PM Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

መዋሐድና መደጋገፍ ካልተቻለ፤ ከምርጫ በኋላ በሐሳብ ብቻ መነጋገር እንደሚቻል ጠቁመዋል

ኢዛ (እሁድ መጋቢት ፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. March 15, 2020)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከብልጽግና ፓርቲ ጋር መዋሐድ የሚፈልጉ ከኾነ ፓርቲያቸው በሩ ክፍት መኾኑን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ እንዲህ ያለውን የፓርቲያቸውን አመለካከት የጠቆሙት፤ ትናንት መጋቢት 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ለብልጽግና ፓርቲ የገቢ ማሰባሰቢያና የምስጋና ፕሮግራም ላይ ነው።

በዕለቱ ወደ 30 ደቂቃ ከወሰደው ንግግራቸው ውስጥ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥሪ ያቀረቡበትን ሐሳብ ያንጸባረቁት በንግግራቸው ማሳረጊያ ላይ ነው።

“ከጅምሩም የሚፎካከሩ ፓርቲዎች ወንድሞቻችን ናቸው ብለን እንደጀመርነው፤ የኛ ማሻት መርከቧም ሳትደናቀፍ ከመድረሻዋ እንድትደርስ ስለኾነ፤ ይህንን ሐሳብ የሚደግፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ግለሰቦች የብልጽግና ፓርቲ ከእናንተ ጋር ለመነጋገር፣ ለመተባበር ሙሉ ዝግጅት ካደረጋችሁ ለመዋሐድ ዝግጁ መኾኑን ልገልጽላችሁ እፈልጋለሁ” በማለት ጥሪ አቅርበዋል።

ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር እስከመዋሐድ የሚደርስ ፍላጎት መኖሩን በይፋ ያንጸባርቃል የተባለውን ይህንን ንግግራቸውን ለማጠናከር የተጠቀሙበት ቃል ብልጽግናዎች ከኛ ወዲህ ላሳር የማይሉ በመኾኑ ነው በማለት ነበር።

“በእኛ ውስጥ በእኛ ሐሳብ የሚሰበሰብ ኃይል፤ የሚደመር ኃይል የኢትዮጵያን ብልጽግና እንደሚያፋጥን የምናምን ከኾነ፤ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች በቀና ልብ ሐሳባችሁን፣ እውቀታችሁን ሰብስባችሁ መዋሐድ በምንችልበት ደረጃ ተዋሕደን መሥራት ይቻላል” ብለዋል።

መዋሐድ የማይቻል ከኾነ፤ መደጋገፍ ይቻላላ በማለትም ከውሕደት በመለስ መኾን ይቻላል ያሉትን ሐሳብ አንጸባርቀዋል።

በዚህ ጉዳይ ያላቸውን ሐሳብና መደምደሚያ ያደረጉት፤ “መደጋገፉም የማይኾን ከኾነ አዳዲስ የፖለቲካ አመራር ሥርዓት ከምርጫው በኋላ ለመላመድ እንዲያስችለን ጥላቻን፣ ስድብንና መወቃቀስን በመተው፤ ከተቻለ ከተቻለ አዳዲስ ሐሳብ በማምጣት፤ ካልተቻለም የእኛኑ ሐሳብ በራሳቸሁ ቋንቋ በመድገም በሐሳብ ብቻ እንድንነጋገር ላሳስባችሁ፤ ጥሪም ላቀርብላችሁ እፈልጋለሁ” በማለት ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ