሄዳል ማለት ነው እንጂ እንደ ዘመነ ኢሕአዴግ ዴሞክራሲ አድሮ ቃሪያ ይሆናል ማለት አይደለም። አዎ፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን መገንባትና ማጠናከር ሒደት ነው፤ ጊዜ ይጠይቃል። ሒደት ነው ማለት ግን መንግሥታዊ ተቋማት የአገዛዙ የመጋለቢያ መሣሪያዎች ይሆናሉ፣ አገዛዙ ተቀናቃኞቹን ለማኮላሸት የሚጠቀምባቸው የአፈና መሣሪያዎች ይሆናሉ ማለት አይደለም። አዎ፣ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ሒደት ነው። ሒደት ነው ማለት ግን እስኪበቃን እንዳየነው የአምባገነኑ ሥርዓት ባለሥልጣናትና ተላላኪዎች የሳምንት ወይም የወር የዘመቻ ሥራ ነው ማለት አይደልም።
አምባገነኖች ስለ ሒደት ማውራት ይወዳሉ። ኢሕአዴም እንደ አንድ አምባገነን ድርጅት ይህንኑ ጉዳይ መልሶ መላልሶ ሲወቅጠው እየታዘብን ነው። ”ከጸረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ የተላቀቅነው በቅርቡ ነው፤ የጸረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዙን ቅሪት አስወግዶ ዴሞክራሲን መገንባት ከባድ ነው፤ እኛ ግን ከመጀመሪያው ጀምረን ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው ብለን ስለምናምን ሒደቱን ጀምረናዋል፤ ይሁን እንጂ ዴሞክራሲ ሒደት የሚጠይቅ ነገር በመሆኑ የጀመርነው ዴሞክራሲ አሁንም ጮርቃ ነው፤ ለጋ ነው፤ ስለዚህ ቀጣይ ሥራችን ይህን የጀመርነውን ዴሞክራሲ የትምክህትና የጥበት ኃይሎች እንዳያኮላሹትና አገራችንን ለብተናና ትርምስ እንዳይዳርጓት እነሱን እየታገልን መቀጠል ነው።” ይባላል፤ ይደጋገማል - በአገዛዙ በኩል።
ይሁን እንጂ ደግሞ አገዛዙ በሙስናና በዘረፋ እስከ አንገቱ የተዘፈቀ ነውና ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር ጨርሶ እንደማይፈልግ በጣም ግልጽ ነው። የእስካሁኑ ድርጊቱ የሚመሰክረውም ይህንኑ ሐቅ ነው። ዜጎች ደልቷቸው ጉቦ ይሰጡ ይመስል አቶ ኃይለማርያም ለባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ”ቢያንስ ጉቦ አትስጡ፤ ጉቦ የሚሰጥ ከሌለ ተቀባይም አይኖርም” የሚል ከንቱ አስተያየት መስጠታቸውን አስመልክቼ ባለፈው ሳምንት ጽሑፌ አንዳንድ ነገሮችን አንስቼ ነበር። እኝህ ሰውየ አሁን ደግሞ መልካም አስተዳደርን ስለማስፈን ሒደትነት ሊያስተምሩን በከንቱ ሲባክኑ እያየን ነው። ሒደትነቱ መቼ ጠፋን። የኛ መነሻ ሒደቱ አልተጀመረም ብቻ ሳይሆን የመልካም አስተዳደር ችግሩ ምንጭ አገዛዙ ራሱ በመሆኑ ከቶም ሊጀምረው አይችልም የሚለው ነው። የኛ መከራከሪያ አገዛዙ የፖለቲካ መሠረት ጥቅም ነውና መሠረቱን የሚንድ ሥራ አይሠራም፤ የሚባለው ሁሉ ማስመሰል ነው የሚለው ነው። ግልጽ ነው?
ምንጭ፡ የቀለም ቀንድ



