ብሔራዊ ስሜትን ያልተላበሰ ተቃውሞ
ስሜነህ ታምራት (ከስዊድን)
ከጥቂት ሣምንታት በፊት ለዐባይ ግድብ ማስፈጸሚያ የሚውል የገንዘብ ማስገኛ ስብሰባን ለማደናቀፍ በኖርዌይ ሁለት ተቃውሞዎች ተደርገዋል። ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ይህ ሚዛን የጎደለው ተቃውሞ ብቻ ሳይሆን፤ ይልቁንም ተቃዋሚዎቹ ከስዊድን ራዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ "እኛ የኖርዌይ ጀግኖች ነን!" ሲሉ መደመጣቸው ነው።
ብሔራዊ የገንዘብ ማሰባሰብ ፕሮግራምን ዓይን ጨፍኖ መቃወም ጀግንነት ከተባለ፤ ለዘመናት ሳይደፈር የቆየውን የዐባይ ወንዝ ለመገደብ ደፍሮ መጀመርስ ምን ሊባል ይቻላል? መልሱንና ፍርዱን ለአንባቢ እተወዋለሁ። ድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ፤
"ወይ ስጋ ሳይሉ መፍረድ ነው እንደራስ፣
እውነት የሰው ሀገር ዐባይ ወይስ ቬጋስ።"
የሚለው የግጥም ቋጠሮው የዐባይ ግድብን በጅምላና በጭፍን ለሚቃወሙ ወገኖች ቁም ነገር ያለው መልዕክት የሚያስተላልፍ ይመስለኛል። ከታሪክ ማህደር እንደሚታየው እያንዳንዱ መንግሥት በዘመኑ የፈጸመው ሕገወጥና ኢ-ሰብዓዊ ተግባር ያለውን ያህል አናሳ ቢሆንም፤ ለመጭው ትውልድ ተክሎት የሚያልፍ በጎ ብሔራዊ ተግባርም አለው። በዋቢነትም የአፄ ዮሐንስ የመተማ አወዳደቅ፣ የአፄ ቴዎድሮስ የባርያ ንግድ ማቆሚያ አዋጅና ሀገሪቱን አንድ ለማድረግ የመነሳት ራዕይ፤ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሁለንተና የሥልጣኔ መሠረቶች፣ የአፄ ኃይለሥላሴ የገለልተኛ መርሆ ፖሊሲ፣ የደርግ መሬት ለአራሹና የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ በጥቅል በጥቅሉ የሚጠቀሱ የየመንግሥታቱ በጎ ተግባራት ናቸው።
ኢህአዴግም እንደቀደምቶቹ መንግሥታት ሁሉ አፍራሽና በጎ ተግባሮች አሉት። ይህን አለመቀበል ይቻላል። ዳሩ ግን ወይ ጭፍን ጥላቻ አልያ ጭፍን አፍቃሪነትን መጠናወት ይሆናል። ብሔራዊ ጠቀሜታ ካላቸው የኢህአዴግ ተግባራት መካከል የዐባይ ግድብ ፕሮጀክት አንዱ ነው ብዬ በግሌ አምናለሁ። ስለሆነም ዐባይ ዛሬም ይሁን ነገ ተገድቦ ለሀገር መዋሉን ቢቻል መደገፍ እንጂ መቃወም ግን ብሔራዊ ኃላፊነትና መቆርቆር የጎደለው ተግባር ይመስለኛል። ኢህአዴግን ከመቃወም ብቻ የመነጨ የፖለቲካ ፍጆታ ከሆነ ይኼ ሌላ ጉዳይ ነው። ይህን የሚያነብ አንዳንድ ችኩል መስካሪ፤ "ተመልከቱ ይኸን የወያኔ አራጋቢ፣ ..." ወዘተ ሊለኝ ይቻላል። ከዚህ ይልቅ ግን፤ ትዕግስቱን ሰጥቶት አንብቦ ቢተቸኝ ደስ ይለኛል። አስተያየቴን መቃወም ሙሉ መብት አለውና።
በአንጻሩም ሌላኛው ደጋፊ ደግሞ አሁንም አንብቦ ሳይጨርስ፤ "እኮ እኛም የምንለው ይኸንኑ እኮ ነው! ..." የሚል የኢህአዴግ አፍቃሪም ሊኖር ይቻላል። ይኽም እስከመጨረሻው አንብቦ በኩረ ሃሳቤን ቢረዳልኝ እወዳለሁ። ሃሳቤን መደገፍና መጋራት ግን መብቱ ነው። ሁለቱም ክፍሎች ያሻቸውን ትርጉም ቢሰጡትም ግላዊ አስተያየቴ ያተኮረው ግን ለነፃነት በሚደረገው የትግል ሂደት ለይቶ መታገልና ሚዛናዊ ተቃውሞ ማሰማት የሚኖረውን ብሔራዊ አስታጽዖ ማሳየት ነው። ከዚሁ ጋር አያይዤም ዐባይና በዐባይ የተነሳ የቆዩ ቅራኔዎችን ምን ይመስላሉ በሚለው ዙሪያ አቅም ፈቀድ ዳሰሳ አደርጋለሁ።
የነፃነት ትግላችን
ከሁሉ በፊት ግን መነሻ ስለሆነው የነፃነት ትግል ከመነሳቱ በፊት፤ ነፃነት ራሱ ምንድን ነው? ነፃነት በሌላ አካል ይሰጣል? የሚሰጥ ከሆነስ ሰጭውና ነሽው ማን ነው? ነፃነቱን የተከለከለ ህዝብስ የነፃነት ትግሉን በምን በምን መልኩ ያካሂዳል? እነዚህና የመሳሰሉት መሪ ጥያቄዎች በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የግንባታ ሂደት መነሳታቸው አይቀርም። ለእነኝህ ጥያቄዎች የታሪክ ባለቤት የሆነው ህዝብና የህዝብን እንቅስቃሴ የሚመዘግበው ታሪክ በርካታ ፍልስፍናዊና ፖለቲካዊ ትርጉሞችን አስተምረውናል። እንግዲህ ህዝብ የሠራቸውንና ታሪክም የጻፋቸውን ሰፊና ጥልቅ የነፃነት ትንታኔ በአንድ ገዥ አገላለጽ ሸብልሎ/ጠቅልሎ ለማቅረብ ቢቻል፤
"ነፃነት የሰው ልጅም ሆነ እንስሳት ተፈጥሮ ከሰጣቸው መብት ጋር መንግሥታትም የሰው ልጅ መብቶችን የሚያስከብሩ ናቸው ብለው የደነገጉዋቸው መሠረታዊ የሆኑና ያልሆኑ መብቶች የመከበር ወይም ያለመከበር መገላለጫ የሆነ የሰው ልጅ ህልወና ነው።" ማለት ይቻላል።
የሰው ልጅን ወደ የነፃነት ትግል የሚያመሩትም እነዚህ የተፈጥሮም ሆኑ በየመንግሥታቱ የተደነገጉ የሰው ልጅ መብቶች አለመከበርና የመብቶቹ መጣስ ናቸው። ስለሆነም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ግንባሮች፣ ነፃ አውጭዎችና ህዝቦች ይበጀናል በሚሉት የትግል ስልቶች እየተጠቀሙ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ይታገላሉ ማለት ነው።
ትግል ሲባልም በጎ ነገሮችን እያበረታቱ ጎጅዎቹ እንዲወገዱ መታገል እንጅ፤ በጭፍን ጠልቶ መነሳሳት ሚዛን የጎደለው ተግባር ከመሆኑም ባሻገር ውጤቱ ሊመዘን አይችልም። ለዚህ ነው የህዝባዊ ጠበብቶች በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚታገሉትን አውቆና ለይቶ መታገል ታላቅ ሚና እንደሚጫወት አበክረው የሚያስገነዝቡት። (ጄን ሻርፕ 2003 ይመለክቱዋል። እኒህ ምሁር ወደ ዲሞክራሲ ሥርዓት ለመጓዝ ስለሠላማዊ ትግል ሰፊ ጽንሰ ሃሳብን ያስጨበጡ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ጠበቃ ናቸው።)
ወደ ነጥቤ ልመለስና፤ ምናልባትም ከዛሬ 10 ዓመት በኋላ አንገብጋቢና ብሔራዊ ጉዳይ ሆኖ ሊያነጋግረን በሚችል ጉዳይ ላይ ዛሬ መናቆሩ የብሔራዊ ቅራኔ አፈታት ሂደትን አለማጤን ስለሚሆን ብሔራዊ ፋይዳው ጉልህ አይደለም። በኅብረተሰብ የእድገት ሕግጋት መሠረት "መጥፎ" ነገር በብቻው አይኖርም። "ደግ" ነገርም እንዲሁ። አንዱ ያለሌላኛው መኖር ትርጉም አይሰጡም። ስለሆነም ከእያንዳንዱ መጥፎ ተግባር ጎን ለጎን አንድ ደግ ነገር መኖሩን መቀበል ግድ ነው።
መጥፎውን ማስወገድ አስፈላጊ ቢሆንም፤ መጥፎ ተግባሮች ካልተወገዱ ጥሩውን ተግባር አልቀበልም ማለት ግን ሩቅ መንገድ አያስኬድም። መጥፎ ነገር በባህርይው ጥሩ ነገርን የመሸፈን/የመደበቅ ሚና ስለሚጫወት ሚዛናዊ አመለካከታችንን እንዳያዛባ መጠንቀቁ ይበጃል። እናም የዐባይ ግድብ ፕሮጀክት እንቅስቃሴን ማደናቀፍ አንድ ትልቅ ብሔራዊ እሴትን እንደመናድ ይመስለኛል።
ዐባይ - ግብጽ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ
የዓለም ረዥሙ ወንዝ ዐባይ (4160 ማይልስ)፤ ጥቁር ዐባይ 80% እና ነጭ ዐባይ 20% በሚሸፍኑ ሁለት ገባር ወንዞች ተጥለቅልቆ የሱዳንና የግብፅ በረሃን እያለማና እያቋረጠ ወደ ሜድትራንያን ባህር ይጓዛል። የዐባይ ተፋሰስ የሚበሉ 10 ሀገሮች ይኑሩ እንጂ፤ የዐባይ ሰማንያ በመቶ ከእኛው ሀገር ከኢትዮጵያ እንደሚሄድ የውሃ ልማት ጠበብቶች ይናገራሉ። ከክርስቶስ ልደት 450 በፊት ሔሮዱትስ የተባለ ግሪካዊ ታሪክ ፀሐፊ፤ ግብፅ የዐባይ ስጦታ ናት፤ ወይም በራሱ አባባል "Egypt is the gift of Nile" በማለት መጻፉ፤ የግብፆች ሕይወትና የዐባይ ወንዝ በመኖርና ያለመኖር ያህል በጥብቁ የተሳሰሩ መሆናቸውን ያመላክታል። በአንፃሩም ኢትዮጵያና ግብፅ ይህን የዐባይ ወንዝን በተመለከተ በዲፕሎማሲ የተሸፈነ ጦርነት ሲያካሂዱ እንደኖሩ ይታወቃል። ዐባይ ተገድቦ ለሀገር ልማት እንዲውል ብዙ ተብሎለታል። ከባህላዊው የከብት እረኛ ጀምሮ እስከ በሙዚቃ ሙያ የተካኑ ባለሙያዎች የዐባይን ብሔራዊ አገልግሎት ለማሳደግ ብዙ ብዙ ተዘፍኖለታል። ተዘምሮለታልም።
"ዐባይ ዐባይ! ዐባይ ዐባይ!
ያገር ሲሳይ ..."
"ወንዞች ይገደቡ ይዋሉ ለልማት
በከንቱ ፈሰዋል ለብዙ ሺ ዓመታት ..."
... እና የመሳሰሉት ብሔራዊ ቁጭቶች ሁሉ የዐባይን የሀገር ውስጥ ፍጆታ የማሳደግ ጥሪና በጎ ምኞቶች እንደነበሩ በቁጭት እናስታውሳለን። ሆኖም ግን ሁኔታው ባለመፍቀዱ በቁጭት ከማዜም የዘለለ ተግባር ለመሥራት አማራጭ አልነበረንምና ቆይተናል። በአንፃሩም ዛሬ ትናንት የነበሩ የኃይል ማዕዘኖች ተለውጠዋል። በአንድ በኩል በሰሜን አፍሪቃና በመካከለኛው ምስራቅ ዐረብ ሀገሮች አምባገነኖችን እያናወጠ ያለው ህዝባዊ ማዕበል የዐረቡን ዓለም ሚዛን አሳጥቶታል። በእጅጉ ይኩራሩበትና ይመኩበት የነበረው የተባበረው የዐረብ ኃይልም በእጅጉ ሳስቷል። በዚህ የተነሳም ሁሉም ትኩረቱን በቤቱ ውስጥ ወይም በሀገር ውስጥ ጉዳዩ እንዲያሳርፍ ሁኔታው የግድ ብሎታል። ትናንት በዐባይ የመጣ በዐይኔ/በሕይወቴ የመጣ ነው ብሎ በጀትና በሮኬት የማስፈራራት አቅም ወደ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ተቀይሯል። (የግብፅና የኢትዮጵያን ስምምነት ያጤኗል።)
በሁለተኛ ደረጃ፤ የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች "የዐባይ የውሃ አጠቃቀም ከትናንቱ የቅኝ ገዥዎች ሕግና አመራር ወጥቶ ሁሉም ሀገሮች ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የሚጠቀሙበት አዲስ ስምምነት ይፈጠር"፤ የሚለው ግፊታቸውና ስምምነታቸውን በፊርማ ማጽደቃቸው፤ ዐባይን መጠቀም ዛሬ ነው ወቅቱ ብለን እንድንነሳ ሁኔታው ፈቅዶልናል። ታድያ ዛሬ የዐባይ መገደብ ብሔራዊ ኩራትና ብሔራዊ ብርታት የሚሰጠን እንጅ፤ እንደትናንቱ እጅ የሚያሰጥና የሚያስቆጭ ድርጊት ሆኖ ሊወገዝ አይገባም እላለሁ።
እንቅስቃሴውን የሚያደናቅፍ ርምጃ መውሰድም፤ ዶሮዋ "ባልበላውም ልድፋው" እንዳለችው አይነት፤ "ለምን ኢህአዴግ ጀመረው?" ካልሆነ በስተቀር ተቃውሞው አሁንም ሚዛን የጎደለው ስህተት ነው እላለሁ።
ሌላው ሌላው ቢቀር በግብፆችና ሱዳኖች ላይ የነበረብንን ዝቅተኝነት መስበር መቻል በራሱ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው። 6 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት መነሳሳት በርካታ ችግሮችን ሊቀርፍ መቻሉ እንዳለ ሆኖ፤ የተፈጥሮ ሀብታችንን የመጠቀም ሉዓላዊ መብታችን መሆኑን ማረጋገጥም በራሱ ብሔራዊ ኩራት ነው።
በሠለጠነው ሀገር እንምናየው የሀገር ልማትን ለማሳደግ በሃሳብ ከሚግባቡት ጋር ብቻ ሳይሆን በሃሳብ ከማይጣጣሙት ጋርም አብሮ መሥራት አመርቂ ውጤት ማምጣቱን በዓይናችን አይተናል። ይኽን አይነት በጎ ተግባር በተለይ እኛ በውጭ የምንኖረው ወገኖች ካልተረዳን ደግሞ ማን ሊረዳው ይችላል? ለዚህ ነው ወቅቱ የሚፈልገውን የትግል አይነት አውቆ መታገል ገንቢ ውጤት ያስከትላል የሚባለው። እንጀራና በርበሬ ከሚሸጥበት መደብር ተላይቶ የማያውቅና በየጊዜው የሽያጭ መኪና ሀገር ቤት እየላከ ጥቅሙን የሚጠብቅ ዜጋ፤ በሰልፍ ላይ እየተነሳ ስለኢኮኖሚ ቦይኮት ማላዘን ሞራል የጎደለው የትግል አካሄድ ቢባል አይደንቅም። ብዙ ተያይተናል፤ ብዙ ግን አልተዋወቅንም። በውል ባለመተዋወቃችንም በውል የምንታገልለትን ዓላማ ማወቅ አልቻልንም። ለዚህ ነው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት ሳንካችን የበዛው።
የእንግሊዝና የቅኝ ተገዥዎችዋ ብልጣብልጥነት በዐባይ ላይ
ዐባይን አስመልክቶ ወደኋላ መለስ ብለን ስንመለከት፤ ግብፅና ሱዳን ለብዙ ሺህ ዓመታት የዐባይ ውሃና ለም አፈር (የዐባይ ወርቅ ማለት ይቻላል) ያለተቀናቃኝ ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሚዎች ሆነው ቆይተዋል። ቅኝ ገዥያቸው የነበረችው ታላቋ ብሪታንያ በ1929 እና 1959 ባፀደቀችው ስምምነት መሠረት ማናቸውም የተፋሰሱ ሀገሮች ዐባይን ገድቦ መጠቀም እንደማይቻል ይከለክላል። ከዛም ባሻገር በዐባይ የውሃ ሀብት ግብፅ 75%፣ ሱዳን 11% የመጠቀም መብታቸውን ሲያከብር፤ ቀሪዎቹ ሀገሮች 14% ብቻ እንዲጠቀሙ ደንግጓል። ይህም በአማካይ ከ2% ያነሰ ማለት ነው። ይታያችሁ፤ 80% የዐባይ ምንጭ የሆነችው የኢትዮጵያ ድርሻም በዚህ ስሌት መሠረት ከ2% በታች ነው። ይህም የሚያሳየው በዘመነ ቅኝ ግዛት ግብፅና ሱዳን ማለት ሁለት የተፋሰሱ ሀገሮች ብቻ አብላጫውን የውሃ ሀብት እንዲጠቀሙና ሌሎች ግን ለጋሽ ሀገሮች እንዲሆኑ ያደረገና የቆየ ሕገ-ኦሪት ነበር ማለት ይቻላል።
እንግዲህ ይህ የኖረ ብሶትና ቁጭት ነው የተፋሰሱ ሀገሮች ለጋሽ ብቻ ሳንሆን ተጠቃሚ መሆን አለብን በማለት ለአዲስ የዐባይ ውሃ አጠቃቀም ስምምነት ያደረሳቸው። በመሆኑም በ2010 ኡጋንዳ ላይ የተሰበሰቡት አራቱ የተፋሰሱ ሀገሮች (ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያና ሩዋንዳ) አዲስና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የዐባይ ውሃ አጠቃቀም ስምምነት እንዲደረግ ተስማምተው ፈረሙ። ለሌሎቹ የተፋሰሱ ሀገራትም ተመሳሳይ ጥሪ በማቅረባቸው ኬንያ፣ ዲ.ሪ. ኮንጎ እና ቡሩንዲ የኡጋንዳውን ስምምነት በመደገፍ እነሱም ስምምነቱን በፊርማ እንደሚያጸድቁ ገለጹ። ሁኔታው የግብፅና ሱዳንን ቅስም ሰበረ። ከፍተኛ ድንጋጤንም ፈጠረ።
ዳሩ ግን ዛሬ ያላቸው ምርጫ እንደትናንቱ በኃይላቸው ማስፈራራት ሁኔታው ባለመፍቀዱ ጊዜን በሚጠይቅና በተለሳለሰ የዲፕሎማሲ ጨዋታ ችግሩን ለመፍታት መለሳለስ ጀመሩ። የኢትዮጵያና የግብፅ ጊዜያዊ ስምምነትም በዚሁ ሁኔታ የተፈጠረ ነበር።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከአፍሪቃ ቀደምት መንግሥት የነበራት ብቻ ሳይሆን የግዛት አድማሷም ሰፊ ነበር። በሰሜን እስከ የመን፤ በደቡብ እስከማዳጋስካር እንደነበር ብዙዎቹ የአፍሪቃ ሀገሮች ያውቃሉ። በዚህ ላይ የራሷ የሆነ ፊደል፣ ልዩ ልዩ ቋንቋዎችና ብሔረሰቦች እንዳሏትም ይረዳሉ። በአህጉሪቱ ይህችው ኢትዮጵያና ላይቤሪ ብቻ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር አለመውደቃቸውም የጠንካራ መንግሥት ባለቤትነትን ይመሰክራል። የኃይማኖት ጉዳይም አለ። በእነዚህና በመሳሰሉት ጉዳዮች በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ በርካታ ትንኮሳዎችና ወረራዎች ተቃጥተውበታል። ከግብፆች፣ ሱዳኖች፣ ቱርኮችና በቅርቡም ከሶማሌዎች ጋር የተደረጉ ጦርነቶች ለዚህ አይነተኛ ማስረጃዎች ናቸው።
በዚህ ላይ የቅኝ ገዥዎች ስውር ተንኮልና ሴራም አለ። የእንግሊዝ መንግሥት ግብፅና ሱዳንን ሁለቱንም ሀገሮች በቅኝ ያስተዳድር ስለነበር፤ ሀገሮቹ የዐባይ ውሃ የዘወትር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ስውርና ቀጥተኛ ተፅዕኖ ያሳድር ነበር። ግብፆች "ዐባይን ከአናቱ ለመቆጣጠር ሁልግዜ መሥራት" በሚለው የዘወትር ብሔራዊ የቤት ሥራቸው በተለያዩ ዘዴዎች የዐባይን ደህንነት ሲከታተሉና ሲጠብቁ ኖረዋል። ለምን ቢባል የዐባይ ደህንነት የግብፆች ደህንነት ነውና። ይኽ ብቻ አይደለም፤ ግብፅ ያለማቋረጥ በሚካሄደውና አሁንም ባላቆመው የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ሳቢያ ከምዕራቡም፣ ከምስራቁም ሰብስባ ያካበተችው ግዙፍና መጠነ ሰፊ የጦር መሣሪያ ሌላኛው ተግባሩ የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች በዐባይ ጉዳይ አንዳችም ርምጃ እንዳይወስዱ አነጣጥሮ መከላከል ነበር። እናም ግብፆች ጠንካራ መንግሥታት ሲገጥሟቸው በዲፕሎማሲ፤ ደካማውን ደግሞ በኃይል በማስፈራራት ዐባይን ለዘመናት ሙሉ ለሙሉ አስገብረውት ኖረዋል ቢባል ከእውነተኛ ታሪክ መውጣት አይሆንም። ሱዳንም በበኩልዋ እንደ የገዥዋ የእንግሊዝ ተቀጽላ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ የግብፅ ተባባሪና ጉዳይ ፈፃሚ በመሆን የዐባይን ሀብት ለራሷና ለጎረቤቷ ጥቅም ማስከበሪያ ስታውለው ኖራለች። ምክንያቱም ሁኔታው ይፈቅድ ነበር።
ዛሬ - እኛ
ዛሬ ደግሞ የተፋሰሱ ሀገሮች አዲስና አግባብነት ያለው የዐባይ ውሃ አጠቃቀም ስምምነት እንዲደረግ የሚወስኑበት አመቺ ሁኔታ እንዳለ መረሳት የለበትም። በዚህ ላይ በ1945 በስድስት ሀገሮች ካይሮ ላይ ተመስርቶ አሁን 22 አባላት ያቀፈው የዐረብ ሊግም ለክርስቲያን መንግሥስት መዳከምና ከጥንት ጀምሮ በቆየው የፀረ-ኢትዮጵያ አቋማቸው አንድነታችንንና ህልውናችንን ሲገዘግዝ መቆየቱ ተገቢ ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባዋል። ዐባይን መጠቀም ቀርቶ ኢትዮጵያ በኢትዮጵያዊነቷ እንዳትኖር በሶሪያ፣ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ኢራቅ፣ ሊቢያ፣ ሶማሊያ፣ ሳውዲ ዐረቢያና ኢራን በመሳሰሉት የዐረብ መንግሥታት ከጥንት እስከአሁን የሚደረግብንን ሴራና ርብርጎሽ እንደትናንቱ ሁሉ ዛሬም እምቢ በማለት ለብሔራዊ ጥቅማችን መነሳሳት የሁሉም የሀገሪቱ ልጆች የዜግነት ግዴታ ይመስለኛል።
ለጊዜ ምስጋና ይግባውና ትናንት ሀገራችንን ሊያፈራርሱና ህልውናችንን ሊያጠፉ የነበሩ ኃይሎች ዛሬ በተራቸው እነሱ ተበታትነውና ፈራርሰው በእኛው ሀገር ተጠግተው ለማየት በቅተናል። ያ ሁሉ እብሪትና እብጠት ዛሬ ተዳክሞና ተልፈስፍሶ መገኘት አንድ መልዕክት አለው። እንግሊዞች "ብረቱ እንደጋለ ቀጥቅጠው (Hit the iron when it is hot) እንዲሉ አቅም አንሶህ ያጣኸውን ብሔራዊ ጥቅም ጊዜው ሲፈቅድልህ ፈጥነህ ማስከበር ብረቱ እንደጋለ በመቀጥቀጥ የምትፈልገውን አይነት ቅርፅ እንዲይዝ የማድረግ አይነት ነው።
ከዚህ እውነታ በመነሳት ዛሬ የዐባይ ግድብ ተግባራዊነትን ቢቻል በሁለንተና መልኩ መደገፍ እንጂ ከዚያ አልፎ በአደባባይ መቃወም አሁንም ብሔራዊ ጥቅምን መገዝገዝ ይሆናል። ተቃውሞው ከራሳችን ከኢትዮጵያዊያን ሲሆን ደግሞ ከትናንቱ የዐባይ አለመገደብ ቁጭት በላይ የሚያስቆጭ ተግባር ነው። ይህን የዐባይ ግድብ ፕሮጀክት መቃወም ቢኖርባቸው እንኳን ሱዳኖችና ግብፆች እንጂ፤ ዐባይ ራሱ ከመነጨባት የተፈጠሩ ኢትዮጵያዊያን መሆናችን በታሪካችን አንድ አሳፋሪ ተግባር እንደፈፀምን ልንገነዘብ ይገባል።
መቋጫ
ቀደም ብየ እንደጠቀስኩት እንደማናቸውም መንግሥት ሁሉ ኢህአዴግም አበጀህ ተብሎ ሊበረታታና አይ ይኽኛው መንገድ አያስኬድም ተብሎ ሊታረም የሚገባው ጣምራ ጎኖች አሉት። በጎውን እያጠናከሩ መታረም ላለበት ሌላ አማራጭ አቅርቦ አማራጩን እንዲቀበል ማስቻል ራሱን የቻለ የትግል አካሄድ ነው። የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እስኪመጣ ወይም ኢህአዴግ ሥልጣን እስከሚለቅ ብሔራዊ ልማት ይቁም ማለት ወይም ሂደቱን ማደናቀፍ የምንመኘውን ሥርዓት አይፈጥርልንም። ሩቅ ጉዞም አያስኬደንም።
በሌላ በኩል ከዐባይ ግድብ በፊት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይገደብ የሚባል አስተያየትም ተሰንዝሯል። እኔ ግን የዐባይ ግድብ ልማት በአንድ በኩል፤ የሰብዓዊ መብት መከበር ትግል በሌላ በኩል፤ ሁለቱንም በጣምራ ማካሄድ ይበጃል እላለሁ። እየታገሉ ማልማት፤ እያለሙ መታገል የፖለቲካና የኢኮኖሚ የማይነጣጠሉ ተግባሮች በመሆናቸው ሁሉንም ነገር ትቶ በፖለቲካ ላይ ብቻ ማነጣጠሩ አሁንም ከጠቀሜታው ጎጅነቱ ያመዝናል።
የኢህአዴግን ፖሊሲ ተቃውሞ ሥርዓቱን መለወጥ አንድ ነገር ነው። ሥርዓቱ እስከሚለወጥ ልማት ይቁም፤ በተለይም ለዘመናት ስንቆጭበት የነበረውን የዐባይ ግድብ ተግባራዊነትን በአደባባይ ማወገዝ ብሔራዊ ጠቀሜታን ያላገናዘበና ሚዘን የጎደለው ርምጃ በመሆኑ ሊታረም ይገባል በማለት ግላዊ አስተያየቴን በዚሁ እቋጫለሁ።
ስሜነህ ታምራት (ከስዊድን)
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



