በጫማ ማምረት ሥራ የሚታወቀው ኦኬ ጃማይካ ጫማ ሥራ አቆመ
ኦኬ ጃማይካ ጫማ ፋብሪካ
ምክንያቱ ለባንክ እዳ አበዳሪው ባንክ ፋብሪካውን በመረከቡ ነው
ኢዛ (ዓርብ ጥር ፲፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 24, 2020)፦ በጫማ ማምረት ሥራ ከሚታወቁ የአገር ውስጥ ፋብሪካዎች በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት ተርታ አንዱ የኾነውና ኦኬ ጃማይካ ጫማ ፋብሪካ ሥራ እንዳቋረጠ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።

የፋብሪካው ሥራ የተቋረጠው ከባንክ ብድር ጋር ተያይዞ፤ አበዳሪው ባንክ ፋብሪካውን በብድር መያዥያነት ይዞት ስለነበር ፋብሪካውን በመውረሱ እንደኾነ እነዚሁ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት በንፋስ ስልክ አካባቢ የሚገኘው ፋብሪካ ሥራ ማቆሙንና ሠራተኞቹም መሰናበታቸው ታውቋል። ፋብሪካው ሥራ ካቆመ ሳምንታት ተቆጥረዋል። ከፋብሪካው ሌላ የኦኬ ጃማይካ ጫማ መሸጫ ሱቆች መዘጋታቸውንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ፋብሪካው ወደ 30 ዓመታት ዕድሜ ያለው እንደኾነ ይነገራል። በባንክ እዳ አበዳሪው ባንክ ፋብሪካው የተያዘበት የኦኬ ጃማይካ ጫማ እንደ “Ok Jamaica“ ያሉ ሞዴል ጫማዎችን በማምረት የሚታወቅ ነው።
እንደምንጮቻችን መረጃ በፋብሪካው ሥራ ማቆም ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ ሠራተኞቹ ሥራ በማቆማቸው፤ ሠራተኞቹ ፋብሪካው ተገቢውን ክፍያና ደምዎዝ ሊሠጠን ይገባል በማለት ወደፍርድ ቤት እንደሚሔዱ ማስታወቃቸውን ለማወቅ ተችሏል። የኦኬ ጃማይካ ጫማ ሠራተኞቹ ከመቶ ሃምሳ በላይ ናቸው። (ኢዛ)



