በኢትዮጵያ የቫይረሱ ተጠቂዎች 38 ደረሱ
ኮሮና ቫይረስን በምስል ለማሳየት በበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል የተሠራጨ
የ85 ዓመቷ አዛውንት አገግመዋል
ኢዛ (ቅዳሜ መጋቢት ፳፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 4, 2020)፦ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 38 መደረሱን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። የ85 ዓመቷ አዛውንት ማገገማቸው ታውቋል።
ዛሬ ቅዳሜ መጋቢት 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው የጤና ሚኒስቴር መረጃ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 38 የደረሰው አዲስ ሦስት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በመገኘታቸው ነው።
ሦስቱም የውጭ አገሮች ጉዞ ታሪክ ያላቸውና የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው። ተጠቂዎቹ የ29፣ የ34 እና የ35 ዕድሜ ያላቸው ሲሆን፤ ሁለቱ ወንዶች ሲሆኑ፤ አንዷ ሴት ናት።
በዛሬው የጤና ሚኒስቴር መግለጫ በኢትዮጵያ በቫይረሱ መያዛቸው ከተገለጹት ውስጥ በዕድሜ ከፍተኛዋ በመኾን የሚጠቀሱት የ85 ዓመትዋ አዛውንት ማገገማቸው ታውቋል።
እኚህ ኢትዮጵያዊት ማገገማቸው እሳቸውን ጨምሮ እስካሁን ከቫይረሱ ያገገሙት አራት ደርሰዋል። (ኢዛ)



