ዳዊት ፋንታ

በአንድ ወቅት ገጣሚና ደራሲ በዕውቀቱ ስዩም "ይህ አዲስ አበባ አይደለም፣ ይህ የገጠር ቀበሌ ነው" የተሰኘ መጣጥፍ ፅፎ ነበር። እናም በዚያች "ሥርዓት አልበኝነት" በነገሰባት የገጠር ቀበሌ ውስጥ የሂሳብ መምህሩ ከመቅፅበት ተነስተው የስዕል መምህር ሲሆኑ ይታያል። በርግጥም የሕግ የበላይነት ባልሰፈነባት በዚያች የገጠር መንደር የሂሳብ መምህሩ የስዕል መምህር መሆን ሳያንሳቸው ተማሪዎቻቸውን ሲያሰቃዩ ይስተዋላል።

 

 

እንግዲህ እስኪ ይህን ትንሽ ከድርሰትነቱ ወጣ ብናደርገውና የገጠር ቀበሌዋን የሂሳብ መምህር ወደ አዲስ አበባ ብናመጣቸው እንዲሁም እሳቸውም በለመዱት "ሕገ-አራዊት" ልመራ ቢሉ በአንፃራዊ ዕድገትና ሥልጣኔ ላይ ያለው የአዲስ አበባ ሰው እንዲህ የሚላቸው ይመስለኛል፦ "ይህ የገጠር ቀበሌ አይደለም፣ ይህ አዲስ አበባ ነው!"

 

በተመሳሳይ ወደ መንበረ መንግስት ከመጣ ከሁለት አሥርት አመታት በላይ ያስቆጠረው የወያኔ መንግስት በኢትዮጵያ የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመጣስ ብዙዎችን ለእስር፣ለእንግልትና ለስደት ከማብቃቱም በላይ በግፍ የገደላቸው ዜጎች ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም። በመሆኑም የወያኔ አገዛዝ ሀገራችን ኢትዮጵያን የፍትህ አልባና የአፈና ተምሳሌት አድርጓት ይገኛል።

 

ይሁን እንጂ ይህ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን በኃይል የመጨፍለቅ ወያኔአዊ አባዜ ባህር ተሻግሮ በምድረ አሜሪካ በቅጥር ነፍሰ ገዳዮቹ አማካኝነት በጋዜጠኛና አክቲቪስት አበበ ገላው ላይ ሊፈፀም የነበረውን የግድያ ሙከራ የአሜሪካ የፌደራሉ የምርመራ ቢሮ እንዳከሸፈው ኢሳት በጃንዋሪ 08, 2013 የዘገበው። እዚህ ጋር ነው እንግዲህ ለወያኔ "ይህ አዲስ አበባ አይደለም፣ ይህ አሜሪካ ነው!" ማለት።

 

የሕግ የበላይነት በሰፈነባት ሀገር በሀይልና በሕገ-አራዊት በመነዳት ንፁሃን ዜጎችን ለመግደል መሞከር አለማቀፋዊ አሸባሪነት ነው!!! በሕግ ሽፋን አንቀፅ 652/2009ን እየጠቀሰ ንፁሃን ጋዜጠኞችን በአሸባሪነት በመወንጀል ወደ እስር ቤት ሲወረውር የነበረው ወያኔ ዛሬ ቅጥር ነፍሰ-ገዳዮችን በመመልመል በአንዲት ሉዓላዊት ሀገር ውስጥ የሽብር ተግባር ሊፈፅም ሲያሴር መገኘቱ መለስ ዜናዊ በሮናልድ ሬገን ህንፃ ከተዋረደበት የሜይ አስራስምንቱ ስብሰባ ቀጥሎ ወያኔን እርቃኑን ያጋለጠ ሌላ አጋጣሚ ሲሆን ለወያኔ ተጨማሪ የፖለቲካ ኪሳራ፥ለአባላቱም ሌላ ስብራት ሆኗል። ቤል ተዋረደ፣ ናባው ተሰባበረ እንዲል ነብይ በመጽሐፉ።

 

በዚህ አጋጣሚ የወያኔን የሽብር ተግባር በእንጭጩ በመቅጨት የአበበ ገላውን ህይወት ለታደጓት የአሜሪካኑ የፌደራል የምርመራ ቢሮ ሠራተኞች ያለንን አክብሮት እየገለፅን "የወይናችንን ቦታ የሚያጠፉትን ቀበሮዎች፥ጥቃቅኑን ቀበሮዎች አጥምዳችሁ ያዙልን" መልዕክታችን ነው!!!ቸር እንሰንብት።

ዳዊት ፋንታ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ