ታሪክ መዛባቱ አያከራክረንም! ለመሆኑ ማን ነው ያዛባው?
ዩሱፍ ያሲን (ኦስሎ)
በቅርቡ ኤርትርያን የጎበኙት የኢሳት ጋዜጠኞች ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ ጋር ያደረጉትን ቃለምልልስ ብዞዎቻችንን እያነጋገረ ነው። እንደገና የሁለቱ አገራትና ሕዝቦች ዝምድናና የወደፊቱ እጣ ተጣማሪነት በተለያዩ ሚዲያዎች መነጋገሪያ አጀንዳ እየሆነ መጥቷል። ልክ እንደ በፊቱ እያወዛገበ ነው ማለቱ ሳይሻል አይቀረም።
የኢሳት ጋዜጠኞች በኤርትራ ጉዞአቸው ሌሎቹ ተጨማሪ ተልእኮዎች ነበሯቸው። እነሱንም አሳክተው ነው የተመለሱት። ዋናው ተልእኳቸው አድርገው የሄዱትን በኤርትራ በኩል የትጥቅ ትግል ላይ የተሰማሩትን ኃይሎችን ሁኔታ፣ ይዞታና እንቃስቃሴ በሰፊው ዳስሰው ለኢሳት ተመልካችና አድማጭ በተለይ፣ ለኢትዮጵያዊ በጥቅል በማሳወቅ ላይ ናቸው። የኤርትራ ሕዝብ አኗኗር ሁኔታንም ተመልክተው በዲያስፖራ ለሚገኘው ሕዝባችን እያካፈሉ ናቸው። ከፕሬዝዳንቱ በተጨማሪ ሌሎች የአገሪቷ ባለሥልጣናትንም ማነጋገራቸው ታውቆአል። እነዚህን ርዕሰ ጉዳዮች ሁሉ ይህ ጽሑፍ አይመለከታቸውም።
ለጊዜው ትኩረቴ በፕሬዝዳንቱ ቃለምልልስ ላይ ነው። ከእሱም ውስጥ በተለይ ያነጣጠረው በታሪክ "መዛባቱ" ጉዳይ ላይ ነው። እንዲያውም ጠበብ አድርጎ ፕሬዝዳንቱ የኤርትራና ኢትዮጵያ ሕዝቦች ትስስር አስመልክቶ የሰጡትን ረዥም ማብራሪያን ነው ቢባል ያስኬዳል። "ምዝንባዕ" የሚትለዋን የትግርኛ ቃል ብዙ ጊዜ ተደጋግማለች በፕሬዝዳንቱ ቃለምልልስ ውስጥ። እንዲያውም በእንግሊዘኛው የቃለምልልሱ ክፍልም "Distortion" አዝማችና ተዘውታሪ አባባላቸው ነበር። ትርጉሙ "መዛባት" ነው ወደ አማርኛ ሲመለስ።
ማኛውም ተገንጥሎ አዲስና ነፃ አገር የመመሥረቱ ውጥን "የተለየ ማንነት ባለቤቶች ነን" ነው ሥርወ መሠረቱና ውልደቱ። አዲስ ማንነት ለይታው ደግሞ አንዱን የማንነት መገለጫ መካድና ሌላውን ማንነት መገለጫ ወይም ዝምድና ማረጋገጥ ሂደት ነው ተብሏል። ተገንጠለው አዲስ አገር ለመመሥረት ከሚገነጠሉባት አገር የግድ ዝምድናም ሆነ ታሪካዊ ትስስር ፈፅሞ የለንም ማለት የተለመደ አካሄድ ነው። የኤርትራ ነፃነት ትግልም ከዚህ ያፈነገጠ ሂደት ከቶ ሊሆን አይችልም።
በቅድሚያ የግድ ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ራሳቸውን "ነፃ ማውጣት" ነበረባቸው ማለት ይቀላል። ስለዚህ ለመዛባቱ ነበራዊ ምክንያቶች ነበሩ ለማለት ነው። "ብሔረተኛነት" በመሠረቱ የተለየ ማንነትን መገለጫዎችን ተንተርሶ የራስን መንግሥት የመቀለስ አይዲዮሎጂና እንቅስቃሴ ነው ቢባል እምብዛም ማጋነን የለበትም። የመገንጠል ጥያቄ አንግበው ለሚነሱ ወገኞች ይህ ሂደት ተፍጥሯዊ ነው። የተለመደ የነፃነት ፍለጋ ትግል አንዱ አካል ነው። ስለዚህ ታላቁ መዛባት ኤርትራ "በረዥም ታሪኳ ራሷን በቻለ ሕልውናዋ" ከጎረቤት ኢትዮጵያ ጋር ምንም ዓይነት ትስስር ሳይኖራት የዘለቀች አገር ነበረበች ትረካ መሠረቱ ይኸው ነው። ስለዚህ ትስስሩና ዝምድናው መካድ ነበረበትና ተካደ፣ ባጭሩ። ኢትዮጵያ የመጨረሻዪቱ የኤርትራ ቅኝ ገዢ አገር ነበረች ትረካ ቦታውን ተካ። በዚሁ ኤርትራ የቅኝ ገዢዎች ፍርርቆሽ ታሪክ መሠረት በቱርክ፣ በግብፅ፣ በጣልያንና በእንግሊዝ ተራ በተራ ከተገዛች በኋላ የመጨረሻዪቱ የኤርትራ ቅኝ ገዢ አገር ኢትዮጵያ ነበረች ነው።
የዛሬን አያድረገውና "ሐበሻነት" ሲያልፍ አይነካካንም ዓይነቱ ዓይኔን ግንባር ያድርገው ትረካውም ግልብ የዓረብ አሚሮችን ማሞኛ ማታልያ በዚህ ማዛባት ስር ሊጠቀስ የሚችል ታሳቢ ነው። ሟቹ አቶ መለስ ዜናዊም ለሙዓመር አል-ጋዳፊ በትውልዱ የየመን ዓረብነት ዝምድናው ያረጋገጠው ይህንን ዱካ ተከትሎ ነው። የዛሬ አያደረገውና "ኮሌጅ ከመግባት ይልቅ ስምነት ሰዓት ከኢሳያስ ጋር ማሳለፉ ይበልጣል" ያለውም በዚያ ትፍ ትፍ በሚያስብለው ፍቅራቸው ወቅት ነበር።
የኤርትራ ብሔረተኛው እንቅስቃሴ ኤርትራውያኑን ከኢትዮጵያዊ ማንነት ራሳቸውን እንዲያገሉ ማድረግ ቀዳሚ ተግባሩ ነበር። "እኛ ኤርትራውያን እንጂ ኢትዮጵያውያን አይደለንም ነው" የክርከሩ መነሻ። የራቢጣ እስላሚያው መሪው ሼክ ኢብራሂም ሡልጣን በ1949 (እ.ኤ.አ) በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መድረክ ላይ ከሰጡት ማብራሪያ አንስቶ የብሔረተኛው እንቅስቃሴ እንደርዳሪ ኃይሉ "እኛ ኤርትራዊያን፣ በረዥሙ ታሪካችን የኢትዮጵያ ታሪክ አካል ሆነን አናውቅም" ነው፤ በየዓለም አቀፍ መድረክ ክርክሩና እሰጣ-አገባው። በ30 ዓመቱ የነፃነት ተጋድሎ ዘመን የተደረገው የርዕዮተ-ዓለሙ ማጠንጠኛ ይኸው ነበር። የብሔረተኛ እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ ከዚያ በፊት ወደ እናት አገራችን ኢትዮጵያ ጉያ እንመለስ ብለው ለተ.መ.ድ. ጠያቂ ቡድን ከኢትዮጵያ መቀላቀል ፍላጎታቸውን ያረጋገጡትም ወገኖች ጭምር ለዚህ ዓላማ ከጎኑ ማሰለፍ ቻለ ማለት ነው። በመሠረቱ በዚህ ሂደት ብሔረተኛው እንስቃሴ ታሪክን ሁለት ጊዜ ነው ያዛባው። አንዴ በነፃነት ትግል ወቅት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ነፃነት እወጃ ማግስት። በመጀመሪያው ጊዜ የነፃነት ትግሉን ሕጋዊነት ለማላበስ ተብሎ፣ ሌላው ጊዜ ደግሞ የአዲስቷ አገር ነፃ አገራዊ ሕልውናን ለማረጋገጥና የግድ አዲስ አገራዊ ማንነት ለማስረፅ ሲባል። ይህ በአገሮች ግንጠላ ታሪክ ያልተለመደ አካሄድ አይደለምም፣ አልነበረምም።
የታሪክ መዛባቶች መኖራቸው ከተቀበልን ዘንዳ ቀጣዩ ጥያቄ፣ "ለመሆኑ ማን ነው ታሪክን ያዛባው ነው?" የሚሆነው፤ እንዴት? የትኛውን ዓላማ ለማሳካት? እንደ ወትሮው በርካታ ጥያቄዎች መግተልተላቸው አይቀሬ ነው። እውነት እነዚህ የታሪክ ማዛባቶች ናቸው በሁለቱ መንግሥታት ብሎም ሕዝቦች መሃል መልካም ጉርብትና ግንኙነት እንዳይኖር ደንቃራ ሆነው አሁንም የሚያስቸግሩን? ላለመግባባቶቻችን መሠረት የሆኑት? እነሱን ከመንገዳችን አስወግደን ማለፊያ በይነ-መንግሥታት ትስስር እንዴትስ ነው የምንፈጥረው? የኤርትራ ፕሬዝዳንት ለምን በአማርኛ አልተናገሩም? ለምን ስለ አስተዳደጋቸው፣ ስለ ቤተሰብ ሁኔታቸው በሚገባ አልገለፁም? ... ዓይነቱ ጉንጭ አልፋ ክርክር ውስጥ መዘፈቅ አይዳዳኝም። ግን ስለ ድርጅቶቹ ምስጢራዊነትና ስለ መሪዎቻችን ማንነት አደባባይ የማይወጡ መገለጫዎች እንደ አንድ የግርጌ ሕዳግ ጣል ማድረጉ አይከፋም። ወደ ጽሑፉ ማሳረጊያ ላይ እመለስበታለሁ።
ባጭሩ ሲጠቃለል፣
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ምንም ትስስር ኖሯት አያውቅ፣
ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ-ግዛት ነበረች፣
ከትግራዊ ኢትዮጵያውን ጋርም ዝምድና የለንም፣
ሐበሻም አይደለንም፣ ዓረብ እንጂ፣ ...
ብለው የሚያስተጋቡ መመሪያዎች በዚያን ጊዜ እንደ አንድ የትግል መሣሪያ የተወሰዱ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያውያን ጋር የነበራቸው ትስስር የመካዱ ስር የሚካተቱ ዋናዎቹ የብሔረተኛው ወገን ድርጊቶች ናቸው ለእኛ የታሪክ መዛባቶች ሆነው የሚታዩት። ስለዚህ ክቡር ፕሬዝዳንት! ታሪክ መዛባቱ አያከራክረንም! ነገር ግን አንድ ጥያቄ መልሱልን ለማለት የምንገደደው። ለመሆኑ ታሪክን ያዛባው ማን ነው? እነዚህን በመሰሉ የሕዝቡን ማንነት "የሚያዛቡ መዛባቶችን" ሲገፋ የነበረው ማን ነው? እነዚህ "ማንነት ያዛቡ" ታሪኮች ናቸው የሁለቱ ሕዝቦች ግንኙነትን "ያዛቡትም" አልፎ ተርፎ የመረዙት ከሚለው ግንዛቤ ነው አነሳሴ።
እነዚህን አባባሎች ገባ ብለን እንመለከታቸው፣ እስቲ። ለዓረቦች ኢትዮጵያ እንደ አገር መጠሪያ ስሟ ሐበሻ ወይም አል-ሐበሻ ነው። ሌላ ትርጉም የለውም። ከታሪክ መዛግብት እንደምንረዳው፣ ከቅድመ እስልምና ጊዜ የነበራት ስያሜ ነው። አሁን በቅርቡ በወጣው ISIS የወደፊቱ ሙስሊማዊ ካሊፌት ካርታቸው ላይ ከሱዳን፣ ከሶማሊያና ኤርትራ ጋር ባንድ ላይ ምድረ ሐበሻ (አርዳል-አልሐበሻ) በተሰኘው እንደ አንድ ትልቅ አድያም (ወላያ) ወይም ክፍፍል ነው የተከለለችው። በነፃነቱ ትግሉ ዘመን ዓረብ አገሮች "ሐበሾች ነን"፤ ነገር ግን "ከሐበሻ ቅኝ ግዛትነት" ነፃ አውጡን ብለው እርዳታ መጠየቁ አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው አያጠያይቅም። ግራአጋቢነቱም ያቺ በነፃነት አከባበር ዕለት ላይ ላቧ የተንጠፈጠፈ ከበሮ እየደለቅች ፀሐፊ ተስፋዬ ገብረአብ አግኝቷቸው ያን የመሰለ ፍንደቃቸው ምክንያት ሲጠይቋቸው "ከኢትዮጵያ" ነፃ የወጣንባት ዕለት በመሆኑ ነው" ያሉት የአሥመራ ወይዝሮ ታሪክ ያስታውሰኛል።
ጋዘጤኛው "እናቴ! ስሞዎትን ማን ልበል" ብሎ ላከታተለው ጥያቄ ግን ምንም ሳያንገራግሩ ፈርጠም ብለው "ኢትዮጵያ! ነዋ" በማለት የሰጡት መልሳቸው ፈገግ ከማድረጉ በላይ፣ "ቁጥርጥር" ያለው የአካባቢው የማንነት ግራአጋቢነት ገላጭ ነው። ይህ ዓይነቱ የማንነት ግብግብ ነው እንግዲህ ፕሬዝዳንት ኢሳያስን ከሲዳማ ነፃ አውጪ መሪ ከነበሩት ከሟቹ ከወልደአማኑኤል ዱባሌ ጋር በኢትዮጵያ ታሪክና ዲሞክራሲ ጉዳይ በ1986 በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ክፉኛ አፋጥጦ ግብግብ ያስገጠማቸው። ምስክርነቱን የሰጠው የኤርትራ ሕዝባዊ ሓርነት ግንባር (ኢ.ፒ.አል.አፍ) የቀድሞ ታጋይና የስለላ መረቡ የቀድሞ ተወካይ የነበረው የማነ ተክለጊዮርጊስ ነው። ባለታሪኩ በ21 አውዲዮ-ካሴት በአሰና ራዲዩ በተሰራጨው ረዥም የትግል ታሪኩና ስለ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የሰጠው መግለጫ እምብዛም አውንታዊ ገፅታ የተላበሰ ባይሆንም ቅሉ "እኔ የምመለከተው የኢትዮጵያንና በአገሪቷ ዲሞክራሲ የማስፈን ጉዳያችን አይደለም፣ የሲዳማ ነፃ ማውጣት እንጂ" የሚለውን የአቶ ወልደአማኑኤልን ክርክር በብርቱ እንደመከቱ ይመሰክርላቸዋል።
አቶ ኢሳያስ "ግንባራችን ኢትዮጵያን የመበታተን ዓላማ የለውም" በማለት ፈርጠም በማለት ነገሯቸው ይላል አቶ የማነ። እንዲያውም ቃል በቃል "ኢሳያስ ሊያብድ ነበር" ይላል (10ኛው አውዲዮ ከደቂቃ 55፡16 ጀምሮ)። የቀድሞ የስለላ ወኪልና የዚያን ጊዜ ግንባሩን ከኋላ የሚያሽከረክረው የኅቡዕ የኤርትራ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ አባል የምስክር ቃሉን ሲሰጥ። ስለዚህ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ "የትግራይ ነፃ ሪብፕሊክ ምሥረታን አልተቀበልንም" አባባላቸው፣ እኔም ለመቀበል አላንገራገርኩም። ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ስብስቦች የራሳቸው መንግሥት ምሥረታ ውጥን የማይቀበሉበት ተጨማሪ ምክንያት እንደነበራቸው ልብ እንበል። ሁሉ ነፃ አውጪ ተብሎ ነፃ መንግሥታት ምሥረታ ትግል ካፋፋሙ የኤርትራ ጥያቄ ዋጋ ያሳጣዋል። ይራከሳል እንበል! ባልረቀቀ ቋንቋ። ያጉዳያቸው ልዩ ጥያቄና ከብሔራዊ ጥያቄዎች ጋር አለመመሳሳሉን አጠያያቂ ያደርግባቸው ነበር፣ በሌላ አባባል። ለወዲ አሥመራ የትግራዊ ሪፐብሊክ ሆነ የሲዳማ መንግሥት ምሥረታ ፍላጎት "ከኤርትራውያኑ ጋር የመወዳደር ከማን አንሼ ማንጠራራት" ተደርጎ ቢወሰድ አይገርመኝም። ለመቀበል የሚያስቸግሩን የአቶ ኢሳያስም ሆነ የአቶ የማነ ትርክቶች ግን በርካታ ናቸው።
ለምሳሌ የ10 ዓመት የሽግግር ጊዜ ጠይቀን ነበር፤ ባንዱ ወይም በሌላው የመንግሥታዊ ቁርኝት እንጣመር ብለን፣ ወያኔ እምቢ አለን ዓይነቱ አባባሎች ለማመን ያስቸግራሉ። የማንቀበለውና የማይዋጥልንን ለይተን በምክንያታዊነት እንጂ በጥላቻም ሆነ የሰሞነኛው ደርሶ የኤርትራ ትግልና የፕሬዝዳንት ኢሳያስን አትንኩብን ባይ ጥብቅናም ሆነ የፕሮፌሰር ሙሴ ተገኝ አሥመራ ደርሶ-መልስ ተሞክሮ ምሬት ስሜታዊነት ቦታ ሊኖረው አይገባም። "አሰባሳቢ ማንነት ባንድ አገር ልጅነት" መጽሐፌ ውስጥም አልፎ አልፎ እነዚህ የማንነት አወሳሳቢ ታሳቢዎችን በመጠኑ ተዳስሰዋል። ለመጽሐፌ ማስታወቂያ እያደረግኩ አለመሆኔን ይታወቅልኝ፤ ሐረግ መጨመር ሊያስፈልግ ነው መሰለኝ!። ከዚህ በተጨማሪ ዓለምሰገድ ዓባይና የኖርዌይ ተወላጅ የሆነው ሸቲል ቱሮንቮል በኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ወቅት በሁለቱ ትግሪኛ ተናጋሪዎች ማለት ትግራዊ ኢትዮጵያውና ትግርኛ ስብስብ ነኝ ባዩ ኤርትራዊ ብሔረሰብ መካከል በተለያዩ የትግሉ ወቅቶች የታዩትን የማንነት መለዋወጦች አጥንተው የምርምራቸው ውጤት አቅርበዋል።የሁለቱም መጽሐፍት ርዕሶች በግርጌው መልክተዋል።
ገና ገና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከዓረቦች ጋር ሳይገናኙ፣ ዛሬ በሚያስገርም ሁኔታ የሚያቀላጥፉት ዓረብኛም ሳይማሩ ገና ገና ድሮ ለወታደራዊ ትምህርት ከተላኩበት ቻይና ሳይመለሱ እነ ዑስማን ሣሊሕ ሳቤ አይገቡ ገብተው በኤርትራ ዓራባዊ ማንነት የዓረብ አሚሮችና ርዕሳነ መንግሥታት ድጋፍና እርዳታ ይሸምቱ ነበር። የሻዕቢያ ወታደራዊ ክንድ የፈረጠመውም በዚሁ ማቴሪያልና የገንዘብ እርዳታ አማካኝነት ነው ቢብላ እምብዛም ማጋነን የለበት። ይህ እንደ ተጠበቀ ሆኖ 25 ዓመታት ከነፃነት እወጃ በኋላም ኤርትራ እንደ አገር የዓረብ ሊጉ (ራቢጣው) ተመልካች አባል እንጂ ሙሉ አባል አልሆነችም። ሌላኛው የኤርትራ የማንነት ለዕይታ ያወሳሰበው ወገንተኛነት አሰላለፍ እንበለው!?
ቅኝ ተገዢዎች እንጂ ኢትዮጵያውያን አይደለንም፣ ጥያቄያችንም ቅኝ ግዛታዊ ነው ብቻ ሳይሆን ከእኛ ጋር አብሮ ለመታገል ይህንን የጥያቄያችን ባሕርይ መቀበል የግድ ነው ባዮች ነበሩ፣ የሻዕቢያ መሪዎች በዚያን ጊዜ። መለስ ዜናዊና የትግል ጓዶች ይህንን ተቀብለው ነው ድጋፍና ትብብር የተለገሳቸው። ይህንን መቀበል አሻፈረን ያሉትማ ድጋፍና ትብብር ተነፈጋቸው። ይባስ ተብሎ ወያኔና ሻዕቢያ ባንድ ላይ በመሆን ተዋጓቸውና ከትግል ሜዳ ውጭ አደረጓቸው። በዚህ ድግግፎሽ ሁለቱም ዓላማቸውን ለማሳካት ስለበቁ ሁለቱም ተጠቃሚዎች ነበሩ። win-win situation ነው የምትሉት! ይህ ብቻ አልነበረም። ከነፃነት በኋላም ባንድ ላይ የሚያጣምራቸው የጋራ አንገብጋቢ ግቦች ነበሯቸው። ሻዕቢያ በዓለም መድረክ ለአዲስቷ አገር ነፃነት የኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና ማረጋገጥ ነበረበት። ሌላ ምክንያትም ነበረ። ከእነሱ ድርጅት ሌላ ማንም ኤርትራዊ ድርጅት እውቅና እንዳይሰጠው ፍላጎት ነበራቸው። 1991 ለአዲስ አበባው የሰኔ የሽግግር ኮንፊረንስ ኢሕአፓና የመኢሶን መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የኤ.አል.ኤፍ አንጃዎች መሪዎችም ያልተጋበዙት እንበለ ምክንያት አልነበረም። ወያኔ/ኢሕአዴግ በሚገባ መሬት ሳይቆናጠጥ ከቀድሞ የትግል አጋሩ አለመግባባት መፍጠር አይፈልግም ነበር። እነዚህ ታሳቢዎች ብዙ የሚያነታርኩ ጉዳዮች አይመስሉኝም።
እመለስበታለሁ ያልኩትን አደባባይ የማይወጡ የድርጅቶች መሪዎች ማንነት መገለጫዎች አልዘነጋሁም። ልከ እንደ ትናንቱ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን የእናታቸው ስም (የሺእመቤት ዓሊ ጋንቾ ፈረዶ?) እንኳን በትክክል በይፋ ሊታወቅ ቀርቶ የአገር ሕልውና-ነክ ምስጢር መስሎ ይታይ እንደ ነበረ ሁሉ፤ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ራሳቸው ሆኑ የእናታቸው ዘመዶች ከትግራዊ ጋር የሚያቆራኛቸው የስጋ-ውልደት ዝምድና አሁንም የተጠቀሰ ነገር የለም። በተቃራኒው የሟቹ የመለስ ዜናዊ እናት ኤርትራዊነትና የሠራዬ አውራጃ ተወላጅነት አገር ያወቀው የአደባባይ ምስጢር ነው። አብራሃም ያዬ የዛሬ ስንት ዓመት በፊት እሱ ከመረብ ሻገር ካለው ሠራዬ አውራጃ ብቻ ሳይሆን ከሦስቱ የኤርትራ ከበሳ ወይም ደጋ አውራጃዎች ከተለያዩ ግለሰቦች ጋር ያላቸው ጥልፍልፍ ያለ ማን ማን ቢወልድ የስጋና የደም ውህደት በግራፍ መሰል አገላለጽ በትግርኛ ከሽኖ አስነብቦናል። አባይ ስብሓትም ኤርትራዊ ቁርኝታቸውን አልደበቁም ወይም አላፈሩበትም ልበል። በተቃራኒው የኤርትራ ቁንጮ ባለሥልጣናት መረብ-ሸገር ትውልድ ሐረግ እንደ መንግሥታዊ ብቻ ሳይሆነ እንደ አንድ የአገር ሕልውና ምስጢር ዛሬም በአሥመራ በሽኩሽኩታ ነው የሚወሳው። አይገርምም! ይቺ ደግሞ ዓቢይ መነገገሪያ ጉዳይ ሆና ነው እንደማትሉኝ ተስፋ አለኝ። ግልፅነት የክፍት ሕብረተሰብ አንዱ መለያ መታወቂያ ነው። በዚህ አካባቢ የምንመለከተው የግራአጋቢው የማንነት ልውውጦች ማሳያም ጭምር ነው።
በመጨረሻ ይህንን የሁለቱን ሕዝቦች፣ እደግመዋለሁ ሁለቱን ሕዝቦች የወደፊት ትስስርና የሁለቱ መንግሥታት የወደፊቱ አዘቦታዊ በይነ-መንግሥታዊ ግንኙነት ያሰናከለው የታሪክ "መዛባት" ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ በቃለምልልሱ እንደሚያረጋግጡት እውነት የሚገባ የተሰነደ ታሪክ ከሆነ እዳው ገብስ ነው። "መዛባቱን" የማጥራቱ ቀዳሚው ተግባር ለተመራማሪ ፈታሽነት ለባለሙያዎቹ ማቅረብ ብቻ ነው። መቼም እስካሁን የሰንዶቹ የምስጢራዊነት ይርጋ ዘመን ይገባደዳል በሚል ተስፋ በመሰነቅ ነው። እነዚህን ሰነዶች ለታሪክ ተመራማሪዎች ክፍት ማድረግ ነው። በዚህ ምርምር መንግሥት አወዳሽ ምሁራን ጎን ለጎን በሂስነታቸው የሚታወቁትን ፕሮፌሰር ተከሰተ ነጋሽ፣ ተስፋፅዮን መንግሥቱ የመሳሰሉ ምሁራን መጨመር ሊያስፈግ ይችላል። ውጤቱ ተዓማኒነት እንዲላበሰ ከተፈለገ ማለቴ ነው።
በሕዝቦች መካከል ዘላቂ ትስስር አለ። በሥልጣን በተደላደሉ መንግሥታት መካከል ግን ለትስስሩ መንስኤና መነሻ ስትራተጂካዊ ጥቅማጥቅሞች ናቸው። በሁለት ድርጅቶች መካከል የነበረው በጋራ ጠላቶች ላይ የጋራ ክንዳቸውን በማሳረፍ ውለታ የመዋዋል ግንኙነት ታክቲካዊ ነበረ። ግንባሮቹም አይክዱም። ብዙ ውጣ ውረዶች ነበሩበት። ይህንን ሐቅም አይክዱም። ከ1975 ጀምሮ እስከ አሥመራና አዲስ አባባ በድል መግባቱ ድረስና ከዚያም በኋላም። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የሁለት ነፃ አውጪ ድርጅቶች ፀረ ደርግ ቃልኪዳና "እኔ ነኝ ውለታ የዋልኩልህ፣ እኔ ነኝ እንጂ የዋልኩልህ" ግራንጃና እሰጣ-አገባ ለዚያኑ ጊዜው የጦር ኮማንዶሮቻቸው መተው ሳይሻል አይቀርም። እነሱ ይወዛገቡበት። በቅርቡ ሜጀር ጀነራል ፃድቃን የሰጠውን ቃለምልልስ ይመለከታል። እኛ ጉዳያችን የወደፊቱ የሁለት ሕዝቦች ትስስር "ሊያዛባ የሚችለውን የታሪክ መዛባት" ነቅሶ ማውጣት ነው ብለናል።
አሁንም የምናወሳው ስለ ሁለቱ ነፃ አውጪ ድርጅቶች ማለት ወያኔና ሻዕቢያ የጋራ ትግል ታሪክ፣ ትስስርና ውዝግብ እንጂ ከሰማኒያ በላይ ስለ ሆኑት የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችና ዘጠኙ የኤርትራ ማሕበረሰቦች ግንኙነትና ታሪክዊ ትስስር እንዳልሆነ መዘንጋት የለበትም። ግፋ ቢል ስለ ሁለ መረብ ዳርቻ ስላሉት ሁለቱ የትግርኛ ተናጋሪዎች ታሪክ መዛባት ነው። ተወደደም ተጠላም ወሳኝ ሚና ያላቸውም አሁንም በመረብ ወንዝ ዳርቻ ያሉት ትግራዊና ትግርኛ ስብስብ ትስስር ብቻ መሆኑን መሰመር ያለበት ሐቅ ነው። ይህም ሌሎቻችን መቀበል ያለብን መራራ ሐቅ ይመስለኛል። የታሪኩን መዛባት ለማስተካከል ብቻ ሳይሆን ዘላቂው ሰላምና መልካም ጉርብትናም ሆነ ማለፊያ የወደፊት ቁርኝት ወሳኙ የሁለቱ ማለፊያ ግንኙነት መሆኑ ላንድ አፍታም መዘንጋት ያለበት አይመስለኝም።
እነዚያ ኤርትራን ተራ በተራ በቅኝ ግዛትነት ተፈራረቁባት የተባሉት ቱርኮች፣ ግብፆች፣ ጣልያኖችና እንግሊዞች ጓዛቸውን ሸክፈው በመጡበት እግር ወደ አገሮቻቸው ተመልሰዋል። ዕድሜ "አልዛባ" ላለው ጂዮግራፊ "የመጨረሻ ቅኝ ገዢዎቹ" ግን እንደ ጥንቱ በነበሩበት አሁንም እንደ ጎረቤት አሉ። የትም አልሄዱም። የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ትስስር መሠረቱ እዚያ ላይ ነው። ባንዱ ወይም በሌላው የመንግሥታት ተጣማሪነት ባይገናኙም፤ ቢያንስ ጎን ለጎን በጉርብትና መኖሩ እጣ ፈንታቸው ሆኖዋል። ከሁሉ በላይ ያለፈውን ታሪክ ብቻ ሳይሆን መጪው እጣ ፈንታቸው የተቆራኘ ነው። መንግሥታትም ድርጅቶችም ጠፊዎች ናቸውና። አገሮችና ሕዝቦች ይኖራሉ። በጉርብትና ይኖራሉ። ጎን ለጎን ባንድ አገር ጥላ ስር ወይም በሁለት ራሳቸውን በቻሉ አገራት ዜግነት። ኤርትራ በትግል ነፃነት መቀናጀት ቻለች። ወያኔ ኢትዮጵያን መቆጣጠር ቻለ። እንኳን በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝቦች መሃል ሰላም ሊያሰፍኑ ቀርተው በድርጅቶቻቸው ውስጥ መረጋጋት መፍጠር አልቻሉም። ሁለቱ ድርጅቶች ቢታረቁም ቢጠፋፉም የሕዝቦቻችን እጣ-ፈንታ ተጣማሪነት ከዕይታችን መራቅ የለበትም። ከጊዜያዊ ድሎች ባሻገር አሻግረን እንመልከት!
ጉዳዩን ጠለቅ ብላችሁ መመልከት ለምትሹት ተጨማሪ ንባብ፣
ዩሱፍ ያሲን፣ የትግርኛ ተናጋሪዎቹ ቋሚና ተለዋዋጩ የማንነት መግለጫዎች - ሁለቱን ሕዝቦች በማቀራረቡ የሚኖራቸው ሚና፣ በሳን ሆዜ የኢትዮጵያና ኤርትራ ወዳጅነት ኮንፊረንስ፣ ማርች 2010
ዩሱፍ ያሲን፣ አሰባሳቢ ማንነት፣ ባንድ አገር ልጅነት ኤሶፕ አሳታሚ፣ 2014
ሐሰን ዑመር ዓብደላ፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ፣ ያልተጠናቀቀ ፍቺ፣ ያልተቻለ ጉርብትና፣ ታህሣስ 1991 ጦቢያ መጽሔት
Hassan Umer Abdalla, Ethiopia & Eritrea: Let's get the facts clear 2009 (http://www.ethiomedia.com/adroit/2560.html)
Abbay, Alemseged, Identity Jilted or Re-imagening Identity? The Different Paths of the Ertitrean and Tigrayan Nationalistic Struggles, Red Sea Press, 1998
Tronvoll, Kjetil, War & Politics of Identity in Ethiopia, Making of Enemies & Allies in the Horn of Africa, 2009



