የብልጽግና ፓርቲ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ አወጣ
ብልጽግና ፓርቲ
“የገጠመን ጦርነት የሞት ሽረት ነው”
ኢዛ (ዓርብ ሚያዝያ ፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 10, 2020)፦ የኮሮና ቫይረስ እንደ አገር የሰነቅናቸውን ሕልሞች ሊነጥቀን የመጣ ጠላት በመኾኑ፤ የምናደርገው ጦርነት በሁሉም መስክ የሞት ሽረት ትግል እንደሚኾን የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።
የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያደረገውን ስብሰባ ተከትሎ ባወጣው መግለጫ አገሪቱ አሁን የገጠማትን ችግር በሰፊው በመተንተን ወረርሽኙ በአገር ደረጃ የተወጠኑ ውጥኖችን ለመንጠቅ የመጣ ሲል ገልጾታል።
በመኾኑም ይህንን ጦርነት በሁሉም መስክ ማሸነፍ የሞት ሽረት ትግል መኾኑንና፤ ይህንን ትግል አሸንፎ የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ኃላፊነት መኾኑንም በመግለጫው አስታውቋል። ሙሉ መግለጫው ከዚህ በታች ቀርቧል። (ኢዛ)
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ያደረገውን ስብሰባን ተከትሎ የተሠጠ መግለጫ
የብልጽግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዚያ 2 ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ዓለም አቀፉ የኮሮና ወረሽኝ በአገራችን ሕዝቦች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ደኅንነት ላይ ሊያሳርፍ የሚችለውን ተፅዕኖ ለመመከት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በዝርዝር ሲመክር ቆይቶ የተለየዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
ክቡራትና ክቡራን ኢትዮጵያውያን
ውድ የአገራችን ሕዝቦች
ፓርቲያችን አገራዊ ለውጡን በመምራት ሒደት እያጋጠሙ የነበሩ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የደኅንነት ችግሮችን ለመቅረፍ የተቀናጀና መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ተጨባጭ ውጤቶችን አምጥቷል። ለውጡ ኢትዮጵያን ፍትሕ የሰፈነባት፣ በዴሞክራሲ የዳበረች፣ በሰብአዊ መብት ጥበቃ የተመሰገነች፣ በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ በሰላምና በደኅንነት የተረጋጋች አገር ማድረግ መሆኑን በማመን ከዴሞክራሲ ሪፎርሙ ጎን ለጎን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ጠንካራ የሕግ ማስከበር ተግባራት ለፍሬ በቅተው ከሞላ ጎደል ወደ ሰላማችን ተመልሰናል። ለሰብአዊ መብትና ለጋራ ተጠቃሚነት ዕንቅፋት የሆኑ ሕጎችና አሠራሮች ተስተካክለዋል። በሁሉም አካባቢዎች ተፈናቅለው የነበሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከሞላ ጎደል ሁሉም ወደ ቀያቸው ተመልሰው የዕለት ተዕለት ኑሮ ጀምረዋል። በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝቡን እያማረሩ የነበሩ ታጣቂዎች እና የጎበዝ አለቆችን አደብ ለማስገዛት በተወሰደ ርምጃ ሥርዓት አልበኝነትን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ ተችሏል።
ኢኮኖሚያችን ከቀውስ ወጥቶ ማንሠራራት ጀምሯል። አገራችን ለበርካታ ጊዜ ያካበተችውን መልካም የዲፕሎማሲ ወረት በመጠቀም ከጎረቤት አገራት እና ከተቀረው የዓለማችን ክፍል ጋር ያላት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት ተጠናክሯል። በደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች መካከል፣ በሱዳን የሽግግር ሒደት እና በኬንያ እና ሶማልያ መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የተሠሩ ተግባራት የዲፕሎማሲ ተሰሚነታችንን ያሳደጉ ሆነዋል። ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድን በመከተል በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ብሔራዊ ጥቅማችን ለመጋፋት የሚደረገውን ጥረት ለማክሸፍ በፅናት ታግለናል። በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻችንን መብትና ጥቅም ለማስከበር ተችሏል።
ክቡራትና ክቡራን
በጥቅሉ ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ እያመራ የነበረውን አገራዊ ሁኔታችንን በማስተካከል፣ ስለ ምርጫ፣ ስለ አገራችን ብልጽግና እና ስለ ወደፊቷ ጠንካራ ኢትዮጵያ ማሰብና መስራት በጀመርንበት በዚህ አጓጊ ወቅት በዓለማችን በፍጥነት በመዛመት ሁለንተናዊ ቀውስ እስያስከተለ ያለው የኮሮና ወረርሽኝ በአገራችንም ተከስቷል።
ቫይረሱ እስካሁን 200 በሚጠጉ አገራት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ አስከትሏል፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አጥቅቶ ወደ 100 ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች ደግሞ የሞት ምክንያት የሆነው ይህ ወረርሽኝ ወደ አገራችን ገብቶ 65 ዜጎቻችን ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተረጋግጧል። ከነዚህ ውስጥ ለ2 ዜጎቻችን ኅልፈተ ሕይወት ምክንያትም ሆኗል። ነገ ምን ያህል ዜጎቻችንን እንደሚያጠቃ በርግጠኝነት ባናውቅም ሁላችንም ተረባርበን አስከፊ ጉዳት እንዳያስርስብን መዘጋጀትና ችግሩን ለመሻገር ተስፋችንን ለማስቀጠል መረባረብ ይጠበቅብናል።
የተደቀነብንን ፈተና ለማለፍ፣ በሽታውን ለመከላከል፣ ለማከምና ተዛመጅ ጉዳቶቹን ለመቀነስ እንደ ፓርቲም ሆና እንደ መንግሥትም በትኩረት መንቀሳቀስ አለብን። በዚህ ወቅት ለብልጽግና ፓርቲ ሕዝባችንን ከዚህ ዓለም አቀፋዊ ወረርሽኝ ከመከላከልና ከማዳን የሚበልጥ ተልዕኮ የለም። ፓርቲያችን ከጅምሩ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ለዚሁ ሥራ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ብሔራዊ የወረርሽኝ መከላከል ኮሚቴና ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማቋቋም ከላይ እስከታች ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር አገራዊ ንቅናቄ በመፍጠር እየሰራ ይገኛል። ከ300ሺህ በላይ የሚሆኑ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ያሉ አመራሮቹን ቀዳሚ ተልእኳቸው ወረርሽኙን መከላከል ሥራ አድርጎ አሰማርቷል። ወረርሽኙ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የተወሰዱት እርምጃዎች አበረታች መሆናቸውን የገመገመው ፓርቲያችን የቀጣይ ጊዚያት ዋና ተልእኮና ተግባራችን የኮሮና ወረርሽኝን መከላከል መሆኑን በማመን የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዝርዝር ጉዳዩች ላይ ተወያይቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል።
1ኛ. ከፊት ለፊታችን የተደቀነውን ፈተና በአሸናፍነት ለማወጣትና ሕዝባችንን ከዚህ ዓለም አቀፋዊ ወረርሽኙን መከላከል፤ ማከምና የከፋ ጉዳት ሳያስከትል መቆጣጣር መቻል፤ እንድሁም ተዛመጅ ጉዳቶቹን ትርጉም በለው መልኩ ለመቀነስ፤ በዚህ ወቅት ፓርቲያችን ከዚህ የሚበልጥ ተልዕኮ ያለመኖሩን በመገንዘብ እንደ ፓርቲም ሆና እንደ መንግሥትም ልዩ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ እንዳለብን ከመግባበት ተደርሰዋል።
2ኛ. የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሒደት ነጻ እና ምቹ አገራዊ ሁኔታን ይፈልጋል። በመሆኑም ቫይረሱን ለመቆጣጠር የምንሠራቸው ሥራዎች ከዘላቂ የዴሞክራሲ ግንባታችንን የማይጣረሱ እንዲሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት በየደረጃው የሚወሰዱ ርምጃዎች ሕግና ሥርዓትን የተከተሉ፣ የጀመርነውን የዴሞክራሲ ጉዞ የማያሰናክሉ፣ ነገር ግን ደግሞ ወረርሽኙ የሚፈልገውን የአስቸኳይ ጊዜ ባሕሪያት የተረዱ መሆን እንዳለባቸው መግባባት ላይ ደርሰናል።
3ኛ. ወረርሽኙን በድንገት እንደታወጀብን ጦርነት በመሆኑ በፍጥነት ጥቃት እያደረሰብን ያለና እንደማንኛውም ጦርነት በኢኮኖሚያችን ላይ የራሱን ከባድ ጫና ሊፈጥርብን ይችላል። ይሄንን ቫይረስ ለመቆጣጠር የምናደርገው ዘመቻም ሀብታችንንና የሰው ኃይላችንን ስለሚሻማ በኢኮኖሚያችን ላይ ሊፈጥረው የሚችለው ጫና ከፍተኛ እንደሚሆን እንረዳለን። በመሆኑም የወረርሽኝ ቁጥጥር ሥራችን ኢኮኖሚያችንን በእጅጉ እንዳያናጋና ቀጣይ የብልጽግና ትልማችንን እንዳያደናቅፍ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃትና ገበያውን ለማረጋጋት በርካታ ሥራዎችን መሥራት እንዳለብን ስምምነት ላይ ደርሰናል።
4ኛ. የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት በሚደረጉ ርብርቦች መካከል የሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ እንዳይስተጓጎል፣ የኑሮ ውድነት እንዳይጨምርና የዜጎች መሠረታዊ ፍላጎቶች በተቻለ መጠን እንዳይጓደሉ ለማድረግ ከፍተኛ ዝግጁነት ያስፈልጋል። ወረርሽኙ በዜጎች ሕይወት ላይ የሚያደርሰውን ማኅበራዊ ጉዳት በመንግሥት ዐቅም ብቻ ለመፍታት አይቻልም። ስለሆነም ከመንግሥት በተጨማሪ ሕዝባችን በዳበረ እርስ በርስ የመረዳዳት ባህሉ ተጋላጭ የሆኑትን ወገኖች እንዲታደግ፤ ማስተባበርና ከዚህ አገራዊ ፈተና እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ባቋራጭ ለመክበር የሚፈልጉ ሕገ ወጦችን ከድርጊታቸው ለመግታት ከምንጊዜውም የተለየ የሕግ ቁጥጥር አስፈላጊ እንደሆነ መግባባት ላይ ተደርሷል።
5ኛ. በዚህ የወረርሽ ወቅት ብሔራዊ ደኅንነታችን እና ሉአላዊነታችን አደጋ ላይ እንዳይወድቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ በማድረግ የአገራችንን ብሔራዊ ጥቅም የሚጋፉትን በማናቸውም መንገድ ለመከላከልና አስፈላጊ የሆነውን ርምጃ ሁሉ ለመውሰድ ዝግጁ መሆን እንዳለብን መግባባት ላይ ተደርሷል።
የተከበራችሁ የፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች
ፓርቲያችን ለየትኛውም ፈተና የማይበገር፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በፅናት ታግሎ ማለፍ የሚችል ፓርቲ ለመሆኑ እናንተ ህያዋን ምስክሮች ናችሁ። ዛሬም በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ተጋረጠውን ይህን ክፉ ወረርሽኝ መላው ሕዝባችንን በማስተባበር በድል አድራጊነት እንደምንወጣው ጥርጥር የለንም። ስለሆነም በዚህ ፈታኝና አስቸጋሪ ወቅት ቢቻል ጠላት የሆነውን ኮሮና ቫይረስ በመግደል እራሳችንንና ሕዝቦችን ለማዳን ካልተቻለ ደግሞ እራሳችንን መስዋዕት በማድረግ ይህን ጠላት በመግደል ሕዝቡን ለማዳን በጋራ እንድንረባረብ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን።
የተወደዳችሁ የሕክምና ባለሙያዎች፤
የተሰለፋችሁበት የሕክምና ሙያ ለወገናችሁ ፈውስና መድህን አድርጎ አቁሟችኋልና ሁሌም ክብርና ኩራት ይገባችኋል። ደከመን ሰለቸን ሳትሉ የሕብረተሰባችሁን ጤና ለመጠበቅ ላደረጋችሁት ሁሉ ፓርቲያችን በዚህ አጋጣሚ ምስጋናውን ያቀርባል። ከወረርሽኙ ጋር የምናደርገው ትግል ከማንም በላይ ዛሬም የናንተን ግንባር ቀደም ተሰላፊነትና ቆራጥነት የሚጠይቅ ነው። እንደሁልጊዜው በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆናችሁና በፅናት ቆማችሁ ለወገናችሁ ጤና ዘብ እንደምትሆኑ ፅኑ እምነታችን መሆኑን እየገለፅን ወቅቱ በሚጠይቀው የቁርጠኝነት ደረጃ፣ በጀግንነት እንድትረባረቡ ጥሪያችንን እያቀረብን ፓርቲያችን ምንጊዜም ከጎናችሁ መሆኑን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።
የተከበራችሁ የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች
ዘመናትን በዋጀ የመሥዋዕትነት ታሪካችሁ የአገራችንን ልዕልናና ህልውና ጠብቃችሁ ሰላምና ደኅንነትን አጎናፅፋችሁናል። ዛሬም ከፊታችን የተደቀነው ፈተና የናንተን ቆራጥ ተጋድሎና ጀግንነት ይጠይቃል። በመሆኑም በስምሪታችሁ ሁሉ በቆራጥነት በመሳተፍ አገራችሁንና ሕዝባችሁን ከወቅታዊ አደጋ እንድትታደጉ ፓርቲያችን ጥሪውን ያቀርብላችኋል።
የተከበራችሁ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች
አገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሁላችንንም የተባበረና የተቀናጀ ርብርብ ትፈልጋለች። በመሆኑም የፖለቲካ አመለካከትና ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ ወረርሽኙን ለመከላከል በጋራ እንድንረባረብ ፓርቲያችን ጥሪውን ያቀርብላችኋል።
የተከበራችሁ የአገራችን የሚዲያና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች
ወረርሽኙን በመከላከል ተግባር በግንባር ቀደምትነት ተሰልፋችሁ በየሙያ መስካችሁ ሕዝባችንን ለማስተማር፣ ለማሳወቅና ለማስተባበር እያደረጋችሁት ላለው ጥረት ፓርቲያችን አድናቆቱን ይገልጻል። ወደፊትም ወሳኝ በሆኑት የሙያ መስኮቻችሁ የተዓማኒና የትክክለኛ መረጃ ምንጭ፤ የሕብረተሰባችን የግንዛቤ ማሳደጊያ፣ ማስተማሪያና መደጋገፊያ መድረክ ሆናችሁ እንድታገለግሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ውድ የአገራችን ሕዝቦች የኮሮና ወረሽኝ እንደአገር የሰነቅናቸውን ሕልሞች ሊነጥቀን የመጣ ጠላት ነው። የምናደርገው ጦርነት ሕብረ ብሔራዊ አንድነቷ የጠነከረ፣ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ያረጋገጠችና ለዜጎቿ ምቹ የሆነች፣ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ፣ የምሥራቅ አፍሪካ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ማዕከል የሆነች አገርን ለመገንባት የሚደረግ የሞት ሽረት ትግል ነው።
ይህንን ትግል አሸንፈን የኢዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ሃላፊነት ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን ወራሪም ሆነ ወረርሽኝ ታግሎ እንጅ አሸንፎን አያወቅምና ዛሬም ይህንን ፈተና በፅናት መክተን የብልጽግና ጉዟችንን እንደምንቀጥል ፓርቲያን ፅኑ እምነት አለው። አንድ ሆነን ተጋግዘን እና ተረባርበን አስቸጋሪውን ጉዞ እናልፋለን፤ ወደ ብልጽግና እንሻገራለን። ስለሆነም መላው የአገራችን ሕዝቦች ሁሉንም አቅሞቻችን አስተባብረን ወረርሽኙን በጋራ እንድንከላከል ፓርቲያችን የከበረ ጥሪውን ያስተላልፍላችኋል።
ሁላችንም ኮሮና ቫይረስን የሚከላከለው ሠራዊት አባላት ነን!!
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ሚያዚያ 02 ቀን 2012 ዓ.ም.
አዲስ-አበባ



