ቫይረሱ ከተገኘባቸው ጋር ንክኪ ያላቸው 922 ሰዎች ክትትል እየተደረገላቸው ነው
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት
34 በማቆያ ማዕከል ኾነው ውጤት እየተጠባበቁ ነው
ኢዛ (ማክሰኞ መጋቢት ፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 17, 2020)፦ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ከተረጋገጡት አምስት ግለሰቦች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸው 992 ሰዎች ክትትል እየተደረገባቸው መኾኑን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ በሠጠው መግለጫ አስታውቋል።
እነዚህ 992 ሰዎች ባሉበት ቦታ ኾነው ለ14 ቀናት ክትትል የሚደረግላቸው መኾኑንም የጠቀሰው ኢንስቲትዩቱ፤ በቫይረሱ የተያዙት ግለሰቦችም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ብሏል።
እንደ ኢንስቲትዩቱ መረጃ በአሁኑ ሰዓት 1285 የሚኾኑ ግለሰቦች ደግሞ ለ14 ቀን የጤና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይቶ፤ ጤንነታቸው በመረጋገጡ የጤና ክትትላቸው ተቋርጧል።
113 ተጠርጣሪዎች በለይቶ ማቆያ ማዕከል እንዲቆዩና የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸው ከቫይረሱ ነፃ መኾናቸው በመረጋገጡ 74ቱ ወደ ሕብረተሰቡ ተቀላቅለዋል። 34 የሚኾኑት ተጠርጣሪዎች ደግሞ በማቆያ ማዕከሉ ኾነው የላብራቶሪ ሕክምና ውጤታቸውን እየጠበቁ ነው ተብሏል። (ኢዛ)



