ግርማ ካሣ

እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ አደረሳችሁ!

(ይህ መልዕክት የክርስትና እምነት ተከታይ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን የተዘጋጀ ነው። ነገር ግን ጌታችን መድኃኒታች ኢየሱስ ክርስቶስ በሙስሊሞች ዘንድም ኢሣ ተብሎ እንደ ታላቅ ነብይ የሚቆጠር ስለሆነ፣ ለሙስሊም ወገኖቼም በተዘዋዋሪ መንገድ ትምህርት ሰጪ ነው ብዬ አስባለሁ።)

የአትላንታ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መጋቢ የሁኑት ቄስ ቶሎሳ ጉዲና ንግግር ያደረጉበት አንድ ታላቅ መንፈሣዊ ስብሰባ በአዲስ አበባ ታላቁ ስቴዲየም ተደርጎ እንደነበረ ሰምቻለሁ። ከስታዲየሙ ትንሽ ሄድ ብሎ በሚገኘው በመስቀል አደባባይ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በተገኙበት፣ የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግም ከጥቂት ቀናት በፊት፣ አቡነ ፓትሪያክ ጳውሎስ ንግግር አድርገው ቡራኬ ሰጥተዋል።

 

እነዚህን ሁለት ታላላቅ ዝግጅቶች እንደምሳሌ ጠቀስኩኝ እንጂ፤ በየአብያተ ክርስቲያናቱ በየጊዜው የሚደረጉ ቅዳሴዎችን፣ ኮንፈረንሶችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን፣ የሰንበት ትምህርቶችን፣ … የመሳሰሉ መንፈሣዊ ስብስቦችን ብንቆጥር እጅግ በጣም ብዙ እንደሆኑ ለመገመት አያስቸግርም።

 

ክርስቲያኖች በአንድ ላይ ተሰባስበው እግዚአብሔርን ሲያከብሩ፣ ወደ አምላካቸው ሲፀልዩና የመስቀሉን ኃይል ሲያውጁ ማየት እጅግ የሚያስደስትና ሊበረታታ የሚገባው ነው። መቋሚያና ጸናጽል በእጆቻችን ይዘን “ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ፣ ዘምሩ ለንጉሥነ ዘምሩ” እያልን በወረብ ለአምላካችንና ለንጉሣችን መዘመራችን፣ በጊታርና በሳክስፎን “በምስጋና ሆ” እያልን በመቅደሱ ውስጥ ማሸብሸባችን መልካም ነገር ነው።

 

ነገር ግን እነዚህ ሁሉ መንፈሣዊ ተግባራቶቻችን ምን ያህል በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት እንዳላቸው ብንጠይቅና ብንመረምር ግን አብዛኞቻችን የምንገረም ነው የሚመስለኝ።

 

እንደሚታወቀው በኦርቶዶክስም ሆነ በሌሎች አብያተ ክርስትያናት ውስጥ የበላይ የሆነውና ሥልጣን ያለው የእግዚአብሔር ቃል ነው። ይህ የእግዚአብሔር ቃል ደግሞ የሚገኘው በመጽሐፍ ቅድስ ውስጥ ነው። የምናደርጋቸው መንፈሣዊ ተግባራት በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ይኖራቸው እንደሆነ ለማወቅ ተግባራቶቻችንን በመጽሐፍ ቅዱሱ ውስጥ ባለው በእግዚአብሔር ቃል መመዘን መቻል ያስፈልጋል።

 

የመስቀል ትርጉም

ከጥቂት ቀናት በፊት የመስቀልን በዓል አክብረናል። መስቀል ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኔንና እናንተን ለማዳን የተሰቀለበት በመሆኑ በክርስቲያኖች ዘንድ ትልቅ ቦታ ያለው የክርስትናም ምልክት የሆነ ነው።

 

መስቀልን በምንመለከትበት ጊዜ፣ ከላይ ወደ ታች የሆነ እንጨት እናያለን። ከላይ ወደ ታች በሆነው እንጨት ላይ በአግድም የሚያልፍ ከቀኝ ወደ ግራ የሆነ ሌላ ሁለተኛ እንጨት አለ። ሁለቱ እንጨቶች ባይገናኙና እንዲሁ ጎን ለጎን ቢተከሉ መስቀል መሆናቸው ይቀራል። እንጨቶቹ መስቀል እንዲሆኑ ካስፈለገ የግዴታ አብረው መገጣጠም አለባቸው። ይሄኛው ያለዚያኛው፤ ያኛው ያለዚኛው ትርጉም የለሽ ነው የሚሆኑት።

 

ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ላይ ከላይ ወደ ታች ያለው እንጨት አንድ ነገርን ያመለክታል። እሱም በምድር የምንኖረውንና የጠፋነውን እኛን መድኃኒዓለም መንገድ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር እንዳቀረበን የሚገለጽ ነው። ምድርን ከሰማይ የማገናኘት ታላቅ የደህንነት ሥራ ማለት ነው።

 

መስቀሉ ላይ ወደጎን ያለው ሁለተኛው እንጨት ደግሞ ብዙዎቻችን ብዙ ጊዜ የማናስበው፣ በዚህ ጽሑፍ ትኩረት ልሰጠበት የምፈልገውን አንድ ሌላ ቁልፍ ነገርን ያመለክታል። እርሱም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሲሞት ወንድም ከወንድም መታረቅና መገናኘት እንዳለበት የሚያሳይ ነው።

 

እግዚአብሔር ፀሎታችንን ለምን አይሰማም?

እንግዲህ የመስቀሉ ምስጢር፣ የእግዚአብሔርን ስም እየጠሩ በመቀደስና በማስቀደስ፣ በመጾምና በመፀለይ፣ መጽሐፍ ቅድስን በማንበብና የሚነበበውን በማዳመጥ፣ በመዘመርና መዝሙርን በመስማት ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን፤ ከዚያም አልፎ የሄደ፣ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በማገልገልም ላይ ያተኮረ እንደሆነ እናያለን። ወደ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሳንመለከት ወደ እግዚአብሔር ብንፀልይ፤ ፀሎታችንን እግዚአብሔር አይሰማም። አራት ነጠብ።

 

ይህን ሃሳብ የበለጠ ለማብራራት ይረዳኝ ዘንድ የሚከተሉትን ሦስት ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ እጠቅሳለሁ፦

 

“ነገር ግን የዚህ ዓለም ገንዘብ ያለው ወንድሙም የሚያስፈልገው ሲያጣ አይቶ ያልራራለት ማንም ቢሆን የእግዚአብሔር ፍቅር በርሱ እንዴት ይኖራል? ልጆቼ ሆይ በሥራና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት አንዋደድ።» 1ኛ ዮሐንስ ም. 3፣ ቁ. 18

“እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ማንም ወንድሙን ቢጠላ ሀሰተኛ ነው። ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?“ 1ኛ ዮሐንስ ም. 4፣ ቁ. 20

«በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል። እናንተ ርጉማን፤ ለሰይጣንና ለመላዕክቱ ወደተዘጋጀው ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፣ ተጠምቼ አላጠጥችሁኝምና፣ እንግዳ ሆኔ አልተቀበላችሁኝምና፣ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፣ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና። እነርሱም ደግሞ ይመልሱና “ጌታ ሆይ ታርዘህ ወይስ ታመህ ወይስ ታስረህ መቼ ነው አይተን ያላገለገልንህ?” ይሉታል። ያን ጊዜ “እውነት እላችኋለሁ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁት፤ ለእኔ ደግሞ አላደረጋችሁትም” ብሎ ይመልስላቸዋል» የማቴዎስ ወንጌል ም. 25፣ ቁ. 44-45

 

ከመጽሐፍ ቅዱስ ከላይ የተጠቀሱት ሦስቱ ጥቅሶች፤ በማያሻማ ሁኔታ በሰዎች ዘንድ ያለው የእግዚአብሔር ሃሳብ ምን እንደሆነ የሚገልጹ ናቸው። እግዚአብሔርን ማምለክና መውደድ ሰውን ከማገልገል ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ነው የምናየው። ወደ ጎን ወደ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን የማንመለከት ከሆነ፣ የተጎዱትንና ከሁላችን የሚያንሱትን የማናነሳ ከሆነ፣ የፈለገ መንፈሣዊ ተግባራትን ብናደርግ፣ የፈለገ ያሬዳዊ ዜማ ብናውቅ፣ የፈለገ ቴዎሎጂ ተምረን ግሪክና እምብራይስጥን ብንተረጉም፣ የፈለገ የቤተክርስቲያን ሹመት ቢኖረን፣ የፈለገ ሁዳዴና ፍልሰታን ብንጾም፣ የፈለገ በየከተሞች የሚደረጉ መንፈሣዊ ኮንፈረንሶች ብንካፈል፣ … እነዚህ ሁሉ ኃይማኖታዊና መንፈሣዊ ሥራዎቻችን ለብቻቸው እግዚአብሔርን አያስደስቱትም።

 

ምንም እንኳን ያማሩ ካባዎችን ለብሰን የመስቀል በዓልን ብናከብርም እውነተኛውን መስቀል ማክበር ተደርጎ ለብቻው ሊቆጥር አይችልም። በስቴዲየም ድምፃችንን ከፍ አድርገን እልልታውንና ሃሌሉያውን በጩኸት ብናቀልጠው፣ እልልታችንና ጩኸታችን ከደመናው አልፎ አይሄድም።

 

በኢሳያስ ምዕራፍ አንድ ቁጥር ከ11 - 15 ላይ ከላይ ያቀረብኩትን ሃሳብ የበለጠ ያሰፋዋል።

 

“የመሥዋዕታችሁ ብዛት ለኔ ምን ይጠቅመኛል? ይላል እግዚአብሔር። የሚቃጠለውን የአውራ በግ መሥዋዕትንና የፍሪዳን ስብ ጠግቤያለሁ፤ የበሬና የበግ ጠቦት የአውራ ፍየልም ደም ደስ አያሰኘኝም። በእኔ ፊት ልትታዩ ብትመጡ ይህን የመቅደሴን አደባባይ መርገጣችሁን ከእጃችሁ የሚሻ ማን ነው? ምናምንቴውን ቁርባን ጨምራቹህ አታምጡ፤ እጣን በእኔ ዘንድ አስጸያፊ ነው። መባቻችሁንና ሰንበታችሁንም በጉባዔ መሰብሰባችሁን አልወድድም፤ በደልንም የተቀደሰውንም ጉባዔ አልታገስም። መባቻችሁንና በዓላቶቻችሁን ነፍሴ ጠልታለች፤ ሸክም ሆነውብኛል፤ ልታገሳቸውም ደክሜያለሁ። እጃችሁንም ወደ እኔ ብትዘረጉ ዓይኔን ከእናንተ እሰውራለሁ። ልመናንም ብታበዙ አልሰማችሁም።»

 

እዚህ ላይ የምትፀልዩትን ፀሎት አልሰማችሁም ነው እግዚአብሔር የሚለን። እጆቻችን በመስቀል አደባባይ፣ በየስቴዲየሙ ሆነ በየቅዳሴዎችና በየኮንፈረንሶች ብንዘረጋ ፊቱን እንደሚያዞር ነው የሚነግረን።

 

ለምን እግዚአብሔር መንፈሣዊ ጉባዔያችንን እንደሚጸየፍ፣ ለምን ፀሎታችንን እንደማይሰማ በዚሁ ኢሳያስ ምዕራፍ አንድ ውስጥ ወረድ ብለን ከቁጥር 16 - 17 ላይ መልሱን እናገኛለን።

 

“እጆቻችሁ ደም ተሞልተዋል። ታጠቡ፣ ሰውነታችሁንም አንጹ። የሥራችሁን ክፋት ከዓይኔ ፊት አስወግዱ። ክፉ ማድረግን ተዉ። መልካም መሥራትን ተማሩ። ፍርድን ፈልጉ። የተገፋውን አድኑ። ለድሃ አደጉ ፍረዱለት። ስለ መበለቲቱ ተሟገቱ።»

 

ሲል እግዚአብሔር የሚያስደስተውን ተግባራት በመዘርዘር፣ ፀሎትም ሆነ በመቅደስ የሚደረጉ ማናቸውም ሥርዓቶች በፊት መቅደም ያላባቸውን የገለጸው።

 

አንድ ወቅት እሥራዔላውያን ጾም ፀሎት አድርገው እግዚአብሔር ፊቱን ያዞረባቸው ጊዜ ነበር። የዚህን ጊዜ እየጾሙ እየፀለዩ ለምን እግዚአብሔር እንደተዋቸው መጠየቅ ጀመሩ። በኢሳያስ ምዕራፍ 58 እንደተጻፈውም እግዚአብሔርም ለምን ፀሎታቸውንና ጾማቸውን እንደማይሰማ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፦

 

“ስለምን ጾምን? አንተም አልተመለከትከንም። ስለምን ሰውነታችንንስ አዋረድን፣ አንተም አላወቅህም? ይላሉ። እነሆ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ። ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ። በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ። እኔ የመረጥኩት ጾም ይህ ነውን? …”

 

እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦

“በእውኑ ይህ ጾም በእኔ ዘንድ የተወደደ ቀን ነውን? እኔ የመረጥኩት ጾም የበደልን እሥራት ትፈቱ ዘንድ፣ የቀንበርን ጠፍር ትለቁ ዘንድ፣ የተገፉትንስ ኣርነት ትሰድዱ ዘንድ፣ ቀንበሩንም ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? እንጀራችሁንስ ለተራበ ትቆርሱ ዘንድ፣ ስደተኞች ድሆችን ወደ ቤታችህ ታገቡ ዘንድ፣ የተራቆቱትን ብታዩ ታለብሱ ዘንድ አይደለምን? (ኢሳ ም. 58፣ ቁ. 6-7)

 

እምነትና ፍትህ አብረው የሚሄዱ ናቸው

በሀገራችን ኢትዮጵያ ያሉትን ችግሮች እዚህ አልዘረዝርም። ሁላችንም የምናወቀውና የምናየው ነው። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን በቀን አንዴ ነው የሚመገቡት። የኑሮ ውድነት ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ነው። ነፍስ የገደሉት በጠራራ ፀሐይ በአደባባይ ሲመላለሱ ወንጀል ያልሰሩ፣ በብርቱካን ሚደቅሳ ላይ እንደደረሰው አይነት፣ በፖለቲካ እምነታቸው ምክንያት ፍርድ እየተዛባ፣ ፍትህ ተጓድሎ ከፍርድ ሥርዓቱ ውጭ በግፍ እየታሰሩ ነው።

 

ታዲያ ይሄ ሁሉ እየሆነ እኛ ክርስቲያኖች ነን የምንል መልሳችን ምንድን ነው? በኛ ወይንም በቤተሰቦቻችን ላይ ችግር እስካልደረሰ ወይንም እኛ እስካልተነካን ድረስ በሌሎች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ የሚደርሰውን ግፍ አይተን ዝም ብሎ ማለፉ እግዚአብሔር የሚወደው ነገር ነውን?

 

አንድ የተማረ ወዳጄ ከቴክሳስ ደወለ። በጨዋታችን መሃል የሀገር ጉዳይ ተነሳና “አንተ ክርስቲያን ነህ። ፖለቲካ ውስጥ ለምን ትገባለህ? ከፖለቲክ ውጣ። አርፈህ በቤተክርስቲያንህ እግዚአብሔርን አገልግል” አለኝ።

 

“የኔ ወንድም። አሁን የማደርገውን የማደርገው እኮ ክርስቲያን ስልሆንኩኝ ነው። የእግዚአብሔር ቃል ለፍትህ እንድንቆም፤ ዜጎች በግፈኞች ሲገፉ ለነርሱ እንድንሟገት፣ ድምፃቸው ለታፈነ ድምፅ እንድሆን፣ የተጣሉትን እንድናስታርቅ አዞናል። የሕሊና እሥረኞች እንዲፈቱ የማደርገው እንቅስቃሴና በማንም ይሰሩ፣ የሚሰሩ ግፎችን ማውገዜ፣ ቅዳሴ ከማስቀደስና በቤተክርስቲያን መድረክ ላይ ከመዘመርና ከመስበክ የበለጠ እግዚአብሔርን የሚያስደስት ነው” የሚል ምላሽ ሰጠሁት።

 

ይህ ሰው ብቸኛ አይደለም። ይህ ሰው የተናገረውን በመጽሐፍ ቅዱስ የማይደገፍ አመለካክት ያላቸው፣ ከኦርቶዶክስም ከወንጌላዊ አብያተ ክርስቲያናትም እጅግ በጣም ብዙ ናቸው።

 

ተራው ምዕመን የእግዚአብሔርን ቃል ጠንቅቆ ካለማወቁ የተነሳ ይህን አይነት አስተሳሰብ ቢኖረው ብዙ አልደነቅም። ነገር ግን ቄሶችና ፓስተሮች፣ ዲያቆናትና የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ነን የሚሉ ግን፤ ቃሉን በድፍረት ያለመሸፋፈን ማስተማር ሲገባቸው፤ ትክክለኛ የወንጌልን ቃል ሸፍነው፣ እውነትን ደብቀው፣ ለጥቅማቸው በማደር፣ ግፍ ሲሠራ ዝም በማለት የኃጢያት ተባባሪ መሆናቸው ግን ያሳዝናል።

 

የኦርቶዶስ ቤተክርስቲያን መንፈሣዊ አባቶችን ብንመለከት እራሳቸው የወንጌል አቡጊዳ እንደገና መማር ያለባቸው ናቸው እላለሁ። መስቀል ይዘው፣ ጥምጥም ጠምጥመው፣ ካባ ደርበው ይዞራሉ። በየቦታው የከበሬታ ቦታ ይፈልጋሉ። ነገር ግን የፍትህ የፍቅር የይቅርታ ጌታ የሆነውን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን እራሳቸውንና ጥቅማጥቅምችን የሚሰጣቸውን ምድራዊ ባለሥልጣናትን ያገለግላሉ። ምዕመናንን ለሁለት ከፍለው፣ መስማማት አቅቷቸው፣ እርስ በርስ እየተወጋገዙ የጌታችንን ስም ያሰድባሉ።

 

በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትም ዘንድ በአደባባይ ጎልቶ አልወጣም እንጂ ተመሳሳይ ሁኔታ ነው ያለው። ለምሳሌ በቶሮንቶ ከተማ ወደ ሰባት የሚሆኑ የወንጌላዊ ቤተክርስቲያናት አሉ። እነዚህ ቤተክርስቲያናት ቁጥራቸው የበዛው፣ የምዕመናን ቁጥር አድጎ፣ ቦታ ጠቦ ቢሆን አንድ ነገር ነበር። ነገር ግን አገልጋይ ነን የሚሉ፣ እርስ በርስ በመጣላታቸውና እግዚአብሔርን ከማክበር ይልቅ የእራሳቸውን ክብርና ጥቅም በማስቀደማቸው እንጂ።

 

ግፍን ማወገዝ ከእግዚአብሔር ሰው ይጠበቃል

አሁን በኤርትራ እየተደረገ እንዳለው፣ በደርግ ዘመን በርካታ ወንጌላዊ አብያተ ክርስቲያናት ተዘግተው ነበር። ብዙዎች በእምነታቸው ምክንያት ተገድለዋል። ብዙዎች ታስረዋል።

 

አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የኢህአዲግ መንግሥት፣ ያኔ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን ከፍቶ በማያጠራጥር ሁኔታ የዜጎች የኃይማኖት ነፃነት እንዲረጋገጥ አድርጓል። ይህ በጎ ሆኖ እያለ፣ የተዘጉ ቤተክርስቲያናትን ኢህአዲግ መክፈቱን እንደትልቅ ውለታ ቆጥረን አሁን ያለው መንግሥት ግፍ ሲሰራ ዝም ማለትና በጭፍን ይህን መንግሥት መደገፍ ትልቅ ስህተት ነው።

 

እዚህ ላይ በ”ጭፍን” የሚለው ቃል ላይ ላሰምረበት እወዳለሁ። አሁን ያለውን አገዛዝ መደገፍ በራሱ ችግር የለውም። ነገር ግን ማንም ጥሩ ሲሠራ ማመስገንና እውቅና መስጠት ተገቢ እንደሆነው ሁሉ፤ ስህተት ሲሠራና ግፍ ሲፈጸም አቋማችንን በግልጽ ማሳወቅና ማውገዝ ይኖርብናል። እንደእግዚአብሔር አገልጋዮች ባለሥልጣናት ግፍ ሲሠሩ እኛ ድምፃችንን ካላሰማን ማን ነው ታዲያ የሚያሰማው?

 

ሄሮድስ አንቲፓስ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢያት በሠራ ጊዜ፣ መጥምቁ ዮሐንስ በአደባባይ በድፍረት ነው የንጉሡን ግፍ ያወገዘው። ንጉሡ ንስኀ ይገባ ዘንድ አስጠነቀቀ። ግፍ ሲሠራ መጥምቁ ዮሐንስ ዝም አላለም።

 

ንጉሥ ዳዊት ሥልጣኑን ተጠቅሞ ኦሪዮን የሚባልን የአንድ ወታደሩን ሚስት ደፈረ። እርሷም ነፍሰ ጡር ሆነች። ንጉሡ የሠራው ኃጢያት እንዳይታወቅበት ኦሪዮንን በዘዴ አስገደለው። ግፍ ተሠራ። የዚህን ጊዜ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሆነው ነብዩ ናታን በድፍረት ወደ ንጉሡ ገባ። ንጉሡን ፊት ለፊት ገጠመ። ንጉሡ እግዚአብሔርን እንዳሳዘነ በኃይል በመናገር ንስኀ እንዲገባ አስጠነቀቀ። ፈርቶ ግፍ ሲሠራ ዝም አላለም።

 

ወደ ዘመናችን ስንመለስ ደግሞ በአሜሪካ ሀገር፣ ቄስና የእግዚአብሔር አገልጋይ የነበሩት ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ በመንግሥት ይፈጸም የነበረውን ዘረኝነት የሞላበት ግፍ ወደ እሥር ቤት እስኪወረወሩ ድረስ አወገዙ። ምዕመኖቻቸውና እግዚአብሔርን የሚፈራ ህዝብ ሁሉ ለፍትህና ለእኩልነት፤ ለሰብዓዊ መብት መከበር እንዲቆም አስተማሩ። እኝህ ሰው፣ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶችን ሁሉ ሳይቀር ፊት ለፊት በሚሠሩት ሥራ ተቃወሟቸው። ግፍ ሲሠራ ዝም አላሉም።

 

በሀገራችን ኢትዮጵያም ጣሊያን በግፍ በወረረን ጊዜ አቡነ ጴጥሮስ የሚባሉ ለእውነት፤ ለፍትህና ለነፃነት እራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ታላቅ የእምነት አባት እንደነበሩንም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚያወቀው ነው። እኝህ ታላቅ መንፈሣዊ አባት ግፍ ሲሠራ ዝም አላሉም።

 

እንግዲህ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ነብዩ ናታን፣ ቄስ ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ እና አቡኑ ጴጥሮስ መንፈሣዊ ማዕረጋቸውን ይዘው፣ የኃይማኖት ውጫዊ ሥርዓት እየጠበቁ፣ በምድራዊ ጥቅም ተንበሻብሸበው፣ ግፍ ሲሠራ አይተው ዝም ብለውና ለራሳቸው ብቻ ቆመው ማለፍ ይችሉ ነበር።

 

ነገር ግን እነዚህ አባቶች ወደ ጎን ወደ ተገፉት፣ ወደ ወንድሞቻቸው፣ ወደ ተራቡት፣ በግፍ ወደታሰሩት፣ ሚስቶቻቸው ወደተደፈሩባቸው፣ ቀንበር ወደ በዛባቸው ተመለከቱ። ፍትህ ሲዛባ ተቆጡ። ለመበለቶችና ደጋፊ ወገን ለሌላቸው ተሟገቱ። እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አንፈራም አሉ።

 

ወድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ!

ዓላማዬ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን መኮነን አይደለም። ዓላማዬ እውነተኛ የወንጌል ምስጢር ምን እንደሆነ ለመግለጽና በአንዳንድ መንፈሣዊ አባቶች የተሳሳተ አመለካከት ተታለን፣ እግዚአብሔር የሚያስደስተውን ለፍትህ የመቆምን ነገር ወደኋላ እንዳንል ለማሳሰብ ነው።

 

የእግዚአብሔር ሃሳብ ፍትህ ነው። የእግዚአብሔር ሃሳብ ሠላም ነው። የእግዚአብሔር ሃሳብ ወንድማማችነት ነው። የእግዚአብሔር ሃሳብ መረዳዳትና መደጋገፍ ነው። የእግዚአብሔር ሃሳብ ከራሳችን አልፈን ለሌላው መቆም ነው። የእግዚአብሔር ሃሳብ ይቅር ተባብለን እርስ በርስ መቀባበል ነው።

 

እንግዲህ እንደሀገር ወደፊት ማደግ ከተፈለገ አንዱ ሲወድቅ ሌላው ያንሳ! አንዱ ሲጠቃ ሌላው ይቆጣ! ዝም አንበል! ለእውነት፣ ለፍትህ፣ ለሠላም እና ለነፃነት እንነሳ! ይህንንም እግዚአብሔር ይወደዋል!


 

ግርማ ካሣ

መስከረም 20 ቀን 2002 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ