Getachew Balcha

አቶ ጌታቸው ባልቻ፣ የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ

ኦነግ ሸኔን ከመደምሰስ ባሻገር ከዘመቻው ጋር ያልተባበሩ እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ የመንግሥት አመራሮችም ከመጠየቅ አያመልጡም ተብሏል

ኢዛ (ረቡዕ መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 7, 2021)፦ ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የተሰማው አንድ መረጃ በብርቱ የሚጠበቅ፤ ምናልባትም አገሪቱን በአሁኑ ሰዓት ያለችበትን ያለመረጋጋትና ዘር ተኮር ጭፍጨፋን ያስቀራል ተብሎ የተገመተ ነው። ይህ ከክልሉ መንግሥት የተሰማው ዜና በአሁኑ ወቅት በጅምላ ጭፍጨፋ ቀዳሚ ተጠያቂ የኾነውን የኦነግ ሸኔ በአሥራ አምስት ቀን ውስጥ ልክ አስገባዋለሁ ማለቱ ነው።

የክልሉ መንግሥት የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ለሸገር እንደገለጹት፤ ኦነግ ሸኔን በ15 ቀን ውስጥ ድባቅ መትቼ ክልሉን ሰላም ለማድረግ እሠራለሁ ነው ያሉት።

ኦነግ ሸኔን ለመደምሰስ 15 ቀን ስጡኝ ያለው የኦሮሚያ ክልል ይህንን እቅዱን ለማሳካትም የክልሉ ጸጥታ ኃይል ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በተቀናጀ ሁኔታ ኦነግ ሸኔ ላይ እርምጃ እየወሰደ መኾኑን ይኸው የኃላፊው ማብራሪያ አመልክቷል።

ኦነግ ሸኔን ከመደምሰስ ባሻገር ከዘመቻው ጋር ያልተባበሩ እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ የመንግሥት አመራሮችም ከመጠየቅ አያመልጡም ተብሏል።

የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ጨምረው እንደገለጹት፤ በምዕራብ ኦሮሚያ ባለፈው ሳምንት የተፈጠረውን ግድያ ተከትሎ ሕብረተሰቡ በየአካባቢው የተጠናከረ ጥበቃ እያደረገ ነው ብለዋል።

የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊዎች ይህንን መግለጫ የሰጡት ትናንት በኦሮሚያና በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች መካከል በዚሁ የግድያና የዘር ተኮር ጭፍጨፋ ጉዳይ ዙሪያ ከመከሩ በኋላ መኾኑ፤ የዛሬው የኦሮሚያ ክልል መግለጫ ከትናንቱ ምክክር ጋር እንዲያያዝ አድርጐታል።

በያዝነው ዓመት 2013 ዓ.ም. ኅዳር ወር መጨረሻ ላይ አቶ ጌታቸው ባልቻ “በሕወሓት ተላላኪው ኦነግ ሸኔ ላይ የማያዳግም እርምጃ እየወሰድን ነው” ሲሉ ለመንግሥት መገናኛ ብዙኀን፤ በተለይም ለኢዜአ ገልጸው እንደነበር አይዘነጋም። የዛሬ አራት ወር በዚያው ገለጻቸው ላይ “በአሁኑ ወቅት በኦነግ ሸኔ ላይ በተወሰደ የማያዳግም እርምጃ በሁሉም የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ሰላም እየሰፈነ ነው” በማለት ተናግረው የነበረ ሲሆን፤ ከዚያ ወዲህ በርካታ ንጹሐን ላይ የዘር ተኮር ጭፍጨፋና ግድያ ሲፈጸም መቆየቱ ይታወቃል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ