Displacement and killings in the western Benishangul Gumuz region

በምዕራብ ወለጋ ከግድያ ተርፈው የተፈናቀሉ ዜጎች በስደተኞች ካምፕ

መንግሥት ሆይ! ከዚህ በኋላ ለዜጐች ሞትና መፈናቀል ምክንያት የኾኑትን አካላት ለፍርድ ያቅርብልን

ኢትዮጵያ ዛሬ (ርዕሰ አንቀጽ) - ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበራት ድርጅት ምክር ቤት “ኢትዮጵያ አሸንፋለችና፤ እናመሰግናለን!” በሚል መሪ ቃል ባዘጋጀው መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተገኝተው ነበር።

በዚህ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ንግግር ብልጽግና በዘንድሮው ምርጫ 2013 ካሸነፈ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ሊኖራቸው የሚችለውን ግንኙነት በግልጽ አስቀምጠዋል።

ይህንንም “ምርጫ ቦርድ ብልጽግና አሸንፏል ቢል፤ ብልጽግና ምርጫውን ሙሉ ለሙሉ እንዳሸነፈ አይወስድም።” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳሸነፈ ስለሚወስድ፤ ከታችኛው እርከን ጀምሮ እስከ ላይኛው የአስፈጻሚ እርከን ድረስ ከሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደተወዳደሩበት ክልልና ሁኔታ፤ እንደ አቅማቸው መጠን፤ በመንግሥት ውስጥ በጋራ ኢትዮጵያን ለማሸነፍ በእኛ በኩል ዝግጁነቱ አለ” በማለት ገልጸውታል።

በዚሁ ንግግራቸው እንዳከሉትም “እስክንወዳደር ይቆይ ያልንበት ምክንያት ማን በምን ያህል እንደሚደገፍ፤ ማን የት እንደሚደገፍ ሳይታወቅ በስመ ፖለቲካ የመጣውን ሁሉ ወደ ሥልጣን ድርድር ብናስገባ፤ አሁን ባለንበት ሁኔታ ኢትዮጵያን ለማሻገር ስለሚያስቸግር እንጂ ከብልጽግና የማያንሱ ሰዎች በየፓርቲው እንዳሉ ካለማመን አይደለም” ብለዋል።

ይህ መልካም የሚባል እሳቤ ነው። ከሐሳብ ባሻገር በተግባር ሲለወጥ የሚያስገኘው ለውጥ በወቅቱ ሊመዘን ይችላል። አሁን ላይ ኾነን ስናየው ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲሱ መንግሥት ውስጥ ቦታ እንዲኖራቸው ይደረጋል መባሉ ያልተለመደ የፖለቲካ አካሔድ ከመኾኑም ባሻገር፤ በአገረ መንግሥት ምሥረታው የብዙኀንን ተሳትፎ እንዲያጐላ ያደርጋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ ይህንን ሐሳብ እንዴት ይቀበሉታል የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ኾኖ፤ በአዲሱ መንግሥት ውስጥ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቦታ እንዲኖራቸው በዚህን ያህል ደረጃ መታሰቡ ትልቅ ነገር ነው። ከአሸናፊው ፓርቲ ሌላ በቀጣዩ መንግሥት ውስጥ የተፎካካሪ ፓርቲዎች በምርጫው ድምፅ ባያገኙ እንኳን ታስፈልጉናላችሁ መባሉም ቢኾን በመልካም የሚታይ ነው። ምናልባትም ለዚህች አገር ፖለቲካዊ ቀውስ በተወሰነ ደረጃም ቢኾን መፍትሔ ሊሰጥ ይችላል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ዋናው ግን በተግባር የሚታየው ውጤት ነው።

እንዲህ ባለው መንገድ አዲሱ መንግሥት ኃላፊነቱን ይረከባል ብለን እናስብና፤ በቀጣዩ መንገድ ሕዝብ እንዲኾንለት የሚፈልገውን አንድ ነገር ብቻ ነጥለን እንይ። ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ለጆሮ የሚከብዱ፣ ለማመን የሚያስቸግሩ አሰቃቂ ግድያዎችና መፈናቀሎች እንዲሁም የንብረት መውደሞች ደርሰዋል።

የሰው ልጅ ተዘቅዝቆ ተሰቅሏል። ኾን ተብሎ በሚፈጠሩ ፀብ አጫሪነት የአንድ አገር ልጆች ነፍስ እንዲጠፋፉ ተደርጓል። እትብቱ የተቀበረበት ቀዬ የአንተ አይደለም ተብሎ እንዲፈናቀል ተደርጓል። ይህ እጅግ አሳዛኝ በኢትዮጵያ ምድር ይፈጠራል ተብሎ የማይታሰብ ቢኾንም፤ ኾኗል። ተከሰቷል። ከሁሉም በላይ ብሔርን መሠረት ያደረገው ጥቃት የዚህች አገር ፈተና ኾኖ ቆይቷል። እንዲህ ያሉ እንደ አገር አንገት የሚያስደፉ ድርጊቶችን ግን ለማስቆም ሳይቻል ዓመታት የቆዩበቱ ምክንያት ደግሞ የበለጠ አሳማሚ ነበር። ዛሬም ጥዩፍ በኾነው ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን መንግሥት ሊከላከል ያልቻለበቱ ምክንያት አሁንም ድረስ እንቆቅልሽ ቢኾንም፤ በሕይወት ተርፈው ነገም ጥያቄ የሚያቀርቡ ዜጐቻችን ግን አሉ። ማንነቱን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ለምን በርክቶ ታየ? መንግሥትስ ከእነዚህ ሰለባዎች ፊት ኾኖ ኃላፊነቱን አልተወጣም የሚለው ጥያቄ አሁንም ያለ ቢኾንም፤ እንዲያውም ከማንነት ጋር የተያያዙ ጥቃቶች እንደ ቀድሞው የማይሰሙ ቢኾንም፤ ከዚህ በኋላ ላለመከሰታቸው እርግጠኛ መኾን አይቻልም።

ስለዚህ አዲሱ መንግሥት ከወቅታዊው አገራዊ ጉዳይ አንጻር በርካታ የቤት ሥራዎች ከፊት ለፊቱ ቢኖሩም፤ እንደ አለፉት ሦስት ዓመታት በምንም ምክንያት ዜጐች በማንነታቸው፣ በብሔራቸው፣ በሃይማኖታቸው መገደል የሌለባቸው ስለመኾኑ ማረጋገጫ ሊሰጥ ይገባል።

ከዚህ በኋላ ሊቀርብ የሚችል ሰበብ ሊኖር አይገባም። ማንነት ላይ ያተኮረ ጥቃት ፈጻሚዎች እጃቸውን እንዳያነሱ መንግሥት ያለውን አቅም ተጠቅሞ ሃይ ሊላቸው ይገባል። በተለይ ደግሞ በማንነት ላይ የተመሠረተ ጥቃት ፈጻሚዎች ከጀርባቸው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ባለሟሎች እንዳላቸው ይታመናልና፤ በሕዝብ ላብ ከሚሰበሰብ ቀረጥ እየወጣ ደምወዝ የሚከፈላቸውን እነዚህን ግለሰቦች ነቅሶ ማውጣት የአዲሱ መንግሥት ኃላፊነት ነው። ዜጐች ፀሐይና ዝናብ በላያቸው እየወረደ ሲመርጡ፤ የሚመረጠው መንግሥት የመጀመሪያው ሥራ ላለፉት ዓመታት የሰማናቸውን ሰቅጣጭ ድርጊቶች እንዲያስቆም ነው።

አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ድምፅ ሲሰጥ በልቡ አዲሱ መንግሥት ሰላም ያምጣልን ብሎ ነው።

በተለይ እስካሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ማስቆም ካልቻለባቸው ምክንያቶች አንዱ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዳይወጣ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት አይደለም የሚል ነበር። ይህ በብዙ መልኩ አሳማኝ ባይኾንም፤ ይህም ከኾነ አሁን በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ይኖረናል እና ይህ የተመረጠ መንግሥት በሕግ የተሰጠውን ኃላፊነት ይወጣ!!

ከዚህ በኋላ የሚያሳብብበት ምክንያት አይኖርም። ይህንን የሕዝብ ምኞት ለማሳካት ግን መንግሥት ብቻውን የሚወጣው አለመኾኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። መንግሥት ይህንን ያድርግ ስንል፤ እኛስ ምን እናግዝ የሚል አመለካከት ሊኖረን ይገባል። አገር የምትቆመው በትብብር እና በአንድነት ነው። ስለዚህ ለአገራችን ሰላም ሁሉም እንደ ዜጋ ሊያበረክተው የሚገባው ነገር ሊኖረን ይችላል።

ወደ ግጭት የሚወስዱ ትርክቶችን ወደ ጐን በማድረግ አንዳችን ለሌላችን ጌጥ አለመኾናችን አስበን፤ ወደ መልካም የሚመሩን ላይ በማተኮር፤ ዜጐች ነገሮችን ለሚያባብሱ ትርክቶች ጆሮ መንፈግም ከቻሉ፤ ሰላም ለማምጣት ሁነኛ ሚና ይጫወታሉ።

የተፎካካሪ ፓርቲዎችም በአዲሱ መንግሥት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ቦታ የሚኖራቸው ከኾነ፤ ከአደነቃቃፊ ነገሮች ተቆጥበው በቀደሙት ዓመታት የታዩትን ሰቅጣጭ ድርጊቶች በማስቆም የራሳቸው ድርሻ ይኖራቸዋል ማለት ነው።

ስለዚህ መንግሥት ሆይ! ከዚህ በኋላ ለዜጐች ሞትና መፈናቀል ምክንያት የኾኑትን አካላት ለፍርድ ያቅርብልን። ሰላማችንን ለማረጋገጥ ሰበብ የማይሻ ስለመኾኑም ሕዝብ በደንብ ያስታወቀ ሲሆን፤ መንግሥት ሆይ! የእስከ ዛሬው ይበቃናል ሰላማችንን አስጠብቅ። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ