መክብብ ማሞ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ታሪካዊው ‹‹ምርጫ›› በኢትዮጵያ ከተደረገና ህወሃት/ኢህአዴግ ራሱ ጥያቄውን አውጥቶ፣ ፈተናውን ካረመና በውጤቱ A+ ማግኘቱን ከነገረን ወዲህ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ ድርጅቶች እና ግለሰቦች መንደር ‹‹የአሁኑ ጊዜ ተከፋፍለን የምንጨቃጨቅበት ሳይሆን የአንድነት ነው›› በማለት ተባብሮ የመሥራት ጥያቄና ሃሳብ ሲቀርብ ሰንብቷል።

 

ከዚህ አኳያ ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌ እና ዓለማየሁ ገ/ማሪያም በግል እንዲሁ አቶ ኦባንግ ሜቶ የሚመሩት ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ ጋራ ንቅናቄ የተለያዩ ጥሪዎችን አስተላልፈው ነበር። በተለይም የአቶ ኦባንግ ጥሪ በጣም ግልጽና ሁሉንም የሚያካትት የነበረ ሲሆን፡ የጥሪውም ይዘት የተለያየ የፖለቲካ አመለካከቶች ያላቸውን ድርጅቶችና ነጻ አውጪ ግምባሮችን እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃኑን በሙሉ ‹‹አንድ ሁኑ›› ለማለት ሳይሆን እነዚህ የተለያየ አካሄድን የመረጡ ነገር ግን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያገባኛል የሚሉ ሁሉ ፊት ለፊት፣ አንድ ቦታ ላይ ተሰባስበው የወደፊቱ የትግል አቅጣጫ በእንዴት ዓይነት ሁኔታ መቀጠል እንዳለበት እንዲመክሩ ለማድረግ ነበር። እንዲያውም ንቅናቄው በጥሪው ላይ እንዳመለከተው ጉባዔው የስደት መንግሥት ለመመሥረት ሳይሆን ተገናኝቶ ለመምከር እንደሆነ አመልክቶ ነበር። ይህ በአቶ ኦባንግ በኩል የተጠራው ስብሰባ ከሁሉም ለየት የሚልባቸዉን ምክንያቶች ልጥቀስ፡-

 

  • ንቅናቄው ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ የአርነት ንቅናቄ ያልወገነ በመሆኑ፤
  • ጥሪው ‹‹ይህ መደረግ አለበት›› የሚል አጀንዳን የወሰነ ሳይሆን ሁሉም አካል ተሰብስቦ ‹‹ምን›› እና ‹‹እንዴት›› መደረግ እንዳለበት የሚወስንበት በመሆኑ፤
  • እያንዳንዱ አካል በአሁኑ ጊዜ የሚመራበትን ፕሮግራም ሳይቀይር ከሌሎች ጋር ተባብሮ እንዴት መሥራት እንዳለበት ስብሰባው የሚያስተባብር በመሆኑ፤
  • ንቅናቄው ስብሰባውን ከማስተባበር እና መንገድ ከመጥረግ ውጪ በስብሰባው ላይ የሚያራምደው የራሱ አጀንዳ የሌለው በመሆኑ፤
  • የንቅናቄው መሪ አቶ ኦባንግ ምንም እንኳን በአኙዋክ ሕዝቦች ላይ በደረሰው ጭፍጨፋ የራሳቸው ቤተሰቦች የተገደሉባቸው ቢሆንም ‹‹የጋምቤላ/የአኙዋክ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር›› የሚል የአርነት እንቅስቃሴ ሳይሆን ‹‹ከጎሣ ይልቅ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ እንስጥ›› በሚልና ‹‹ሁላችንም ነጻ ካልወጣን ማንም ነጻ ሊሆን አይችልም›› በሚል ሕብረብሔራዊ ዓላማ የያዘ ትግል የሚመሩ ቅን ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው፤

 

በእነዚህና በሌሎች ምክንያቶች በአቶ ኦባንግ በኩል የተጠራው የትብብር ስብሰባ ብዙ ውጤቶችን ሊያመጣ የሚችል ፈርቀዳጅ ስብሰባ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። በተለይም ንቅናቄው ከየትኛውም የፖለቲካም ሆነ የአርነት ንቅናቄ ያልወገነ መሆኑ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እጅግ ተከፋፍለው የሚገኙትን ቡድኖች ወደ ኅብረት ለማምጣት አመቺ ሁኔታ ሊፈጥር የሚችል ይሆን ነበር። ሆኖም ከጥቂት የሲቪክ ማኅበረሰቦች በስተቀር ለጥሪው በቂ ምላሽ ከፖለቲካ ድርጅቶችና የአርነት ንቅናቄዎች ባለመሰጠቱ ስብሰባውን የተሰረዘ መሆኑ ተዘግቧል።

 

ከዚህ በኋላ ሰሞኑን እየተሰማ ያለው ጉዳይ የብዙዎች መከራከሪያና መጨቃጨቂያ እየሆነ መጥቷል። ይህም የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግምባርን ወደትግሉ ለመቀላቀልና የትግሉን ኃይል ለማጠናከር በሚል ዓላማ ላይ የተመረኮዘ እንደሆነ ይደመጣል። በተለይም ይህ የጠነከረ ሃሳብ በግንቦት 7 ደጋፊዎች በከፍተኛ ሁኔታ ግፊት እየተደረገበት ያለ ጉዳይ እንደሆነ ይስተዋላል። ይህ ዓላማ የግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ሊደግፈው የሚገባ ተግባር ነዉ። ይህ የሁላችንንም ቁስል የሚነካ አጀንዳ በመሆኑ እና ችግሮቻችንም እርበርሳቸው የተጠላለፉ በመሆናቸው መፍትሔውም ሁሉንዓቀፍ ትግል የሚጠይቅ ነው። ሆኖም ግን የኦነግ ስም ሲጠራ አብረውት የሚነሱ በርካታ ጥቄዎች አሉ።

 

  1. በአሁኑ ጊዜ ኦነግ ቢያንስ ለ3 ተከፋፍሏል - እንዲያውም አንዳንዶች ለ4 ነው ይላሉ - ድርድር ይጀመር ቢባልስ ከየትኛው ኦነግ ጋር ነው የሚደረገው? ከአንዱ ጋር ብቻ ተስማምቶ ውሳኔ ቢደረስ እንኳን ሌሎቹ ስምምነቱ እኛን አይወክልም ብለው በኦነግ አርማ መግለጫ እንደሚያወጡ ጥርጥር የለውም።
  2. ኦነግ በድረገጹ ላይ ‹‹ኦሮሚያ›› የምትባል አገር እንዳለች እና ይህችኑ ‹‹ኦሮሚያን›› በቅኝ ግዛት የያዘች ኢትዮጵያ (አቢሲኒያ) የምትባል ‹‹ኋላ ቀር ቅኝ ገዢ አገር›› እንዳለች በግልጽ ይናገራል። ሲቀጥልም ‹‹ኦሮሚያን›› ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር እኩል በማድረግ አውሮፓውያን አፍሪካን ሲቀራመቱ አቢሲኒያ ደግሞ ‹‹ኦሮሚያን›› ቅኝ እንደያዘችና ሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች ነጻ ሲወጡ ‹‹ኦሮሚያ›› ግን በአንዲት ‹‹የጥቁር አፍሪካ አገር እስካሁን ቅኝ መያዟ ጉዳዩን ልዩ እንደሚያደርገው›› ከሚያምን ድርጅት ጋር ምን ዓይነት ድርድር ነው የሚካሄደው? ለመጀመርስ እንዴት ነው የሚቻለው?

 

ሌላው ሰሞኑን በአዲስ ድምጽ ሬዲዮ እንዲሁም በአውራምባ ታይምስ ላይ አቶ ጃዋር ሲራጅ ሲናገሩ ኦነግ በተለያዩ ጊዜያት ‹‹የፕሮግራም መሻሻል በማድረግ ይበልጥ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ችግሩን የመፍታት›› ውሳኔዎችን እንዳደረገ ከጠቆሙ በኋላ ይህንኑ ዓይነት የመለካከት ለውጥ ከተቃራኒው ወገን መምጣት እንዳለበትና ‹‹ወደ መሃል የመምጣት ሥራ መሠራት እንዳለበት›› ይህ ግን ‹‹በተጨባጭ እየታየ እንዳልሆነና በተለይ ከአማራው ወገን ወደ መሃል መምጣቱ ወሳኝ›› እንደሆነ ተናግረዋል።

 

ለመሆኑ ኢትዮጵያ የአማራ ብቻ ነች? ከሆነችስ ‹‹ወደ መሃል የሚመጣው›› እንዴት ነው? የአንድነት ደጋፊ የሆነው ‹‹ኢትዮጵያ ኦሮሚያን ቅኝ ገዝታለች›› ብሎ ከተናገረ ነው ‹‹ወደ መሃል መጣ የሚባለው››? በመሠረቱ አማራውን ከኢትዮጵያዊነት ጋር ማጣመሩ ለዘመናት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የድንበር መጠበቅ የተሰዉትን የሌሎች ብሔር ጀግኖችን (ኦሮሞዎችንም ጨምሮ) ክብር የሚያጎድፍ ብቻ ሳይሆን ‹‹ለአማራ የቆሙ ባንዳዎች›› ብሎ ከማዋረድ የሚተናነስ አይደለም።

 

ገበየሁ ቢሞት ተተካ ባልቻ

መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ፤ የተባለለትን የአድዋ ጀግና ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶን እንዲሁም እስከዛሬ በዓለም የአየር ወለድ ታሪክ አቻ የማይገኝለት ዝላይ ዘልሎ ወደር የሌለው የጦር ሜዳ ጀብዱ የፈጸመውን የናቅፋው ጀግና ብ/ጄ ተስፋዬ ሀ/ማርያምን (የጉራጌ ተወላጅ) እንዲሁም ሌሎች የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆችን ማዋረድ አይሆንምን? ሌሎችንም ማንሳት ይቻላል!

 

የኦነግ ከሌሎች ጋር አብሮ ለመሥራት መፈለግ መለኪያዉ በመጀመሪያ በኢትዮጵያ የሕዝቦች መብት መከበር እና የዴሞክራሲ መስፈን ቀዳሚው ተግባር መሆኑን እንደ ድርጅት ሲያምን፤ ጽንፈኛ አቋሙን ሲያለዝብ እና ለኦሮሞ ሕዝብ መብቶች መከበር የሚያቀርበው መፍትሔ ከ‹‹መገንጠል›› በመለስ ሌሎች አማራጮችን ወደ ጠረጴዛው ሲያቀርብ ብቻ ነዉ። እነዚህ ሲሟሉ ነው ኦነግ ‹‹ወደ መሃል›› መጣ የሚባለው። ካልሆነ ግን የዛሬ 40ዓመት የቆሙበት ቦታ ላይ ሆኖ ሌላውን ‹‹ወደ መሃል›› መምጣት አለባችሁ ማለት ሌላ የ40ዓመት ዕድሜ ለመጨመር ከመፈለግ ያለፈ የትም የሚያደርስ መከራከሪያ አይደለም። ይህንን ከግንዛቤ ያላስገባ የድርጅቶች ድርድርም ሆነ የትብብር ስምምነት ሀገራዊ ፋይዳዉ ጎጂ ከመሆኑ በተጨማሪ ጊዜያዊ ‹‹ሆያ ሆዬ›› ከመፍጠር ባለፈ ለታሪክ ተጠያቂነትም ይዳርጋል።


መክብብ ማሞ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ