ልጅ ተክሌ (ኦታዋ - ካናዳ)

መጀመሪያ አገራችንን፣ ቀጥሎ ደግሞ ባህላችንን፣ ከዚያ ማንነታችንን

1 - ሰዉ ሁሉ፡ የሚተነፍሰው ሊቢያን ነው። ግብጽን ነው። ቱኒሲያን ነው። የመንን ነው። ጅቡቲንም ሳይቀር። ስለዚህ ያኛው ጉዳይ ብዙ ሰዎች ስለበዙበትና የተጣበበ ስለመሰለኝ፡ “እንቁላላችንን ሁሉ ባንድ ቅርጫት” እንዳናደርግ በማሰብ፡ ደግሞም ትግሉ ፈርጀ ብዙ ስለሆነ እነሆ ፊቴን ወደ ባህልና ውርስ አዞርኩ። ለነገሩ የፖለቲካ ሩጫችንስ ቢሆን የባህልና የባህርይ ለውጥ ለማምጣት፡ ማንነታችንንና እኛነታችንን ለማስጠበቅ አይደል?

 

2 - ካንደኛው ልጀምር። አንደኛ በ2009 ክረምት ላይ ይመስለኛል (ሀምሌ ወይንም ነሀሴ)፡ ዋሽንግተን ዲሲ ለሁለት ሳምንት መጥቼ ሳለ፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ 34ኛው የኤርትራ የባህል ትርኢት የሚደረግበት ሳምንት ነበርና የአርበኞች ግንባር ሰዎች ጋብዘውኝ ከተወሰኑ ኢትዮጵያዊያን ጋር እሁድ ይሁን ቅዳሜ ማታ ሄድኩኝ። ቀላዋጭ!! ልትይኝ ትችያለሽ። በይኝ። ቦታው በታላቁ የዋሽንግተን ዲሲ የስብሰባ ማእከል ነው (ኒው ዮርክና 7ኛ መንገድ ላይ መሰለኝ)። የተመለከትኩት ነገር እጅግ የሚያስቀናና የሚገርም ነበር። ያንን የሚያህል የስብሰባ ህንጻ ተቆጣጥረዉት፡ ባራቱም ማእዘን፡ ስፍር ቁጥር የሌለው ኤርትራዊ ይገባል ይወጣል። ደረጃውን ሁሉ የሞላው ኤርትራዊውዊን ትተሽ፡ በየፎቁ ላይ የተኮለኮሉት የታጋዮች፣ የሴቶች፣ የምናምኖች የቀድሞ ምናምኖች ማህበራት የሚሸጧቸው ሸቀጦች … ተይው እህቴ።

 

3 - አዳራሹ ውስጥ ስንገባ መንቀሳቀሻ የለም። ጢም ብሎ ሞልቷል። ሀምሳ ሀምሳ ብር እየተከፈለ ቢገባም፡ እኛ እንግዶቻቸው ስለነበርን በነጻ ነው የገባነው። ከሚኒስትራቸው ጎን ወስደው አስቀመጡን። እነሱ፡ ኤርትራዊያኑ ይወያያሉ። አይገርምም፡ በሀያ ዓመት፡ እነሱና እኛ ስንሆን። አይ ሀያ ዓመት፡ ስንት ነገር ይለውጣል?! ከዚያ ውይይቱ ሲያልቅ ጭፈራ መጣ። በረከት መንግስተ አብ … ሄለን ምናምን፡ አከሌ እንቶኔ፡ የቆነጃጅቱ ብዛት፡ የህጻናቱ ብዛት፡ ሹሩባቸው፤ ቀሚሳቸው፤ አንገታቸው፤ ሀብላቸው፤ ይሄንን ሁሉ ሰው ነበር እንዴ ኢትዮጵያዊ አድርገን ስንቆጥር የነበረው አልኩኝ?

 

4 - ግን አስቀኑኝ። እኛ የሚቆረቆርልን፡ የምንወደው የሚወደን መንግስት በማጣታችን መሰባሰብ ሳንችል ስንቀር፡ እነሱ ግን ከኛ ባነሰ ቁጥራቸውና ሀብታቸው፡ እኔ ምስክር የሆንኩበት ታላቅ ፌስቲቫል አካሄዱ። በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ ኤርትራዊያን ነበሩ ብል አላጋነንኩም። ያ ካንድ ኳስ ሜዳ ከሚበልጥ አዳራሹ ውስጥ ብቻ ከአራት ሺህ ሰው በላይ ነበር። ውጭ ያለውን ተይው። ይሄ በያመቱ እንደሚደረግና ሁሉም ኤርትራዊ እንደሚሳተፍበት ሰዎች አጫወቱኝ። እንግዲህ ባንድ ቀን በዚያ ሰዓት ያን ያህል ህዝብ ከመጣ፡ በሶስቱ ቀን ፌስቲቫል ደግሞ ምን ያህል እንደሚመጣ አስቢው።

 

5 - (አንባቢ ሆይ፡ ይሄ ጽሁፍ የዛሬ አምስት ስድስት ወር አካባቢ፡ በዋሽንግተን ለምትገኘው፡ ነገር ግን ሀሳቤ ለሚደክማትና፡ ብዙም ደርጅቶ ላልታያት፡ ላልተወለደችኝ፡ ታላቅ እህቴ ከተጻፈ መልእክት የተወረሰና፤ ለአንባቢ እንዲስማማ ሆኖ የተጻፈ ነው)። ለመሆኑ ምን አስቤ ጻፍኩላት?

 

6 - በዘመነ ኢህአዴግ፡ ብዙዎቻችን አገራችንን ተቀምተናል። (የመጀመሪያው በነገራችን ላይ፡ በዘመነ ኢህአዴግ ብዙዎች አገራቸውን ያገኙም አሉ)። እኛ አገራችንን ያጣነው፡ አገራችንን እናስመልሳለን። እስከዚያው ግን በዚህ በውጭ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን፡ በያለንበት፡ ቢያንስ ባህላችንንና ማንነታችንን፡ እያስጠበቅን የምናቆይበት ተቋማትና ዝግጅቶች ያስፈልጉናል፤ ዘወትር ደረቁ ፖለቲካ ላይ ብቻ እያተኮረን፡ እስር እስር ግን የኢትዮጵያዊነት መገለጫና መቀመጫ የሆኑትን፤ የእምነትና የባህል ተቋማት እየተቀማን ነው። ስለዚህም፡ ታላቄ፡ እታለም፡ ገጣሚ፡ ጸሀፊ፡ አርቲስት ብቻ ስትባይ ከምትኖሪ፡ ምናለ አንድ ነገር ሰርተሽ ብታልፊ ብዬ ነው፡ ይሄንን የጻፍኩላት።

 

7 - ለተከበርሽው ውድ እህቴ፡ ታላቄ እታለም፡ እታበባ ከነቤተሰቦችሽ እንዴት ሰንብተሻል? ይሄንን ወረቀት ካነበብሽ በኋላ ጤንነቴ ካላጠራጠረሽና ያው እንደተለመደው “ቀውስ” ካላልሽኝ በስተቀር፡ እኔ እጅጉን ደህና ነኝ። ጨቅጭቄሽ ጨቅጭቄሽ አልሰማ ብለሽኝ፡ በመጨረሻ ግን በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጎበዛዝት ጥረት “የኢትዮጵያዊነት እሴት ማህበረሰብ በሰሜን አሜሪካ” (እነሱ “የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ማህበረሰብእ” ብለውታል፤ ሁለቱም ያስኬዳል።) ተሳክቶ ተመስርቶ ሳይ የተሰማኝን ደስታ ልነግርሽ አልችልም።

 

8 - በመቀጠል የማጫውትሽ ነገር ቢኖርም ከዚያው ካለፈው የቀጠለ ይሆናል። መቼም የኔ ነገር ባጭር አያልቅም፡ እያረፍሽም ቢሆን እስከመጨረሻው እንድታነቢው አደራ እልሀለሁ። ጽሁፌን የምጀምርልሽ በሶስት የምልሽን ነገሮች እንዳስረዳሽ በሚያግዙኝ ክስተቶች ነው። ሶስት ብቻ። አንዱን ከላይ ከመግቢያው ስላለነበብሽው ብዙ አይቀርሽምና ታገሺኝ። አንደኛው የኤርትራዊያኑ ተሞክሮ ነው።

 

9 - ሁለተኛ፡ በዚያው አመት መሰለኝ፡ በዚያኑ ሰሞን፡ በ2008/9 ክረምት፡ ከቨርጂኒያ ወደ ዲሲ፡ እንደኔ ቆሞ አልቀርም ብሎ በቅርቡ ትዳር ከመሰረተ ወጣት ወዳጄ ጋር ስንነዳ፡ በስተግራ በኩል ባለው የዋሽንግተን መታሰቢያ ሀውልቱ ጋር ያለው አውላላ ሜዳ ላይ ድንኳኖች ተደኩነው ነጠላ የለበሱ የኢትዮጵያ ሴቶችና ሌሎችም ኢትዮጵያዊያን፡ ካህናት፡ መዘምራን ሲገቡ ሲወጡ ተመለከትኩ። ሁለት ቀን የዋለ የቀሳውስት ወይንም የካህናት ቀን (መሰለኝ) የተባለ ዝግጅት እንደነበረ ሰማሁ። ገብቼም ተሳተፍኩኝ። ብዙ ድንኳኖች ተደኩነው፡ ስብከት፡ መዝሙርና መጻህፍት ሽያጭ፡ መረጃ አቅርቦት ይካሄዳል። ይዘመራል። ቅኔም ይቀኛሉ። የስእልና ፎቶ ኤግዚብሽንም ነበር። ብቻ ደስ ይል ነበር። የሰዉ ስሜትና ደስታ ወደር አልነበረውም። እንግሊዘኛ ተናጋሪዎችም ይገባሉ ይወጣሉ። ባካባቢው ያሉት ጎብኚዎችም ተጨማሪ ትእይንት አግኝተው ይጎበኛሉ።

 

10 - ሶስተኛው፡ የቫንኩቨር የኢትዮጵያ ማህበረሰብንና የመጀመሪያውን፡ እኔ እነደምለው የክረምት፡ ሌሎች እንደሚሉት ደግሞ የበጋ፡ ፌስቲቫል ይመለከታል። ልብ አድርጊ ብዙውን ግዜ ወይንም ሁልግዜ እኛ አገር የፖለቲካ፡ የእድር፡ የጽዋ፡ የምንም ማህበር ምርጫ ላይ ሰዎች የሚመረጡት በግድ ነው እንጂ ራሱን ምረጡኝ ብሎ አቅርቦ የሚመረጥ አታገኝም። እስኪ አቶ ሀይሉ ሻውልን ጠይቂያቸው። ጥንትም ዘንድሮም፡ “ተለምኜ ነው፡” “እኔ እምቢ ብዬ ነበር” ነው የሚሉሽ። በመስከረም 2009 ቫንኩቨር ግን እንደዚያ አልነበረም። “እኔን ምረጡኝ፡” ባልተለመደ መልኩ፡ “እንቶኔን ምረጡ” የሚል መጣ። “እንቶኔ ለፕሬዚደንት” የሚሉ ማስታወቂያዎች በየቤተክርስቲያኑ፡ በየምግብ ቤቱ በዙ። እሱን የመሰለ ልጅ አግኝተው ነው?! ያው የታወቀ ነው ተመረጠ። (ሁለተኛው በነገራችን ላይ፤ በነገራችን ላይ፡ እነዚህ አሁን ስልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ቶሎ ወድቀው፡ አገሬ ገብቼ “በአርሲ ነገሌ ወረዳ “የግንቦት ሰባት” ወይንም “የኢትዮጵያ ዴሞክራሲአዊ ሀይሎች ሕብረት” ወይንም የታጠቅ ለአንድነትና ለነጻነት” ብቻ ያንዱ እጩ ተመራጭ ለመሆን እንዴት ቋምጫለሁ መሰለሽ።” “ኢንሽ አላህ”። እንደ እስልምና እምነት ተከታይ ወዳጆቼ።

 

11 - ዋናው ነገሬ እሱ አይደለም። የቫንኩቨር የኢትዮጵያ ማህበረሰብእ አመራር አባላት ከተመረጡ በኋላ፡ አሰልቺና ፈታኝ ቢሆንም ብዙ ጥቃቅን ነገሮችን ሰሩና፡ ዋንኛው የአመቱ የመዝጊያ ስራቸው አመታዊ ፌስቲቫል ማዘጋጀት ሆነ። በከፍተኛ ርብርብ የተሳካ፡ ወደ ሁለት ሶስት ሺህ ኢትዮጵያዊን ባሉባት ቫንኩቨር ከአራት ሺህ ሰው በላይ የተገኘበት ፌስቲቫል አዘጋጁ። አላየሽው እንደሆነ እንጃ እንጂ፡ የዝግጅቱን ሁኔታ ቀንጨብጨብ አድርጎ ወዳጄ እንደልቡ በቪዲዩ አውጥቶታል። ግሩም ነበር።

 

12 - የከተማው ከንቲባ “ሞክሩ፡ ግን እንደምታስቡት ላይሆን፤ ሰው ላይወጣላችሁ ይችላል” ብሎ አስፈራርቶ ነበር። ነገር ግን፡ በሚያስገርምና በሚያስደንቅ መልኩ የተሳካ ፌስቲቫል አደረጉ። ኪሳራ ለመቀነስ ሲጥሩ፡ ባልገመቱት መልኩ የገንዘብም የሞራልም ትርፍ አገኙ። ኮሚኒቲውን ሲረከቡ ሁለት ሺህ ብር ብቻ የነበራቸው ቢሆንም፡ ከአመት በኋላ ሲያስረክቡ ግን ያንን በሶስት እጥፍ አሳድገውት ነው። እግዲህ ከ10 ሺህ ብር በላይ የፈጀውን ፌስቲቫል ስታስቢ፡ በፌስቲቫሉ ላይ የተገኙት የንግድና የሀይማኖት ድርጅቶች በአማካይ ያገኙትን አንዳንድ ሺህ ብር ስታስቢና ያንን በቫንኩቨር ከሚገኙ በጣት የሚቆጠሩት ኢትዮጵያዊያን ጋር ስታስተያዪው ገንዘቡ ትንሽ አይደለም። ከገንዘቡ ይልቅ ኩራቱ !! እኛንም አኮሩን።

 

13 - ባህልና ታሪክ፡ አገርና ዝና፡ ውርስና ቅርስ እንደሌለው ህዝብ፡ መልካም እረኛ አጥተን፡ ከኛ ኃላ በቅኝ ግዛት የተፈጠሩት እነ ትሪንዳድና ቶቤጎ፡ እነክሮሺያና ሮማኒያ አመታዊ የባህል ትርኢት አድርገው፡ ባህል እንደሌለው ታሪክና ውርስም እንደሌለው ኢትዮጵያዊ፡ ሄጄ ስቀላውጥ እንዴት ውስጤ ይቃጠላል መሰለሽ። ደግሞ እኮ ከዚያች አልፎ አልፎ ከምትመጣብን ጥቁር የረሀብ ነጥብ በስተቀር፡ እሱንም እድሜ ለርስበርስ ጦርነትና ለክፉ አገዛዞች፡ ሰው ፊት የሚቀርብ የሚያኮራ የማያሳፍር ታሪክ ነው ያለን። ነገር ግን፡ ኢትዮጵያዊነት ደበረንና፡ እነሆ እንደ ኦሮሞና እንደ ሀደሬ፡ እንደ ትግሬና እንደ አማራ፡ መሰባሰብን መረጥን። ብሄር መሰረት ያደረጉ ስብስቦች ጋር ችግር ባይኖርብኝም፡ የኔም ምርጫ ቢጠበቅና እንደ ኢትዮጵያ የሚሰበስበን ቢኖር ደስታዬ ወደር አልነበረውም። የሆነ ሆነና ያ ቅናት እያቃጠለን እኔና የስራ አጋሮቼ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ በቫንኩቨር የመጀመሪያውን የተሳካ የባህል ትርኢት እንዲያደርግ አደረግን። ክብር ለፈጣሪ፡ አሜን።

 

14 - ታላቄ፡ በዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘውን ሀበሳ ቁጥር ግማሹ ሶስት መቶ ሺህ ግማሹ ደግሞ አምስት መቶ ሺህ ያደርሰዋል። እንግዲህ አምስት መቶም ሁኑ አምስት መቶ ሺህ፡ የሙዚቃ ባለሙያዎችን፡ የጥበብ ባለሙያዎችን፡ የንግድና የሀይማኖት ድርጅቶችን፡ የባህልና የማህበረሰብ እንዲሁም የሙያ ማህበራትን አሰባስባችሁ አንድ አመታዊ የባህል ፌስቲቫል ማዘጋጀት እንዴት ያቅታችኋል? እንግዲህ በየክረምቱ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ስመላለስ አምስት አመት ሞላኝ። “አስቴር በዚህ ትዘፍናለች፡ ቴዴ አፍሮ በዚህ ይጫወታል። ክበበው በዚህ ይቀልዳል፡ ገበየሁ በዚያ ይሄዳል” ሲባል እንጂ፡ “ኢትዮጵያዊያን ማህበራት ወይንም የባህል ተቋማት ለሶስት ቀን ወይንም ለሳምንት የቆየ የባህል ዝግጅት አዘጋጁ ወይም ያዘጋጃሉ” ሲባል አይቼ አላውቅም። እነሆ አሁን ግን ያ ቀን መጣ።

 

15 - ያ የኢትዮጵያዊያን ስፖርትና ባህል ፌደሬሽን በሰሜን አሜሪካ በ2008 ክረምት የእግር ኳስ ዝግጁትን በዋሽንግተን ዲሲ ባዘጋጀበት ጊዜ እዚያ ነበርኩ። እጅግ በጣም ቆንጆ ነበር። ነገር ግን ፌደሬሽኑ ትኩረቱ በስፖርት ላይ ስለሆነና፡ እንዲሁም ፌደሬሽኑ በየአመቱ በተለያዩ የአሜሪካን ከተሞች ስለሚዘዋወር፡ ለባህልና ውርስ ፌስቲቫል ብቻም ሳይሆን፡ ቋሚ የሆነ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችና ህጻናት፡ አረጋውያንና ምሁራን እየመጡ ልምድ የሚለዋወጡበት የባህል ማእከል ለመገንባት፡ ከኢትዮጵያ ቀጥሎ ኢትዮጵያዊያን በብዛት በሚገኙበት ዋሽንግተን ዲሲና አካባቢው፡ የኢትዮጵያውያንን ሚናና ተሰሚነት የሚጨምር የባህል ትእይንት ለማዘጋጀት፡ መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገ የባህልና የታሪክ መዘክር እንዲቋቋም ስመኝ፡ ስጥርም ነበር። አንቺንም ስለማመጥሽ የነበረው ለዚሁ ነበር። አንቺ ጣጣሽ አያልቅም። እነሆ፡ ከብዙ ድካምና ውይይት፡ ምክክርና ክርክር በኋላ፡ “የኢትዮጵያዊያን ውርስና ቅርስ ማህበረሰብእ በሰሜን አሜሪካ” ለመመስረት በመቻላችን እጅግ አስደስቶኛል። ያንቺ ነገር ደግሞ፡ የተጋገረውንም መብላት ያቅትሻል አንዳንዴ፤ ዝርዝሩን ኸዚህ www.ethiopianheritagesociety.com ገብተሽ እይው።

 

16 - እታለም፡ እንግዲህ ለዚህ ነው፡ መጀመሪያ አገራችንን ተነጥቀን ተሰደድን፤ ቀጥሎ ደግሞ ባለንበት ባህላችንንና ውርሳችንን ማስጠበቅ ካልቻልን፡ ማንነት የሚባለው ነገር ይጠፋንና ማንም ሆነን ለልጆቻችንም ምንም ሳናወርሳቸው ከዚህ ዓለም እናልፋለን ያልኩሽ። እንግዲህ፡ ያ የምመኘው ቀን መጥቷል። ጁን 30 እስከ ጁላይ 3። በመጪው ሰኔ መጨረሻና ሀምሌ መጀመሪያ ላይ በሚካሄደው በዚህ “የኢትዮጵያዊያን ሄሪቴጅ ፌስቲቫል” እስክንገናኝ፡ ደህና ሰንብችልኝ።

 

17 - ባንድ በኩል አብይ ጾም በሌላ በኩል ትምህረት በሌላ ጎን ደግሞ ፖለቲካ እያንገላቱኝ ቢሆንም፡ ፈጣሪ ከፈቀደ፡ ከዚያ በፊት በዓለ-ትንሳኤን ከዲሲ አድባራት ባንዱ ለማክበር፡ ከወዲሁም ለዚህ ለባህል ትእይንቱ ቅስቀሳ ለመጀመርና ለጠቅላላ ጉባኤ ወዳንቺ ላንድ ሳምንት ልመጣ አስቤያለሁ። ይሄ የቱኒዚያውና የግብጹ ነገር ገፍቶ ከሄደና ስለታችን ከሰመረም፡ ሁሉን ነገር አዲስ አበባ ስላሴ፡ መርካቶ አንዋር፡ ወይም ጌጃ ቃለ-ሕይወቱ እናከብር ይሆናል። እስከዚያው ግን እታበባ እናፍቃለሁ። እስካይሽ ደህና ሰንብች።

መጋቢት፡ 2011

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ